አሜሪካ ጦሯን ዳግም ወደ ሶማሊያ ለመመለስ ለምን ፈለገች?

አሜሪካ በጅቡቲ ትልቅ የጦር ሰፈር አላት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አሜሪካ ዳግም ከ500 የማያንሱ ወታደሮቿን ወደ ሶማሊያ ለመላክ ማቀዷ በግልጽ ለአዲሱ የአገሪቱ ፕሬዝደንት ያላትን ድጋፍ የሚያሳይ ነው።

በቀድሞ በሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ ፋርማጆ መንግሥት እና በድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር መካከል የነበረው አለመግባባት አሜሪካ ወታደሮቿን ከሶማሊያ እንድታስወጣ አድርጓታል።

አሜሪካ ዳግም ጦሯን ወደ ሶማሊያ ለመላክ መወሰኗ የትራምፕ አስተዳደር ውሳኔን የሚቀለብስ ነው።

አሜሪካ የቀድሞውን የሶማሊያ ፕሬዝደንት አስተዳደርም ሆነ እስላማዊ ታጣቂዎችን በመዋጋት ረገድ ያደረጉት ጥረት ውጤታማ አልነበረም ብላ ታስባለች።

ውሳኔውን የዩኤስ አፍሪካ ኮማንድ (አፍሪኮም) አሜሪካ በሶማሊያ "አነስተኛ" ቁጥር ያለው ጦር በሶማሊያ ማሰማራቷ የእስላማዊ ታጣቂዎች ጥቃት ለጨመረባት ሶማሊያ እረፍት የሚሰጥ ነው ብሏል።

የትራምፕን ውሳኔ ተከትሎ የተፈጠረውን የደኅንነት ክፍተት ለመሙላት ከጅቡቲ በመነሳት ወደ ሶማሊያ ገብተው ለሚወጡ የአሜሪካ ወታደሮችም ሥራ የሚያቀል አንደሆነ አፍሪኮም ገልጿል።

የአሜሪካ ጦር መውጣትን ተከትሎ በሶማሊያ ጥቃቶች ተበራክተዋል። 'ዘ አፍሪካ ሴንተር ፎር ስትራቴጂክ ስተዲስ' እንደሚለው የጦሩን መውጣት ተከትሎ በነበረው ዓመት በአል-ሻባብ የደረሱት ጥቃቶች ከ1771 ወደ 2072 አድገዋል።

ከፀጥታ አካላት ጋር የሚደረጉ ውጊያዎችም በ32 በመቶ ከፍ ብሏል። ባለፈው ወር ብቻ 450 የሚደርሱ የአል-ሻባብ ተዋጊዎች በደቡብ ሶማሊያ የሚገኝን የአፍሪካ ሕብረት ካምፕን በማጥቃት 40 የቡሩንዲ ወታደሮችን ገድለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሙያዎች ራሳቸውን ከአልቃይዳ ጋር ከሚያያይዙ ድርጅቶች አል-ሻባብ ጠንካራው መሆኑን ይገልጻሉ። ቡድኑ 12 ሺህ ተዋጊዎች እንዳሉት ይገምታሉ። ወርሃዊ ገቢውን ደግሞ 10 ሚሊዮን ዶላር ያደርሱታል።

“የአሜሪካ ወታደሮች ወደ ሶማሊያ መመለሳቸው ትልቅ ለውጥ ያመጣል” የሚሉት መቀመጫውን በሞቃዲሾ የሆነውና በደኅንነት ጉዳዮች ላይ የሚያተኩረው ሂራል ኢንስቲቲዩት ዳይሬክተር የሆኑት ሳሚራ ጋይድ ናቸው።

“ጦርነቱን ማሸነፍ ባያስችልም ለአዲሱ አስተዳደር ደኅንነት ቅድመ ሁኔታዎችን እንዲያመቻች ዕደል ይሰጣል” ይላሉ።

የአል-ሻባብ ታጣቂዎች

የፎቶው ባለመብት, AFP

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አፍሪኮም “ተባባሪ" ለሚላቸው ኃይሎች የአሜሪካ ጦር የሥልጠና፣ የማማከር እና ከፍ ሲልም የማስታጠቅ ድጋፍ ያደርጋል።

በርካታ የአል-ሻባብ አመራሮችን ዒላማ የማድረግ ሌላኛው በአሜሪካ ጦር ላይ የተጣለ ኃላፊነት ነው።

ቀደም ሲል የተደረጉ የአሜሪካ የአየር ጥቃቶች የቡድኑን እንቅስቃሴ አስተጓጉለዋል። መሪዎቹ እንደልብ እንዳይንቀሳቀሱ እና ታጣቂዎቹም ትልልቅ ጥቃቶችን እንዳይፈጽሙ አግዷል።

አንዳንዶች ግን በጦሩ መመለስ ውሳኔ ደስተኞች አይደሉም። ለዚህም እንደምክንያት በአሜሪካ የሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) ጥቃት ሲቪሎች ላይ ጉዳት መድረሱን ያነሳሉ።

“በአሜሪካ የአየር ጥቃት ሲቪሎች እየተገደሉ ነው” ያለችው በአልሻባብ የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት አባቷን ያጣችው እና ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የሆነችው ሃሊማ አህመድ ናት።

“የእባብን ጭንቅላት መቁረጥ ብዙ እባቦችን ነው የሚፈጥረው” ስትል በታጣቂው አመራሮች ላይ ብቻ ስላተኮረው ጥቃት ትገልጻለች።

በሌላ አጋጣሚ ደግሞ አሜሪካ ያሰለጠነቻቸው እና ያስታጠቀቻቸው ወታደሮች እርስ በርስ አፈሙዝ እስከመደጋገን ደርሰዋል።

እአአ በ2021 ከፊል ራስ ገዝ በሆነችው ፑንትላንድ የሚገኝ እና በአሜሪካ የሰለጠነ የፀረ-ሽብ ኃይል ተከፍሏል።

ሁለቱ ወገኖች ጦርነት የጀመሩት አሜሪካ ባስታጠቀቻቸው መሳሪያ ነው። ህጻናትን ጨምሮ ከ20 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።

የሶማሊያን የፀጥታ ኃይሎች በማሰልጠን እና በማስታጠቅ ላይ የምትገኘው አሜሪካ ብቻ አለመሆኗ ሌላው ችግር ነው።

በቅርቡ ወደ ሞቃዲሾ ያቀናችው የቢቢሲ ጋዜጠኛ ወታደሮች እና ፖሊሶች የተለያየ ልብስ እና መሣሪያ ይዘው ለመታዘብ ችላለች።

'ዳናብ' ወይም መብረቅ ብርጌድ በመባል የሚታወቁትና በአሜሪካ የሰለጠኑ ኮማንዶዎች በጣም ጨካኞች እንደሆኑ ይነገራል። ብዙውን ጊዜ ጥቁር ጭምብል እና ትልልቅ መሣሪያዎችን ይዘው ይቀመጣሉ።

'ጎርጎር' ወይም ንስሮች የሚባሉት ደግሞ የሚሰለጥኑት ሞቃዲሾ በሚገኘው የቱርክ የጦር ሰፈር ነው። የጦር ሰፈሩ ቱርክ ከግዛቷ ውጪ ያላት ትልቁ ወታደራዊ ተቋም ነው።

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ኳታር፣ የአውሮፓ ሕብረት፣ የአውሮፓ ሕብረት፣ ኤርትራ፣ ኡጋንዳ፣ ኬንያ፣ ጅቡቲ እና ሌሎችም ተሳትፈዋል።

ይህም በፀጥታ ኃይሉ ውስጥ ቅንጅት እንዳይኖር እንቅፋት ሆኗል። አንዳንዴ ደግሞ በአንድ አገር የሰለጠኑ ወታደሮች ከአንድ የፖለቲካ ቡድን ጋር ይሰለፋሉ።

እአአ ሚያዝያ 2021 ሞቃዲሾ ውስጥ በተለያዩ የፀጥታ ኃይሎች መካከል ከባድ ጦርነት ተከፈተ። ይህም እአአ በ1990ዎቹ ወደ ነበረው የእርስ በርስ ጦርነት እንዳያመራ ስጋት ፈጥሮ ነበር።

በመደበኛው ሠራዊት እና በፖለቲካዊ ወይም በጎሳ ላይ በተመሰረቱ ሚሊሻዎች መካከል ያለው ልዩነት በጣም ቀጭን ነው። አንድ ወታደር ዛሬ የአገሪቱን ጥቅም፣ ነገ ደግሞ የራሱን ጎሳ ወይም የፖለቲካ ቡድን ጥቅም ማስጠበቅ ላይ ሊያተኩር ይችላል።

የሶማሊያ ጦር በፖለቲካ እና በጎሳም ይከፋፈላል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከቻይና እና ሩሲያ አሜሪካ ‘መምረጥ’

ዩናይትድ ስቴትስ ወታደሮቿን ወደ ሶማሊያ መሰማራት ብቻ አይደለም ፍላጎቷ። ከ31 ዓመታት በፊት ከሶማሊያ የተገንጠለችው እና ዓለም አቀፍ ዕውቅና ባላገኘችው የሶማሊላንድ ሪፐብሊክ ዓይኗን ስትጥል ቆይታለች።

የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢሳ ካይድ “በመጋቢት ወር በአሜሪካ ተጋብዘን ነበር። በጣም ውጤታማ ጉዞ ነበርን” ብለዋል።

"ዋናው ትኩረት በደኅንነት እና በመረጃ ልውውጥ ላይ መቀራረብን ለመፍጠር ነው።”

ከሁለት ወራት በኋላ ደግሞ አሜሪካ ምላሽ ሰጠች። የአፍሪኮም አዛዥ እና በአፍሪካ ከፍተኛ ወታደራዊ ኃላፊዋን ጄኔራል ስቴፈን ታውንሴንድን ወደ ሶማሊላንድ ላከች።

ጄነራሉ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት በሶቪየት ኅብረት የተገነባውንና አራት ኪሎ ርዝማኔ ያለውን የአውሮፕላን ማረፊያ ጎብኝተዋል። አሜሪካ በበርበራ የጦር ሰፈር ልትገነባ ነው የሚል ወሬ በሶማሊላንድ እየተናፈሰ ነው።

"አሁን ማለት የምችለው የአሜሪካ ጉብኝቶች እየበዙ እንደሚሄዱ ነው" ብለዋል።

"የእኛን የፀጥታ ኃይሎች እና የባሕር ዳርቻ ጠባቂዎችን በማሰልጠን እንደሚያግዙን እንጠብቃለን። ቻይና እና ሩሲያን ጨምሮ ብዙ ኃያላን አገራት በሶማሊላንድ አሻራቸውን ለማሳረፍ ፍላጎት አላቸው። እኛ ግን በጋራ እሴቶቻችን ምክንያት አሜሪካንን እንመርጣለን።"

እንደ አፍሪኮም ገለጻ የጄኔራሉ የጉብኝት ዓላማ "ለድንገተኛ ጊዜ ለመዘጋጀት፣ ለልምምድ ወይም እንደ አስፈላጊነቱ የኃይል አሰፋፈርን ለማስተካከል የሚችሉበትን ቦታዎችን ለመገምገም" ነው።

ዩናይትድ ስቴትስ በሶማሊላንድ ያላት ፍላጎት እንዲጨምር የሚያደርጉ ብዙ ምክንያቶች አሉ።

አካባቢው በጣም ስልታዊ የሆነ ቦታ ላይ የሚገኝ ነው። 800 ኪ.ሜ የሚረዝመው የባሕር ዳርቻዋ በጣም ብዙ መርከቦች ከሚመላለሱበት አንዱ ነው።

ትንሿ ጎረቤት አገር ጂቡቲ የቻይናው እና የአሜሪካን ጨምሮ የብዙ አገራትን ወታደራዊ የጦር ሰፈሮች አቅፋ ይዛለች።

በርበራ ጥሩ አማራጭ ሆና ቀርባለች። መረጋጋት ለራቃቸው የመን፣ ሶማሊያ እና ኢትዮጵያም በቅርብ ርቀት ላይ ትገኛለች። አገራቱ ‘በፀረ ሽብር ጦርነት’ የአሜሪካ ወዳጆች ቢሆኑም በውስጣዊ ግጭቶች እየተናጡ ነው።

“ዕውቅና ያላገኘችው ሚጢጢዋ አገራችን ዓለም የተረጋጋች እንድትሆን ትልቅ ሚና እየተወጣች ነው። ሁከት በበዛበት ክልል ዘብ መቆም የቻልን የመረጋጋት ምልክት ነን” ያሉት ካይድ ናቸው።

ዩናይትድ ስቴትስ ከሶማሊላንድ ጋር የበለጠ መቀራረብ ካለባት በጥንቃቄ መራመድ አለባት። የግዛቴ አካል ናት ለምትለው ሞቃዲሾ እርምጃው ቁጣ ሊፈጥር ይችላል።

በጣም ተለዋዋጭ በሆነው የአፍሪካ ቀንድ እና የቀይ ባሕር ቀጠና መረጋጋቱን ለማሻሻል፤ በአልሸባብ ላይ የተጀመረውን ጦርነት በድል አጠናቆ ከዓለም አቀፍ ተቀናቃኞቿ እኩል ከመራመድ አንፃር ዩናይትድ ስቴትስ በሁለቱም አገራት ላይ ከማተኮር ሌላ አማራጭ የላትም።