ዩኬ በጋዜጠኝነት ሽፋን ‘ለቻይና ሲሰልሉ’ ነበሩ ያለቻቸውን አባረረች

የፎቶው ባለመብት, Gettyimages
በጋዜጠኝነት ሽፋን ለቻይና ሲሰልሉ ነበር የተባሉ ሦስት ጋዜጠኞች ከወራት በፊት ከዩናይትድ ኪንግደም እንዲወጡ ተደርገው እንደነበረ ተገለጸ።
ጋዜጠኛ መስለው ለቻይና መንግሥት ሲሰልሉ ነበሩ የተባሉት ሰዎች ከዩኬ ተገደው እንዲወጡ መደረጋቸው ሳይሰማ የቀረው ግለሰቦቹ በጋዜጠኝነት ቪዛ ወደ ዩኬ በመግባታቸው ነው ተብሏል።
ግለሰቦቹ በጋዜጠኝነት ሽፋን ለቻይና ብሔራዊ ደህንነት ሚንስትር መረጃ ሲሰበስቡ ነበር ተብሏል። ግለሰቦቹ ጋዜጠኛ መስለው በየትኛው መገናኛ ብዙሃን ሲሰሩ እንደቆዩ ግልጽ አልሆነም።
የዩናይትድ ኪንግደም የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስቴር በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል። በለንደን የሚገኘው የቻይና ኤምባሲም በተመሳሳይ በጉዳዩ ላይ ምንም ሳይል አልፏል።
ይህ መረጃ የተሰማው የዩናይትድ ኪንግደም የመገናኛ ብዙሃን ተቆጣጣሪ ድርጅት የቻይናው ብሔራዊ ጣቢያ ሲጂቲኤን በዩኬ የነበረውን የሥራ ፍቃድ መሰረዙን ተከትሎ ነው።
የቻይና የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር የመገናኛ ብዙሃን ተቆጣጣሪ ድርጅቱን ውሳኔ አጥብቆ እንደሚቃወም አስታውቋል።
“ሴጣናዊ ተግባራት”
በተያያዘ ዜና የቢቢሲን ዘገባ ተከትሎ የአሜሪካ መንግሥት በቻይና የሙስሊሞች አያያዝ እጅጉን እንዳሳሰባት አስታውቃለች። ቢቢሲ በዘገባው የኡጉሩ ሙስሊም ሴቶች በማጎሪያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚደርስባቸውን ወሲባዊ ጥቃቶች አጋልጧል።
“እነዚህ ጥቃቶች አስደንጋጭ ናቸው። ጠንከር ያለ እርምጃ መወሰድ ይኖርበታል” ሲሉ የመንግሥት ቃል አቀባይ ተናግረዋል።
የዩኬ መንግሥት ሚንሰትር የሆኑት ኒጌል አደምስ የቢቢሲ ሪፖርት “ሴጣናዊ ተግባራት” መፈጸማቸውን አጋልጧል ሲሉ ለአገሪቱ ምክር ቤት አባላት ተናግረዋል።
በመላ ቻይና በሚገኙ ማጎሪያዎች ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኡጉሩ ሙስሊሞች እንደሚገኙ ይገመታል።
ቢቢሲ ትናንት ባቀረበው ዘገባ በማጎሪያ ጣቢያዎች ውስጥ በሚገኙ ሙስሊሞች ጾታዊ ጥቃቶች እና ስቃይ እንደሚደርስባቸው አጋልጧል።















