ሶማሊያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በተባለለት ጊዜ ማካሄድ ሳትችል ቀረች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሶማሊያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ማካሄድ በነበረባት ወቅት ባለማካሄዷ የፖለቲካ ቀውስ ይገጥማታል ተብሎ ተፈርቷል። ሶማሊያ ምርጫ ማካሄድ የነበረባት ዛሬ ሲሆን የፕሬዝዳንት አብዱላሂ ፎርማጆ የሥልጣን ዘመንም በዛሬ ዕለት ይጠናቀቃል።
የፌደራል መንግሥቱ እና የክልል መንግሥታት ምርጫ ማካሄድ ስለሚቻልበት መንገድ እያደረጉት የነበረው ውይይት አርብ እለት ያለውጤት ተበትኗል። ዛሬ፣ ሰኞ መግለጫ ያወጡት ለፕሬዝዳንትነት የሚፎካከሩት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የፕሬዝዳንት ፎርማጆ የሥልጣን ዘመን በማብቃቱ እውቅና እንደማይሰጧቸው ገልፀዋል።
አክለውም የሁለቱ ምክር ቤቶች አፈ ጉባዔዎች የተካተቱበት፣ የክልል አስተዳደሮችና አጋሮቻቸው በጋራ በመሆን እስከ ምርጫ ድረስ የሚያስተዳድር የሽግግር መንግሥት እንዲመሰረት ጠይቀዋል።
የሶማሊያ ጦርንም ከፕሬዝዳንት ፎርማጆ ማንኛውንም ትዕዛዝ እንዳይቀበል ጥሪ አስተላልፈዋል።
ሶማሊያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ምርጫ ማካሄድ የነበረባት በታሕሳስ ወር ቢሆንም የፌደራል መንግሥቱ ከክልል አስተዳደሮች ጋር በገባው እሰጥ አገባ ምክንያት አልተካሄደም።
የተለያዩ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች በፌደራል እና በክልል መንግሥታት መካከል የተቋረጠው ንግግር እንዲቀጥልና ምርጫ በተቻለ ፍጥነት እንዲካሄድ እየጠየቁ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ባወጠው መግለጫ ላይ እንዳለው ከዚህ ቀውስ ለመውጣት ያለው ብቸኛ መፍትሔ የተቋረጠውን ድርድር ማስቀጠል ነው።
አሜሪካም ተመሳሳይ ይዘት የያዘ መግለጫ አውጥታለች።
የተባበሩት መንግሥታት ፖለቲከኞች የሕዝቡን ፍላጎት ያማከለ ውሳኔ በፍጥነት እንዲወስኑ ጠይቋል።












