በአልሻባብ ከባድ ግብር ሳቢያ ገበሬዎች የእርሻ ሥራቸውን እየተዉ ነው ተባለ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የሶማሊያው ታጣቂ እስላማዊ ቡድን አልሻባብ በቁጥጥሩ ስር በሚገኙ አንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች በአርሶ አደሮች ላይ በጣለው ከፍተኛ ግብር ምክንያት የግብርና ሥራቸውን ትተው ወደሌሎች አካባቢዎች ለመሄድ እየተገደዱ መሆናቸው ተነገረ።
በአገሪቱ የተከሰተውን የድርቅ ሁኔታ እንዲከታተሉ በልዩ መልዕክተኝነት በአዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት የተሰየሙት አብዲራህማን አብዲሽኩር ዋርሳሜ እንዳሉት፣ ከአልቃኢዳ ጋር ግንኙነት ያለው አልሻባብ በጣለው ግብር ምክንያት አርሶ አደሮች እርሻቸውንና ቤታቸውን ጥለው ለመሰደድ ተገደዋል።
ለአስርታት ታይቶ በማይታወቅ ከባድ ድርቅ ከተመቱት የምሥራቅ አፍሪካ አገራት መካከል አንዷ በሆነችው ሶማሊያ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትት በቅርቡ አስታውቋል።
ልዩ መልዕክተኛው ይህንን የተናገሩት የአገሪቱ ፕሬዝዳንትና የሶማሊያ የተለያዩ ክልሎች መሪዎች በተገኙበት ሞቃዲሾ ውስጥ ለሁለት ቀናት በተካሄደው ስብሰባ ላይ ነው።
ባለሥልጣኑ ጨምረው እንደተናገሩት አገሪቱን ባጋጠማት ድርቅ ሳቢያ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ሶማሊያውያን ለችግር ተዳርገዋል። ከእነዚህም ውስጥ 250,000 የሚሆኑት የረሃብ አደጋ ተጋርጦባቸዋል።
“ሕዝቡ በድርቅ ምክንያት ብቻ ሳይሆን በደኅንነት ስጋት ጭምር ነው ከመንደራቸው እየተፈናቀሉ ያሉት። በአሸባሪው የአልሻባብ ቡድን ቁጥጥር ስር የሚገኙ አርሶ አደሮች የግብርና ሥራቸውን ከማከናወን ታግደዋል” ሲሉ ዋርሳሜ ተናግረዋል።
"አልሻባብ በአርሶ አደሮች ላይ በመሬት ዝግጅት፣ በዘር እና በምርት ስብሰባ ወቅት ጭምር ግብር ያስከፍላል። በዚህም ምክንያት ሰዎች የግብርና ሥራቸውን ማከናወን አልቻሉም። በተጨማሪም ከብቶቻቸውን ለመሸጥ የሚፍልጉ ሰዎች ከእንስሳቸው ዋጋ በላይ ግብር እንዲከፍሉ ይገደዳሉ።” ብለዋል።
ብዙ ጊዜ ሶማሊያ ውስጥ ድርቅ በሚከሰትበት ጊዜ ታጣቂው ቡድን አልሻባብ ገጽታውን ለመገንባት ሲል ለሕዝቡ እርዳታ የማቅረብ ሥራ ያከናውናል።
ባለፈው ጥር ወርም ቡድኑ “የድርቅ እርዳታ” አቅርቦት ዘመቻ መጀመሩን አስታውቆ ነበር።
እስላማዊው ታጣቂ ቡድን የጁባና ሸበሌ ወንዞች የሚያቋርጧቸውን በአገሪቱ በእጅጉ ለም የሆኑ አካባቢዎች ተቆጣጥሮ ይገኛል።
















