አሜሪካ ሠራዊቷን መልሳ ሶማሊያ ውስጥ እንድታሰማራ ፕሬዝዳንት ባይደን ፈቀዱ

የአሜሪካ ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በመቶዎች የሚቆጠሩ የአሜሪካ ወታደሮች እንደገና ወደ አፍሪካ ቀንድ አገሯ ሶማሊያ እንዲሰማሩ ፈቃድ መስጠታቸው ተዘገበ።

ይህ የጆ ባይደን ውሳኔ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ 700 የሚጠጉ ሶማሊያ ውስጥ ሰፍረው የነበሩ ሁሉም ወታደሮቻቸው አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ያደረጉበትን እርምጃ የሚቀለብስ ነው።

አሁን ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ምን ያህል ወታደሮች ወደ ሶማሊያ እንደሚያሰማሩ ባይታወቅም፣ ነገር ግን ወታደሮቹ የልዩ ተልዕኮ ኃይል አባላት እና እዚያው ሶማሊያ ውስጥ የሚሰፍሩ እንደሚሆኑ ተገልጿል።

ፕሬዝዳንት ባይደን የአሜሪካ ሠራዊት አባላት ዳግም ሶማሊያ ውስጥ እንዲሰማሩ ከመፍቀዳቸው ባሻገር፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው ተጠርጣሪ የአልሸባብ መሪዎችን ኢላማ ያደረገ ዕቅድ ማጽደቃቸው ተነግሯል።

ይህ የፕሬዝዳንቱ ውሳኔ አሜሪካ ሠራዊቷን ከአፍጋኒስታን ካስወጣች በኋላ ጥያቄ ውስጥ ገብቶ የነበረውን የፀረ ሽብርተኝነት ዘመቻን መልሶ እንዲያንሰራራ የሚያደርግ ነው ተብሏል።

እስላማዊው ታጣቂ ቡድን አልሻባብ ተደጋጋሚ ጥቃት በሚፈጽምባት ሶማሊያ፣ ቡድኑ አስከ 10ሺህ የሚደርሱ አባላት እንዳሉት የአሜሪካ የደኅንነት ባለሥልጣንት ይገምታሉ።

ምንም እንኳን አልሻባብ ሶማሊያ ውስጥ የሚንቀሳቀስ ቢሆንም፤ የቡድኑ አንዳንድ አባላት ግን በአሜሪካ ላይ ጥቃት የመፈጸም ፍላጎት እንዳላቸው ባለሥልጣናቱ ይናገራሉ።

ከሁለት ዓመት በፊትም ኬንያ ውስጥ በሚገኝ የአሜሪካ የአየር ኃይል ሰፈር ላይ አልሻባብ ከባድ ጉዳት ያደረሰ ጥቃት መፈጸሙ ይታወሳል።

ለሦስት አስርት ዓመታት በቀውስ ውስጥ በቆየችው ሶማሊያ አሜሪካ ወታደሮቿን ለማሰማራት መወሰኗ የተሰማው፣ ከአንድ ዓመት በላይ የተራዘመው ምርጫ ተካሂዶ ሶማሊያ አዲስ ፕሬዝደንት መምረጧን ተከትሎ ነው።