ፕሬዝደንት ባይደን፡ ለትራምፕ የአገር ምስጢር መነገር የለበትም

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን

የፎቶው ባለመብት, CBS

ፕሬዝደንት ጆ ባይደን የአገር ሚስጥር ለቀድሞ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ መነገር የለበትም አሉ።

ጆ ባይደን የቀድሞ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የአገር ሚስጥር መስማት የለባቸውም ያሉት ትራምፕ “የማይገመት ባህሪ” ስላላቸው ነው ብለዋል።

አሜሪካ በተቀማጩ ፕሬዝደንት ፍቃድ ለቀድሞ የአገሪቱ ፕሬዝደንቶች አገራዊ ጉዳዮች ላይ ገለጻ የማደረግ ልምድ አላት።

ባይደን አስተዳደራቸው ለቀድሞ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የጸጥታ ጉዳዮችን በተመለከተ ገለጻ እንደሚያደርግ ሲጠየቁ፤ “ይህ የሚሆን አይመስለኝም” ሲሉ መልሰዋል።

ባይደን የትራምፕን “መገመት የማይቻል ባህሪ” ከግምት በማስገባት ክልከላ እንዳደረጉ ተናግረዋል።

ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ትራምፕ ሚስጥራዊ ጉዳዮች ገለጻ ቢደረግላቸው ምን ይፈጠራል ብለው እንደሚሰጉ ሲጠየቁ ቀጥተኛ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ይሁን እንጂ ባይደን ትራምፕ አገራዊ ሚስጥር ቢነገራቸው፤ ሚስጥሩን ለሌሎች ሳያጋሩ ይዘው ይቆያሉ ብሎ መገመት እንደማይቻል ጠቁመዋል።

“ለእርሳቸው የደህንነት ገለጻ ማድረጉ ጥቅሙ አይታየኝም። ለእርሳቸው ገለጻ ማድረጉ ምን የሚጨምረው ፋይዳ አለ? አምልጧቸው የሆነ ነገር ካላሉ በስተቀር” ሲሉ ፕሬዝደንት ባይደን ተናግረዋል።

ትራምፕ በስልጣን ዘመናቸው ከአገሪቱ ደህንነት ሰዎች ጋር እስጠ አገባ ውስጥ ቆይተዋል። በአራት ዓመት የፕሬዝደንትነት ዘመናቸው ስድስት የብሔራዊ ደህንነት ዳይሬክተሮችን ቀያይረዋል።

ትራምፕ የአገራቸው ደህንነት ኤጀንሲ ሩሲያ በ2016 የአሜሪካ ምርጫ ጣልቃ ገብታለች ማለቱ አበሳጭቷቸው ነበር። የአሜሪካ ደህንነት በኢራን ላይ በቂ እርምጃ አልወሰደም ሲሉም በተደጋጋሚ ተችተዋል።

እአአ 2017 ላይ ደግሞ ትራምፕ የኢስላሚክ ስቴት ኦፕሬሽንን በተመለከተ ለሩሲያ የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ጥብቅ ሚስጢራዊ መረጃን አሳልፈው ሰጥተዋል። ይህም በበርካታ የአሜሪካ ደህንነት ሹሞች ዘንድ እንደ ክህደት ተቆጥሮ ነበር።