አሜሪካ ሶማሊያ ውስጥ በፈጸመችው የአየር ጥቃት የአልሻባብ ታጣቂዎችን መግደሏ ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, AP
አሜሪካ ሶማሊያ ውስጥ የአልሻባብ ታጣቂዎችን ኢላማ ያደረገ የአየር ጥቃት ፈጽማ በቡድኑ ላይ ጉዳት ማድረሷን የሶማሊያ መንግሥት አስታወቀ።
ከሶማሊያ የማስታወቂያ ሚኒስቴር የወጣ መግለጫ እንዳመለከተው “ከአገሪቱ መንግሥት ጋር በመቀናጀት” ትናንት አርብ በተፈጸመው የአየር ጥቃት አምስት የአልሻባብ ታጣቂዎች ተገድለዋል።
የሶማሊያ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የአየር ጥቃቱን በተመለከተ በትዊተር ላይ ባወጣው መግለጫ፣ እርምጃው የአልሻባብ ታጣቂዎች ከኪስማዮ ከተማ ደቡብ ምዕራብ በሚገኝ አካባቢ ያለ የሶማሊያ መንግሥት ኃይሎች ላይ ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ ነው።
ይህ ጥቃት የተፈፀመው አሜሪካ ወታደሮቿን ወደ ሶማሊያ መልሳ ለማስፈር ከወሰነች ከሳምንታት በኋላ ነው። ፕሬዝዳንት ባይደን 500 የሚሆኑ የልዩ ተልዕኮ ወታደሮቻቸው ወደ ሶማሊያ እንዲሰማሩ የወሰኑት በሶማሊያ ከተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በኋላ ነበር።
ለሁለተኛ ጊዜ የተመረጡት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት አሜሪካ መልሳ ወታደሮቿን በአገራቸው ለማሰማራት መወሰኗን ደግፈውታል።
ከሶማሊያ መንግሥት የማስታወቂያ ሚኒስቴር የወጣው መግለጫ፣ ሞቃዲሾ እና ዋሽንግተን አልሻባብን በጋራ ለመዋጋት ቁርጠኛ ናቸው ብሏል።
አሜሪካ ከሁለት ዓመታት በፊት በቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትዕዛዝ ወታደሮቿን ከሶማሊያ ከማስወጣቷ በፊት ተመሳሳይ የአየር ጥቃቶችን በታጣቂው እስላማዊ ቡድን ላይ ስትፈጽም ነበር።
ቀደም ሲል በሰው አልባ በተፈጸሙ ጥቃቶች ከፍተኛ የአልሻባብ መሪዎች መገደላቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ በተመሳሳይም በርካታ ሰላማዊ ሰዎች በጥቃቶቹ እንደተገደሉ ይነገራል።
አርብ ዕለት በተፈጸመው ጥቃት አምስት ያህል የአልሻባብ ተዋጊዎች መገደላቸውና በሰላማዊ ሰዎች ላይ ግን የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን የሶማሊያ መንግሥት አሳውቋል።
እስካሁን የአሜሪካ መከላከያ መሥሪያ ቤትም ሆነ ወታደራዊ ባለሥልጣናት ሶማሊያ ውስጥ ስለተፈጸመው የአየር ጥቃት ያሉት ነገር የለም።
የአየር ጥቃቱ አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐመድ ወደ ሥልጣን ከመጡና አሜሪካ ሠራዊቷን ወደ አፍሪካዊቷ አገር ለመመለስ ከወሰነች በኋላ የመጀመሪያው ነው።












