የአልሻባብ ታጣቂዎች ድንበር አልፈው የፈፀሙት ጥቃት ዓላማ ምን ነበር?

የፎቶው ባለመብት, AFP
ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት የሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት ከወደቀ በኋላ በነበሩት ዓመታት የጎሳ ድጋፍ የነበራቸው የጦር አበጋዞች የበላይነትን ለመያዝ ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
በኋላም እነዚህ ኃይሎች ከጎሳ ባሻገር የሃይማኖት ቅርጽ የያዘ ኃይል በመፍጠር ጥንካሬ ማግኘት ጀምረው ነበር። በዚህም የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት የተባለው ስብስብ ተጽዕኖው እየሰፋ በአካባቢው አገራት ጭምር እንደስጋት መታየት ጀመረ።
ቡድኑ በተለይ ከኢትዮጵያ አንጻር የነበረው አመለካከትና ሲሰነዝራቸው የነበሩት ዛቻዎች በወቅቱ ኢትዮጵያ ወታደራዊ እርምጃ ምክንያት ሆኗል።
የኢትዮጵያ ሠራዊት ወደ ሶማሊያ ገብቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ቡድንን ከበርካታ ቁልፍ የሥልጣንና የኢኮኖሚ ማዕከላት ለማስወገድ ችሎ ነበር።
በዚህም የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ቡድኑ ተዳክሞ፣ አሁን ከሶማሊያ አልፎ ለአካባቢው አገራት ስጋት የሆነው አልሻባብ የተባለው የወጣቶች ቡድን ተመስርቶ፣ በሶማሊያ እና በጎረቤት አገራት ውስጥ ከባድ የሽብር ጥቃቶችን እየፈጸመ ነው።
ከትላልቅ ከተሞች ውጪ በርካታ የሶማሊያ አካባቢዎችን ተቆጣጥሮ የሚገኘው ይህ ታጣቂ ቡድን፣ በሶማሊያ ውስጥ ያልተቋረጠ ከባድ የቦምብ እና የሸምቅ ጥቃቶችን በመፈጸም ለበርካቶች ሞት ምክንያት ሆኗል።
ለአገሪቱ ሕዝብና መንግሥት ከባድ የደኅንነት ፈተና እንደሆነም አለ።
አልሻባብ ከሶማሊያ ባሻገርም በጎረቤት ኬንያ ውስጥ ዋና ከተማዋን ናይሮቢን ጨምሮ በተለያዩ ስፍራዎች ያልተጠበቁ እና ከፍተኛ ጉዳትን ያደረሱ የሽብር ጥቃቶችን በመፈፀም ኃላፊነቱን ወስዷል።
በተጨማሪም ከሶማሊያ ጋር ድንበር የማትጋራው ኡጋንዳም ከአልሻባብ ጥቃትና ዛቻ አልተረፈችም።
ሠራዊቷን ከሁሉ ቀድማ በሶማሊያ ያሰማራችው ኢትዮጵያም የቡድኑ ቀዳሚ ኢላማዎች ከሆኑት አገራት መካከል አንዷ ብትሆንም፣ እስካሁን ድረስ ከሙከራ የዘለለ ይህ ነው የሚባል ጥቃትን ለመፈጸም አልቻለም።
የኢትዮጵያ የደኅንነት ባለሥልጣናት በተለያዩ ጊዜያት ባወጧቸው ሪፖርቶች የአልሻባብ ጥቃቶችን ማክሸፋቸውንና አባላቱን መያዛቸውን ሲናገሩ ቆይተዋል።
ባለፈው ሳምንት ግን ቡድኑ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ተዋጊዎቹን ከሶማሊያ ድንበር አሻግሮ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት በማስገባት ጥቃት ፈጽሟል።
ይህም በኢትዮጵያ ላይ በአልሻባብ የተሞከረ ግልጽ ድንበር ዘለል ወታደራዊ ጥቃት ነው።

የፎቶው ባለመብት, AP
የአልሻባብ ጥቃት በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ
ባለፈው ረቡዕ ሐምሌ 13/2014 ዓ.ም. የአልሻባብ ታጣቂዎች ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር በምትዋሰንባቸው የድንበር ከተሞች ላይ ጥቃት ከፍተው ከባድ ውጊያ ተካሂዷል።
በቀድሞው ሸማቂ ቡድን የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) ከዚያም በኋላ በአልሻባብ እንቅስቃሴ ሳቢያ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር በምትዋሰንበት በረጅሙ የድንበር አካባቢ ሠራዊቷንና የክልል ልዩ ኃይልን በማሰማራት ጥብቅ ቁጥጥር ስታደርግ ቆይታለች።
ይህም አልሻባብ በቀጥታ ጥቃት ለመሰንዘር እንዲሁም ወደ አገሪቱ ሰርጎ ለመግባት ዕድልን አልሰጠውም።
በትግራይ ከተቀሰቀሰው ጦርነት በኋላ አብዛኛው የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ከአካባቢው ቢወጣም፣ በአስር ሺዎች እንደሚቆጠር የሚነገረው የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል በቦታው ተሰማርቶ የድንበር ጥበቃውን እየከናወነ ይገኛል።
ባለፈው ሳምንት አልሸባብ ጥቃቱ የጀመረው በቀጥታ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ አልነበረም።
ይህ ከአልቃኢዳ ጋር ግንኙነት አለው በሚባለው አልሻባብ ረቡዕ ዕለት የተፈጸመው ጥቃት፣ ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር በምትዋሰንበት ግዛት በኩል በሚገኙት ዬድ እና አቶ ላይ ነበር።
ይህንንም ተከትሎ ከኢትዮጵያ ጋር በሚዋሰኑት የሶማሊያ አካባቢዎች ነበሩ የተባሉት የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ አባላት ጋር ከባድ ውጊያ ተካሂዶ በሁለቱም ወገን ጉዳት መድረሱን የአካባቢው ነዋሪዎች እና ባለሥልጣናት መናገራቸው ተዘግቧል።
የአልሻባብ ጥቃት ግን እዚያው ሶማሊያ ድንበር ውስጥ አልቆመም።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች፣ ታጣቂዎቹ በበርካታ ተሽከርካሪዎች ተጭነው ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቀው በመግባት በሶማሌ ክልል አፍዴር ዞን ውስጥ ከሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባላት በተደረገው ከባድ ውጊያ ጉዳት መድረሱን አረጋጠዋዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በጥቃቱ የደረሰ ጉዳት
ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር በምትዋሰንበት በኩል የሚገኙት ዬድ እና አቶ በብዙ ኪሎ ሜትሮች ተራርቀው የሚገኙ ናቸው።
አልሸባብ አስቀድሞ በአቶ ላይ ጥቃት ካደረሰ በኋላ ሁለተኛው ጥቃት የፈጸመው በዬድ ላይ ነበረ።
የቡድን አባላት ከሶማሊያ ተሻግረው ወደ የኢትዮጵያ ግዛት ሲገቡ፣ በሶማሌ ክልል አፍዴር ዞን ውስጥ ውጊያ ተደርጎ በርካታ የአልሻባብ አባላት መገደላቸው ተገልጿል።
የተቀሩት ደግሞ የክልሉ ልዩ ኃይል በሐረገሌ ወረዳ ውስጥ በሚገኘው ሁልሁል በተባለው ስፍራ መከበባቸውን ቢቢሲ በወቅቱ ዘግቦ ነበር።
ለሦስት ቀናት በአልሻባብ እና በሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል መካከል በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ በተካሄደው ግጭት ሰላማዊ ሰዎችን ጨምሮ በርካታ ተዋጊዎች መገደላቸው እና ጥቂት የማይባሉ ተሽከርካሪዎች መቃጠላቸውን ነዋሪዎች ይናገራሉ።
ስለጥቃቱ የፌደራል መንግሥቱና የሶማሌ ክልል መስተዳደር ምንም ባላሉበት ወቅት የአልሸባብ ወታደራዊ ኦፕሬሽን ቃል አቀባይ አብዱያሲስ አቡ ሙሳብ በሶማሊያ ውስጥ ሁለት ቀበሌዎችን ቡድኑ በቁጥጥር ሥር ማድረጉን፣ በዚህ ውጊያም በርካታ የልዩ ፖሊስ ኃይል አባላትን መገደላቸውን ለሮይተርስ ተናግሮ ነበር።
የእስላማዊው ታጣቂ ቡድን ቃል አቀባዩ ግን በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ስለተፈጸመው ጥቃት እንዲሁም በቡድኑ ላይ ስለደረሰው ጉዳት ለዜና ወኪሉ ያለው ነገር አልነበረም።
ጥቃት መፈጸሙን በተመለከተ ከኢትዮጵያ በኩል ቀድሞ የተሰማው ከኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) ነበር።
ቡድኑ ሐሙስ ምሽት ባወጣው መግለጫ አሸባሪ ሲል የጠራው አልሻባብ ጥቃት ሰንዝሮ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት እንደደረሰና የክልሉ መንግሥት የሕዝቡን ደንኅንት ለማስከበር አስቸኳይ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል።
የሶማሌ ክልል ዘግየት ብሎ ድንበር አልፈው የገቡት የአልሻባብ ታጣቂዎች ለሦስት ቀናት ከክልሉ ልዩ ኃይል ጋር ባደረጉት ውጊያ ከ100 በላይ የሚሆኑት መገደላቸውን፣ 13 ተሽከርካሪዎቹ መውደማቸውንና ትጥቅና ስንቅ መማረኩንም አስታውቋል።

የፎቶው ባለመብት, Somali Regional Communication/fb
የጥቃቱ ምክንያትና ዓላማ
እስካሁን ድረስ የአልሻባብ ጥቃት ዓላማ እና ምክንያት ምን እንደሆነ ከቡድኑ ባይገለጽም፣ በሶማሌ ክልል ውስጥ ከጥቃቱ ቀደም ያሉ ክስተቶችና ተያያዥነት ያላቸው ሌሎች ሁኔታዎች ግን ይነሳሉ።
አንድ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አዛዥ ለሮይተርስ የጥቃቱ ምክንያት ሊሆን ይችላል ያሉትን ሲናገሩ፣ አንድ የአልሻባብ ታጣቂዎች አዛዥ የቡድኑን ህዋስ በኢትዮጵያ ውስጥ ለማቋቋም ወደ የኢትዮጵያ ድንበር ገብቶ መገደሉን አስታውሰዋል።
በተጨማሪም ከጥቃቱ ቀደም ብሎ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል በክልሉ በኤልከሬ ወረዳ ውስጥ በሚገኝ ሂሎ ማዶው በተባለ መንደር ውስጥ ባካሄደው አሰሳ በጉድጓድ ውስጥ ተቀብረው የነበሩ የተለያዩ አይነት የጦር ማሳሪያዎችን አግኝቶ ነበር።
ከዚህም ጋር በተያያዘም የአልሻባብ አባላት ናቸው የተባሉ ሰዎችን ፖሊስ በቁጥጥር ስር ያዋለ ሲሆን፣ አሁን አልሻባብ የሰነዘረው ጥቃትም ከዚሁ ጋር የተገናኘ ሊሆን ይችላል የሚል እምነት አለ።
ከቀናት ዝምታ በኋላ የሶማሌ ክልል የፀጥታ ምክር ቤት ቅዳሜ ምሽት ባወጣው መግለጫ፣ ወደ ሶማሌ ክልል አፍዴር ዞን የገባው “አሸባሪው የአልሸባብ ታጣቂ ቡድን ሁልሁል በሚባል ንዑስ ቀበሌ ከተከበበ በኋላ ለወሬ ነጋሪ ሳይተርፍ ሙሉ ለሙሉ ተደምስሷል” ብሏል።
ጨምሮም የአልሻባብ ታጣቂዎች አላማ በክልሉ በኤልከሬ ወረዳ በኩል አልፎ ወደ “ኦሮሚያ ክልል በመግባት ከሸኔ ሽብርተኛ ቡድን ጋር ለመገናኘት አልሞ ነበር” ሲል፣ ድንበር ጥሶ የገባው ቡድን ዓላማው በኦሮሚያ ክልል ከሚንቀሳቀሰው እና መንግሥት በሽብርተኝነት ከፈረጀው ቡድን ጋር ለመቀላለቀል እንደነበር ጠቅሷል።
ታጣቂው አስላማዊ ቡድን ግን እስካሁን ለምን በዚህ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ዘልቆ እንደገባ እና ስለደረሰበት ጉዳት ያለው ነገር የለም።
የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት አልሻባብ በርካታ ታጣቂዎችን በማሰማራት ድንበር አልፎ በመግባት ስለፈጸመው ጥቃት እስካሁን ያለው ነገር የለም።
ነገር ግን በተለያዩ ጊዜያት ይፋ የሆኑ የደኅንት መረጃዎች በአገር ውስጥ በሕገወጥነት ከተፈረጁት ቡድኖች ባሻገር አልሻባብ እና አይኤስ በአገሪቱ ውስጥ፣ በተለይም በዋና ከተማዋ ላይ ጥቃት ለማድረስ ያደረጉት ሙከራዎች መክሸፋቻውና ሰርገው ለመግባት የሞከሩ አባሎቻቸው በቁጥጥር ስር ስለማዋላቸው ሲገልጽ ቆይቷል።
ባለፈው ቅዳሜም እንዲሁ የአገሪቱ የፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ ባወጣው መግለጫ በአዲስ አበባ ውስጥ የሽብር ጥቃት ሊፈጽሙ ነበር ያላቸው የሶማሊያው እስላማዊ ቡድን አልሻባብ እና ዓለም አቀፉ የሽብር ቡድን አይኤስ 31 አባላት መያዛቸውን አመልክቷል።












