ቻይናውያን ሙስሊሞች፡ ቻይና ልጆችን ከቤተሰቦቻቸው እየነጠለች ነው

ቻይና ሆነ ብላ ከሙስሊም ቤተሰብ የተገኙ ልጆችን ዢንጂያንግ በወደሚባለው ክልል በመውሰድ እምነታቸውን፣ ቋንቋቸውንና ባህላቸውን እንዲረሱ እንደምታደርግ በቅርቡ የተሠራ አንድ ጥናት ይፋ አደረገ።
ከዚህ በተጨማሪ ዕድሜያቸው ከፍ ያለ ቻይናዊ ሙስሊሞች በተለያዩ ትላልቅ ማቆያዎች እንዲሰበሰቡ እየተደረገ ሲሆን፤ ገዘፍ ያሉ አዳሪ ትምህርት ቤቶቸን የመገንባት ሥራውም በፍጥነት እየተከናወነ መሆኑ ተነግሯል።
ቢቢሲ የተለያዩ ይፋዊ መረጃዎችን በማሰባሰብና በአስርታት ለሚቆጠሩ የቤተሰብ አባላት ቃለ መጠይቅ አድርጎ ባገኘው መረጃ መሠረት በአንድ ከተማ ውስጥ ከ400 በላይ የሚሆኑ ሕፃናት አብዛኛዎቹ እናትና አባቶቻቸው በማረሚያ ቤት አልያም በማቆያ ማዕከላት ውስጥ የሚገኙ ናቸው።
ዢንጂያንግ ባለው ከፍተኛ የቁጥጥር ስራ ምክንያት የውጭ ሃገር ጋዜጠኞች በቀን 24 ሰአት ክትትል የሚደረግባቸው ሲሆን በአካባቢው የሰዎችን የምስክርነት ቃል መቀበል እጅግ ከባድ ነው። ነገር ግን ቱርክ ውስጥ ነዋሪነታቸውን ያደረጉና ታሪካቸውን ለማጋራት ፈቃደኛ የሆኑ ብዙ ቻይናውያን ይገኛሉ።
በቱርክ ዋና ከተማ ኢስታንቡል በስደት የሚገኙት አብዛናዎቹ ልጆቻቸውን ጨምሮ በርካታ የቤተሰብ አባላቶቻቸው የት እንደሚገኙ የማያውቁ ሲሆን የበፊት ምስሎቻቸው ብቻ እንደ ማስታወሻ እጃቸው ላይ እንደቀረ ይናገራሉ።
''ማን እንደሚንከባከባቸው አላውቅም'' ትላለች አንዲት እናት፤ ወደያዘችው የሶስት ሴት ልጆቿ ምስል እየጠቆመች፤ "በምንም ዓይነት ሁኔታ መገናኘት አንችልም።"
ቢቢሲ ቱርክ ውስጥ ባደገረው ከ60 በላይ ቃለመጠይቅ መሰረት ከ100 በላይ የሚሆኑ ሕፃናት ወደ ዢንጂያንግ ከተወሰዱ በኋላ የት እንደሚገኙ እንደማያውቁ ቤተሰቦች ገልጸዋል።
በዢንጂያንግ የሚገኙ በብዛት የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ከቱርክ ጋር የሃይማኖት፣ የባህልና የቋንቋ ቁርኝት አላቸው። ለዚህም ነው ለዘመድ ጥየቃ፣ ለትምህርት አልያም በቻይና ያለውን 'አንድ ልጅ' ፖሊሲ በመሸሽ ወደ ቱርክ የሚመጡት።
ባለፉት ሶስት ዓመታት ደግሞ ቻይና ከቱርክ ጋር ግንኙነት ያላቸውን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቿን በትልልቅ ማቆያ ማዕከላት ውስጥ ማጠራቀም ጀምራለች።

ማቆያ ማዕከላቱ የዢንጂያንግ ነዋሪዎች የክህሎት ትምህርት የሚያገኙባቸውና አክራሪ የሃይማኖት አስተሳሰብን ለመቀነስ ትምህርት የሚሰጥባቸው ቦታዎች ናቸው ይላሉ የቻይና ባለስልጣናት።
ነገር ግን አብዛኘዎቹ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በማዕከላቱ የሚገኙት ዜጎች ወደማዕከላቱ የሚወሰዱት እምነታቸውን በአደባባይ ስለገለጹ አልያም እንደ ቱርክ ባሉ የውጪ ሃገራት ካሉ ሰዎች ጋር ግንኙነት ስላላቸው ነው።
ባሳለፍነው የአውሮፓውያኑ 2017 ዓ.ም. በዢጂያንግ ማዕከላት የሚገኙ ህጻናት ቁጥር በግማሽ ሚሊየን የጨመረ ሲሆን 90% የሚሆኑት ደግሞ ኡግሁር ከሚባሉት እስልምና ሃእማኖት ተከታይ ማህበረሰቦችና ሌሎች የሃይማኖቱ ተከታዮች የተወጣጡ ናቸው።
በደቡባዊ ዢጂያንግ ብቻ በተሌያዩ ሕንጻዎች በዘመናዊ የደህንነት መሳሪያዎች ለማሟላትና የህጻናት ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት እስከ 1.2 ቢሊየን ዶላር ድረስ ፈሰስ ተደርጓል።
ባሳለፍነው ሚያዝያ ደግሞ የክልሉ ባለስልጣናት እስከ 2000 የሚደርሱ ሕፃናትን በዙሪያው ከሚገኙ መንደሮች ወደ ማዕከላቱ ያመጡ ሲሆን ሕፃናቱ በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ማወቅ እጅግ ከባድ ነው።












