ምዕራባዊያኑ በትግራይ ጉዳይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ምን መከሩ?

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሰሞኑ ከአንዳንድ ምዕራባዊያን መሪዎች ጋር መምከራቸውን የሚዘክር ፅሑፍ በማሕበራዊ ድር አምባ ገፆቻቸው አስታውቀዋል።

ከእነዚህ መሪዎች መካከል የጀርመኗ መራሂተ-መንግሥት አንግላ ሜርክልና የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑዔል ማኽሮ ይጠቀሳሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ጠዋት ደግሞ ከአዲሱ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ጋር ውይይት ማድረጋቸውን አሳውቀዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ አዲሱ የጆ ባይደን አስተዳደር አባል የሆኑት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር መምከራቸውን ገልፀዋል።

ሚኒስትር ብሊንከን በትዊተር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት ከጠ/ሚ ዐቢይ ጋር መነጋገራቸውን አስታውቀው በትግራይ ክልል ያለውን ቀውስ እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል።

ጨምረውም በትግራይ ክልል ምንም ዕክል የሌለው የሰብዓዊ እርዳታ ፍሰት እንዲኖር ጥሩ አቅርበዋል።

'ነገር ግን ተግዳሮቶች ቢኖሩም ዩናይትድ ስቴትስ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ለውጥ እንዲቀጥልና ሰላማዊ ለውጥ እንዲኖር ድጋፍ እንደምታደርግ' ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን ለውጥ ለመደገፍ ላላቸው ቁርጠኝነት አመስግነዋል። አክለው በዩኤስ እና ኢትዮጵያ መካከል የሚኖር ጠንካራ ግንኙነት ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ግንባታ አስፈላጊ እንደሆነ አስምረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትዊተር ገፃቸው በፃፉት መልዕክት ትግራይ ክልል ስላለው ሁኔታ ምንም ያሉት ነገር የለም።

በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጀርመኗ መራሂተ መንግሥት ጋር ባደረጉት የስልክ ልውውጥ ስለሃገራዊና ቀጣናዊ ጉዳዮች እንዲሁም ስለ ኮቪድ-19 እና ምጣኔ ሃብታዊ ግንኙነቶች ማውራታቸውን በትዊተር ገፃቸው አሳውቀዋል።

በኢትዮጵያ የጀመርን ኤምባሲ የትዊተር ገፅ በበኩሉ መራሂተ-መንግሥት ሜርክል ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በነበራቸው ቆይታ ሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶቸና መገናኛ ብዙሃን በትግራይ ክልል በነፃ እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ ማቅረባቸውን አስታውቋል።

በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ጋር በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ስለማጠናከር እንዲሁም ሃገራዊና ቀጣናዊ ጉዳዮችን በተመለከተ መምከራቸውን አስታውቀዋል።

የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑዔል ማኽሮ ስለዚህ ጉዳይ በማሕበራዊ ድር አምባዎቻቸው ያሉት ነገር ባይኖርም የፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባወጣው መግለጫ ፈረንሳይ በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ እንዳሳሰባትና የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶች ፈቃድ እንዲሰጥ መጠየቋን አስታውቋል።

በሌላ በኩል በአስመራ የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ የኤርትራ መንግሥት ወታደሮቹን ከትግራይ ክልል በአስቸኳይ እንዲያስወጣ አሜሪካ ጥሪ አቅርባለች ብሏል።

ኤምባሲው በፌስቡክ ገፁ የአሶሺዬትድ ፕሬስ ዘገባን አጋርቷል። በዘገባው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ 'የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ክልል የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየፈፀሙ እንደሆነ የሚጠቁም መረጃ አሜሪካ እንዳላት' ተናግረዋል ብሏል።

የኤርትራ መንግሥት በትግራይ ክልል ስላለው ጦርነት ብዙም ያለው ነገር ባይኖርም ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ጦርነት አልተሳተፉም ሲል በተደጋጋሚ አስተባብሏል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው ያገለገሉ አምባሳደሮች በቅርቡ ትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ አሳስቦናል ብለው ግልፅ ደብዳቤ ፅፈው ነበር።

የኤርትራ መንግሥት ማስታወቂያ ሚኒስትር ለዚህ ግልፅ ደብዳቤ ምላሽ መስጠቱ አይዘነጋም።