ኢትዮ ሱዳን: የሁለቱን ሃገራት ድንበር ጉዳይን ለመፍታት ሶስተኛ ወገን አያስፈልግም ተባለ

አቶ ውሂብ ሙሉነህ በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ከድንበር ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ቴክኒካል አማካሪና በኢትዮጵያ ሱዳን ድንበር ኮሚሽን አባል

ኢትዮጵያ በሱዳን ድንበር ያለውን ውጥረት ለመፍታት የሶስተኛ አካል ጣልቃ ገብነትን እንደማትፈልግ አቶ ውሂብ ሙሉነህ በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ከድንበር ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ቴክኒካል አማካሪና በኢትዮጵያ ሱዳን ድንበር ኮሚሽን አባል ለቢቢሲ ገለፁ።

አቶ ውሂብ ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ያለውን የድንበር አለመግባባት ውዝግብ በውይይት ብቻ ለመፍታት ጥብቅ ፍላጎት እንዳላት ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ሱዳንም ብትሆን እስካሁን ድረስ በሁለትዮሽ ንግግር የሚል ሃሳብ ብቻ እንዳላቸው የሶስተኛ ወገን አደራዳሪነትን እንዲኖር አለማቅረባቸውን ተናግረዋል።

ሁለቱን አገራት ለማስታረቅና ለማሸማገል የተለያዩ አካላትም ጥረት እያደረጉ መሆናቸው የተነገረ ሲሆን ጉዳዩ ያሳሰባት የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ኢትዮጵያና ሱዳን ያላቸውን የድንበር ላይ ውዝግብ በሰላማዊ መንገድና በውይይት እንዲፈቱ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ በኩል ባወጣችው መግለጫ ጠይቃለች።

የሰሜን ጎንደር አስተዳዳሪና ነዋሪዎች የሱዳን ሠራዊት ወረራ ፈጽሞበታል ወደ ሚባሉት ስፍራዎች ዘልቆ መግባት የጀመረው በአካባቢው የነበረው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወደ ትግራይ ክልል መንቀሳቀስ ከጀመረ በኋላ በጥቅምት 29 2013 ዓ.ም እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

በድንበር አካባቢ ያለውን አለመግባባት በተመለከተ ጉዳዩ በሁለቱ አገራት መንግሥታት አማካይነት በሠላማዊ መንገድ እንደሚፈታና ለዚህም ጥረት እያደረገች እንደሆነ ኢትዮጵያ ስትገልጽ ብትቆይም ሱዳን ግን የያዘችውን መሬት ለቅቃ እንደማትወጣ ገልጻለች።

ኢትዯጵያ በበኩሏ ሱዳን በኃይል የያዘችውን መሬት ለቅቃ እስካልወጣች እንድትወጣ ቅድመ ሁኔታ ያስቀመጠች ሲሆን ይህ ተግባራዊ ካልሆነ ድርድር እንደማይኖር መግለጿ ይታወሳል።

የኢትዮጵያና ሱዳንን የድንበር ጉዳይ መፍታት የሚቻለው ሁለቱ ሀገሮች ባቋቋሟቸው መዋቅሮች ብቻ መሆኑን አቶ ውሂብ ገልፀዋል።

የድንበሩ ሁኔታ እስኪፈታ ድረስ ግን ኢትዮጵያና ሱዳን የፈረሟቸው ስምምነቶች ተከብረው መቆየት እንዳለባቸው አቶ ውሂብ አፅንኦት ይሰጣሉ።

"የኢትዮጵያን ሕልውና የሚጻረሩ ኃይሎች መኖራቸውን እናውቃለን" ያሉት አቶ ውሂብ " ሌላ ሶስተኛ አካል ሊኖር ይችላል" ሲሉ ተናግረዋል።

ከኢትዮጵያ በኩል ሶስተኛ አካል ሊኖር ይችላል የሚሉ ንግግሮች ቢሰሙም ሶስተኛ ወግን የተባለው እስካሁን በስም አልተጠቀሰም።

ሆኖም እነዚህን ኃይላት በመጋበዝ በዚህ የድንበር ውዝግብ ውስጥ ሚና እንዲኖራቸው ማድረግ ኢትዮጵያ እንደማትፈልግ አክለው ያስረዳሉ።

በተለያዩ ጊዜያት በሁለቱ ሀገራት መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት እኤአ 1972 የሀሳብ ልውውጥ ስምምነት ተፈራርመው ድንበራቸውን እንደገና ለማካለል መስማማታቸውን አቶ ውሂብ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

በስምምነቱ መሰረት ሁለቱ ሀገራት የሚቀበሉት የመፍትሔ ሀሳብ ላይ እስኪደርሱ ድረስ የድንበር ነባራዊ ሁኔታው ባለበት ተከብሮ እንዲቆይ መስማማታቸውን አመልክተዋል።

በ1972 ዓ.ም የተደረሰው ስምምነት በተባበሩት መንግሥታት የተመዘገበ መሆኑን በማንሳት፣ ይኸው ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆንና ጦርነት እንደማያስፈልግ ኢትዮጵያ ለሱዳን ማስረዳቷን ይገልጻሉ።

"የጦር ፍላጎት በኢትዮጵያ ዘንድ የለም" የሚሉት አቶ ውሂብ ሁለቱ ሕዝቦች በተለያየ ነገር እንደሚተሳሰሩ ተናግረዋል።

የትኛውም ጦርነት ሲያልቅ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ እንደሚመጣ በማስታወስ፣ ከጦርነት አማራጭ ይልቅ ልዩነቶችን በመነጋገር መፍትሔ መስጠት የተሻለ መሆኑን አክለዋል።

በአፄ ኀይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ኢትዮጵያ ከኬንያ ጋር ያላትን የድንበር ጉዳይ በጋራ መፍታቷን ያነሱት አቶ ውሂብ፣ የድንበሩን አለመግባባት ለመፍታት ሶስተኛ ወገን አስፈላጊ አይደለም ብለዋል።

የኢትዮጵያና የሱዳን ድንበርን የሚያሳይ ካርታ

በድንበሩ አካባቢ አሁንም አልፎ አልፎ ተኩስ እንደሚሰማ የገለፁት አቶ ውሂብ፣ ይህ ጉዳይ እንዲቆም ኢትዮጵያ መናገሯን ገልፀዋል።

አቶ ውሂብ ሁለቱ አገራት የሚያደርጉት ውይይት መች ሊቀጥል ይችላል ተብለው ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ሱዳን እና ኢትዮጵያ በድንበር ጉዳይ የሚያደርጉት ንግግር በማንኛውም ሰዓት ሊቀጥል ይችላል ብለዋል።

ኢትዮጵያና ሱዳን የጋራ ድንበር ኮሚሽን፣ የጋራ ድንበር ቴክኒክ ኮሚቴ እና የጋራ ልዩ ኮሚቴ አቋቁመው ለድንበሩ ጉዳይ መፍትሔ ለመስጠት ሲሰሩ መቆየታቸው ይታወሳል።

ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል "የሕግ ማስከበር ዘመቻ" ላይ በነበረችበት ወቅት የሱዳን መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ መጠየቋን የገለፁት አቶ ውሂብ፣ በዚህም በመስማማት ድንበራቸውን እንደሚዘጉ መናገራቸውን ይገልጻሉ።

ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር አልፋ እንድትጠብቅም ሆነ መሬት እንድትይዝ የተደረሰ ስምምነት እንደሌለ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከሰሞኑ ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው ።

"ድንበር አካባቢ የሁለቱን አገሮች ደህንነት የሚጎዳ እንቅስቃሴ እንዳይኖር በኛ አመራር ለሱዳን መንግሥት አደራ ተሰጥቷል" ያሉት ቃለ አቀባዩ አክለውም ሆኖም "ድንበሩን አልፈው አገራችን ግቡ መሬት ይዛችሁ ጠብቁልን የሚል አይነት ሊኖር የሚችል አይደለም፤ አልነበረም" ብለዋል።

ከሰሞኑ የሱዳን ምክር ቤት ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን ሱዳን ሰራዊቷን ወደ ድንበር ያስጠጋችው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ዐብይ አህመድ ጥያቄና ፈቃድ ነው መባሉ ተዘግቧል።

ድንበሩን የሚቆጣጣረው መካናይዝድ (የተቀናጀ) ጦር ወደ ትግራይ ሲሰማራ የሱዳን ጦር የኢትዮጵያን ድንበር በማለፍ ሰባት የወታደራዊ ካምፖችን በቁጥጥሩ ስር በማድረግ ወረራ መፈፀሙን አማካሪው ተናግረዋል።

በወቅቱም ሰብሎችን ማቃጠል እንዲሁም ዘረፋ መፈፀሙን አክለዋል።

ለዚህም ምላሽ የሰጡት ቃለ አቀባዩ "ቅዠት ነው" ካሉ በኋላም "አጥፊ ኃይሎች የናንተን ድንበር ተጠቅመው ወደኛ ድንበር እንዳይገቡ ማለት ኑና ገብታችሁ ጭራሽ ያልተከለለና መቶ አመት በዚሁ ሁኔታ ይሁን ተብሎ የቆየውን መሬት ድንበር የኛ ነው በሉ ማለትም አይደለም" ብለዋል።

ማንም አገር የድንበር አለመግባባት ሲገጥመው የጋራ ኮሚሽን በማቋቋም ጉዳዮን ለመፍታት እንደሚሰራ በመግለጽ፣ ይህ አለማቀፍ አሰራር በሁለቱ አገራት መካከልም ይቀጥል በማለት ለሱዳን ከፍተኛ ኃላፊዎች ጥያቄ መቅረቡን ተናግረዋል።

ከዓመታት በፊት ኢትዮጵያና ሱዳን ለረጅም ጊዜ ተቋርጦ የነበረውን 744 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን ድንበራቸውን ለይቶ ለማመላከት የሚያስችል ንግግርን መልሰው መጀመራቸው ይታወሳል።

በዚህ መፍትሄ ለመስጠት አስቸጋሪ የሆነው አካባቢ ፋሽጋ የሚባለው ነበር። በ1902 እና በ1907 (እአአ) የነበረው የቅኝ ግዛት ስምምነት መሰረት ዓለም አቀፉ ድንበር ወደ ምሥራቅ ይዘልቃል።

በዚህም ሳቢያ መሬቱ ወደ ሱዳን የሚካተት ይሆናል። ነገር ግን ቦታው ኢትዮጵያውያን የሚኖሩበት ሲሆን የግብርና ሥራ በማከናወንም የሚጠበቅባቸውን ግብር ለኢትዮጵያ መንግሥት ሲከፍሉ ቆይተዋል።