ሕዝቡ የማይመርጥበት የሶማሊያው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ

የሞቃዲሾ ጎዳናዎች

የሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾ ጎዳናዎች እሁድ በሚካሄደው ምርጫ በሚወዳደሩት ፕሬዝዳንታዊ ዕጩዎች ትላልቅ የማስታወቂያ ሰሌዳዎች ተንቆጥቁጣለች።

በመኪኖች በተጨናነቀው የትራፊክ እንቅስቃሴም አላፊው አግዳሚው ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው ምርጫ ከመድረሱ በፊት የተሰቀሉትን ፖስተሮችን ይቃኛሉ።

ነገር ግን ሕዝቡ አይመርጥም።

ሕዝብ የማይመርጥበት ምርጫ እንዴት? ልትሉ ትችላላችሁ።

ለዚህም ምክንያቱ ሶማሊያ ውስብስብ እና ቀጥተኛ ያልሆነ የፖለቲካ ሥርዓት ስለምትከተል እና የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ስለማይወዳደሩ ነው።

ይልቁንም 275 አባላት ያሉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሚመረጡት በክልል ባለሥልጣናት በተሰየሙ የጎሳ የአገር ሽማግሌዎችና የሲቪክ ማኅበራት አባላት ነው።

በተጨማሪም የሶማሊያን አምስት ክልላዊ መንግሥታት የሚወክል 54 አባላት ያሉት ከፍተኛ ምክር ቤት (ሴኔት) አለ።

ከዚያም የሁለቱም ምክር ቤቶች የፓርላማ አባላት 16.3 ሚሊዮን የሚሆነውን የሶማሊያን ሕዝብ የሚመራውን ፕሬዚዳንት ይመርጣሉ።

ፕሬዚዳንታዊ ዕጩዎቹ

ፕሬዚዳንታዊ ጩዎቹ እነማን ናቸው?

ሶማሊያ ለረጅም ጊዜ የተጓተተውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዛሬ እሁድ ግንቦት 07/2014 ዓ.ም. ታካሂዳለች። ይህም መጀመሪያ ሊደረግ ከታቀደው ከአንድ ዓመት በላይ ዘግይቶ ነው።

በሥልጣን ላይ የሚገኙትን መሐመድ አብዱላሂ መሐመድ ወይም ፋርማጆን ጨምሮ በፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ለመወዳደር 39 ዕጩዎች ቀርበዋል።

በአውሮፓውያኑ 1991 በሲያድ ባሬ የሚመራው የሶሻሊስት መንግሥት ከተገረሰሰ ወዲህ ከፍተኛው ለፕሬዝዳንትነት የሚወዳደሩ ዕጩዎች ቁጥር ነው ተብሏል።

ከዕጩዎቹ መካከል ሁለቱ የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች፣ ሻሪፍ ሼህ አህመድ እና ሐሰን ሼክ መሐሙድ እንዲሁም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሐሰን አሊ ኬሬ ይገኙበታል።

ሌላኛዋ ዕጩ ፋውዚያ ዩሱፍ አደም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ያገለገሉ ሲሆን፣ ብቸኛዋ ሴት ዕጩ ተወዳዳሪ ናቸው።

የወቅቱ የሶማሊያ ከፊል ራስ ገዝ የፑንትላንድ ክልል ፕሬዝዳንት ሰኢድ አብዱላሂ ዴኒም ውድድሩን ተቀላቅለዋል።

የሚመረጠው ፕሬዚዳንት ለአራት ዓመታት የሚያገለግል ሲሆን እንደገና መመረጥም ይችላል።

ይሁን እንጂ ቀጥተኛ ባልሆነ የድምፅ አሰጣጥ ሥርዓት በአውሮፓውያኑ 2000 ከተጀመረ ወዲህ አንድም የሶማሊያ ፕሬዝዳንት በድጋሚ አልተመረጠም።

አብዱላሂ መሀመድ ወይም ፋርማጆ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ለምን ተራ ዜጎች አይመርጡም?

ይህ ሁኔታ በሶማሊያ ያለውን የጎሳ ኃይል የሚያሳይ ነው። የምዕራባውያን አይነት ዲሞክራሲ ባልሰፈነበት ማኅበረሰብም የጀርባ አጥንት ናቸው።

በአውሮፓውያኑ 1991 በሶማሊያ የማዕከላዊ መንግሥት መውደቅን ተከትሎ አገሪቱ መንግሥት አልባ ሆና የቆየች ሲሆን ይህንንም ክፍተት የጎሳ መሪዎች ሞልተውታል።

በሶማሊያ ጎሳዎች መካከል ከፍተኛ ፉክክር ስላለ ሥርዓቱ በሥልጣን ክፍፍል ቀመር ላይ የተመሰረተ ሲሆን፣ አራቱ ትላልቅ ጎሳዎች እኩል ቁጥር ያላቸው የፓርላማ መቀመጫዎችን ሲይዙ ቀሪዎቹ ጎሳዎች አንድ ላይ ተጣምረው ግማሹ የፓርላማ መቀመጫ ይሰጣቸዋል።

ይህም ሁኔታ የሶማሊያ ጎሳ ተወካዮች በአገሪቱ አድራጊ ፈጣሪ እንዲሁም የአገሪቱን መሪ ወደ ሥልጣን የሚያመጡ ኃያላን ያደርጋቸዋል።

ሰንደቅ አላማ የያዘች ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሁለቱን ምክር ቤቶች ምርጫ ተከትሎ ወደ 300 የሚጠጉ የፓርላማ አባላት ቃለ መሃላ ፈፅመዋል።

ምርጫዎቹ መጠነ ሰፊ ሙስና፣ ሥልጣንን አላግባብ የተጠቀሙበት እና የምርጫ ሕግጋት ችላ የተባሉበት ነው ተብሏል።

በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ልዑካንን ለመግዛት በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ወጪ ተደርጓል ተብሎ ይታመናል።

እንደ አለመታደል ሆኖ አገሪቱ ሙስናን የሚቆጣጠሩ ተቋማት የሏትም።

ኳታር በሶማሊያ ፖለቲካ መድረክ ዋና ተዋናይ ነች።

ተንታኞች እንደሚናገሩት በአውሮፓውያኑ 2017 የፕሬዚዳንት ፋርማጆ የምርጫ ዘመቻን ወቅት ኳታር በብቸኝነት ከፍተኛ ድጋፍ ያደረገች ሲሆን ከአስተዳሩም ጋር ጠበቅ ያለ ግንኙነት ነበራት።

ለምን ይህን ያህል ጊዜ ዘገዬ?

የፕሬዚዳንት ፋርማጆ የሥልጣን ወቅት በአውሮፓውያኑ የካቲት 2021 ቢጠናቀቅም በነበረው የፖለቲካ አለመግባባት በሥልጣን ላይ ቆይተዋል።

ለፓርላማ አባላት የነበረው ምርጫ ዝግጅት አለመኖር ምርጫውን ያዘገየው ሲሆን እሳቸውም ሆነ ሕግ አውጪዎች የመምራት ሥልጣን ባይኖራቸውም እየመሩ እንዲቆዩ አድርጓቸዋል።

በግጭት የምትናጠው ሶማሊያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፓርላማ ምርጫው በመጨረሻ የተካሄደው በምዕራባውያን ለጋሾች ግፊት ነው። አሜሪካ የምርጫውን ሂደት እያዘገዩ ነው ያለቻቸውን ባለሥልጣናት ቪዛ አግዳለች ።

ምርጫው ከታኅሣሥ እስከ መጋቢት ድረስ አራት ወራትን አስቆጥሯል።

በግንቦት ወር አጋማሽ ምርጫው ካልተጠናቀቀ ለሶማሊያ የሚሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ ሊያቆም እንደሚችል ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) አስታውቋል።

አዲሱ መንግሥት ሥልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ ድርቅን ጨምሮ የሶማሊያን ተግዳሮቶች መፍታት ይኖርበታል።

ድርቁ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ የተባባሰ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የረድዔት ድርጅቶች ረሃብ ሊከሰት እንደሚችል እያስጠነቀቁ ነው።

በአሁኑ ወቅት ከ3.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን 1.4 ሚሊዮን ህጻናት ለከፍተኛ የምግብ እጥረት ተጋልጠዋል።

ምዕራባውያን በሶማሊያ ያላቸው ፍላጎት ምንድን ነው?

ምዕራባውያን ዋናው ጭንቀታቸው የታጣቂ እስላማዊ ቡድን እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ ማንሰራራት ነው። ሶማሊያ የአል-ሸባብ ማዕከል ስትሆን የአልቃይዳ አጋር የሆነው አልሸባብ በአፍሪካ ውስጥ በጣም አደገኛ ነው ተብሎ ይታሰባል።

ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት በአሜሪካ የሚደገፉ የኢትዮጵያ ወታደሮች የእስልምና ፍርድ ቤቶች ሕብረትን ከሥልጣን ለማውረድ ዋና ከተማይቱን ሞቃዲሾን ከወረሩ በኋላ የታጣቂ እስልምና እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ ተንሰራፍቶ ይገኛል።

የሶማሊያ የፓርላማ አባላት

የፎቶው ባለመብት, BBC/ Ibrahim Adan

የእስልምና ፍርድ ቤቶች ሕብረት መሸነፍ አልሸባብን እንዲጠናከር ረድቶታል፤ የአልሻባብ ታጣቂዎች "ወራሪዎቹን" ለማባረርም ቃል ገቡ።

በአሁኑ ወቅት አልሸባብ በርካታ የሶማሊያ አካባቢዎችን ተቆጣጥሮ የሚገኝ ሲሆን መንግሥትን ለመጣል እና እስላማዊ አገዛዝ ለመመስረት በማለም ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ይፈጽማል።

በአውሮፓውያኑ 2012 እና 2016 ምርጫ አልሸባብ የጎሳ ሽማግሌዎችን ከእስልምና እምነት ውጪ በሆነው ምርጫ ተሳትፈዋል በሚል ካወገዛቸው በኋላ የዛተባቸው ሲሆን አልፎ ተርፎም የታገቱም ነበሩ።

በአሁኑ ምርጫ የአልሸባብ ድምጽ ያልተሰማ ሲሆን ምክንያቱ አባላቱ ወይም ደጋፊዎቹ በድብቅ የፓርላማ መቀመጫ ፈልገው ከውስጥ ሆነው ሥርዓቱን ለመናድ ሊገቡ ስለሚችል ስጋት እንዳይፈጠር በሚል ነው።

ይህንንም ጉዳይ የጎረቤት አገር ጂቡቲ ፕሬዝዳንት ኦማር ጉሌህ ስጋታቸውን በይፋ ገልጸዋል "አልሸባብ በተዘዋዋሪ የሚቆጣጠረው ፓርላማ እንዳይኖር እሰጋለሁ፤ ምክንያቱም የአንዳንድ የፓርላማ አባላትን ድጋፍ ሊገዙ ይችላሉ" ብለዋል።

አንዳንድ ተንታኞች ፕሬዚዳንት ጉሌህ አልሸባብ ፓርላማውን በተዘዋዋሪ ይቆጣጠረዋል ማለታቸው የተጋነነ ነው ያሉ ሲሆን፣ ነገር ግን በሶማሊያ ውስጥ ትልቅ የፖለቲካ ኃይል ስለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም።

ሶማሊያ ዲሞክራሲያዊ አገር ልትሆን ትችላለች?

በሶማሊያ የፖለቲካ ሥልጣን ክፍፍል ሂደት ውስጥ ተጽእኖ ያላቸው ወገኖች በዚህ ዓመት ሕዝብ የሚመርጥበት ሥርዓት በዘንድሮው ምርጫ እንደሚዘረጉ ከረጅም ጊዜ በፊት ተስማምተው የነበረ ቢሆንም ቃላቸውን ሳይፈጽሙ ቀርተዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና አዲስ ሕገ መንግሥት በሕዝበ ውሳኔ ማጽደቅን ጨምሮ ለዚህ የሚያስፈልጉ ዋና ዋና መስፈርቶች ባለሟሟላታቸው ይህ የሚያስደንቅ አልነበረም።

በርካታ ግዙፍ ፈተናዎች የሚገጥሙት የቀጣዩ መንግሥት ቀዳሚ ጉዳይ ምን ያህል እንደሚሆን ግልጽ አይደለም።