የአሜሪካ ምርጫ 2020፡ ጆ ባይደን ከውሻቸው ጋር ሲጫወቱ ወድቀው ተጎዱ

ጆ ባይደን

የፎቶው ባለመብት, DELAWARE HUMANE ASSOCIATION

ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ከውሻቸው ጋር ሲጫወቱ ወድቀው መጎዳታቸውን ዶክተራቸው አሳወቁ።

የ78 ዓመቱ ባይደን ቅዳሜ ዕለት ነው ከውሻዎቻቸው ጋር ሲጫወቱ የወደቁት ተብሏል።

ተመራጩ ፕሬዝደንት አዳልጧቸው ከወደቁ በኋላ ጉልበታቸው ላይ ጉዳት ገጥሟቸዋል።

ዴሞክራቱ ባይደን በተጎዱ በቀጣዩ ቀን ዴልዌር ውስጥ ያለ የአጥንት ሐኪም መጎብኘታቸው ታውቋል።

የግል ሐኪማቸው ኬቪን ኦ'ኮነር ተመራጩ ፕሬዝደንት ኤክስ-ሬይ ተነስተው አጥንታቸው መሰንጠቁን አውቀናል ብለዋል።

ዶክተሩ እንዳሉት ባይደን በቀኝ እግራቸው ጉልበት አካባቢ ሁለት ትንናሽ መሰንጠቅ ይታያል።

ፕሬዝደንት ትራምፕ "ጨርሶ ይማርዎ" ሲሉ በትዊተር ግድግዳቸው ላይ ፅፈዋል።

ሪፐብሊካኑ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕን ረትተው ወደ ሥልጣን እየመጡ ያሉት ባይደን ከሰኞ ጀምሮ ስለሚመሯት አገር ዕለታዊ ገለፃ ማግኘት ይጀምራሉ ተብሎ ነበር።

ባለፈው ወር 78 ዕድሜያቸውን የደፈኑት ባይደን በአሜሪካ ታሪክ አዛውንቱ ፕሬዝደንት ሆነው ነው ቀጣይ ጥር ሥልጣን የሚጨብጡት።

ይህን ተከትሎ የተመራጩ ፕሬዝደንት ወዳጆችና ተቃዋሚዎች ጉዳዩን ቅርበት እየተከታተሉት ይገኛሉ።

ዶክተራቸው፤ ባይደን ወደ ጤናቸው እየተመለሱ ይገኛሉ ብለዋል።

ባለፈው ታኅሳስ ዶክተራቸው በለቀቁት መግለጫ ጆ ባይደን የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሆነው ለማግልገል ምንም የሚያንሳቸው ነገር የለም ብለው ነበር።

ባይደን ቻምፕ እና ሜጀር ሲሉ ስም ያወጡላቸውን ሁለት ውሾች ይዘው ነው ወደ ነጩ የአሜሪካ መንግሥት መቀመጫ ቤተመንግሥት ለመግባት ያቀዱት።

ውሾቹ 'ጀርመን ሼፐርድ' የተሰኘ ዝርያ ያላቸው ናቸው ተብሏል።

ተመራጩ ፕሬዝደንት እና ባለቤታቸው ጂል ባይደን ከሁለት ዓመት በፊት ነበር ሜጀርን ለማሳደግ ወስነው የወሰዱት።

ነገር ግን ቻምፕ ዋይት ሐውስ ብርቁ አይደለም።

ጆ ባይደን የኦባማ ምክትል በነበሩ ጊዜ በዋይት ሐውስ የተከረከመ ሳር ላይ ሲቦርቅ ታይቶ ነበር።