ግብፅ እና ሳዑዲ አረቢያ ኢትዮጵያን ከቀይ ባሕር መድረክ ለምን አገለሏት?

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency
አገራት በየቀጠናው ለተለያየ ዓላማ ይቧደናሉ፡፡
አንዳንዴ ንግድን ለማሳለጥ፤ ሌላ ጊዜ ምጣኔ ሀብታቸው ለማፈርጠም፡፡
አንዳንዴ ሰላምና ደኅንነት ሲያሰጋቸው፣ ሌላ ጊዜ የጋራ ጠላት ሲያስበረግጋቸው፡፡
ኔቶ ራቅ አለ እንጂ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ ለነገሩ በዚህ ዘመን ሩቅ የሚባል ነገር አለ?
የሶቭየት ኅብረት የወረራ ፍርሃት የዛሬ 70 ዓመት የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት "ኔቶ"ን ወደለ፡፡
ሶቭየት ኅብረት የቅርጫ ያህል ፈራርሳ 15 አገራትን ወለደች፡፡
ኔቶ ግን ጸና እንጂ አልፈረሰም፡፡
እንዲያውም እየጎመራ መጣ፡፡ 12 አገራት መሥርተውት፣ አሁን 30 ደረሰ፡፡
አሁን ደግሞ በብቸኝነት ጭንቅ ውስጥ ካሉ አገራት በሚላክ የአስገቡን ማመልከቻ ተጨናንቋል፡፡
በአጭሩ ኔቶ፤ በ2ኛው የዓለም ጦርነት ተወልዶ በሦስተኛው የዓለም ጦርነት የስጋት ደጅ ላይ ቆሟል፡፡
ዓላማና ተግባራቸው፣ ሥሪትና ተልዕኳቸው ይለያይ እንጂ በምዕራባዊ አፍሪካ "ኢኮዋስ"፣ በአፍሪካ ቀንድ ደግሞ 'ንቁ አይደለም' የሚባለው ኢጋድ ይገኛሉ፡፡
ከሰሞኑ ብቅ ያለ ኅብረት መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ የቀይ ባሕር የትብብር መድረክ ይሰኛል፡፡ ኢትዮጵያን ያሰጋታል? ስለሱ እናውራ፡፡
የቀይ ባሕር የትብብር መድረክ የማን ነው?
የዚህ መድረክ መሥራች አባቶች ሁለት ናቸው፡፡ ግብፅና ሳዑዲ አረቢያ፡፡ ከእነርሱ ሌላ 6 አባል አገራት አሉ፡፡
ጎረቤት ኤርትራ፣ ጎረቤት ሱዳን፣ ጎረቤት ሶማሊያ፣ ጎረቤት ጂቡቲ፣ ዮርዳኖስ እና የመን፡፡
የባሕረ ሰላጤው አገራትና የአፍሪካ ቀንድ ተፈጥሮ አጎራብቷቸዋል፡፡ ከቀይ ባሕር ማዶ ለማዶ ይተያያሉ፡፡
እርግጥ ነው ይህ ቀጠና የማንንም ብልጹግ አገር ቀልብ ወከክ የሚያደርግ ነው፡፡ ለምን ከተባለ በዚህ አካባቢ ቅልጥ ያለ የንግድ እንቅስቃሴ ይካሄዳል፡፡
ዶላር በውሃ አካል የሚንሳፈፍበት ቦታ ነው፡፡
በዓለም ላይ ከባድ የባሕር ትራንስፖርት የትራፊክ መጨናነቅ አለበት የሚባል ቦታ ነው፤ ይሄ፡፡
እሲያን፣ መካከለኛው ምሥራቅና አውሮፓ ሄደው ሄደው፣ የሚገጥሙበት ቦታ ነው፡፡
በሜዲትራኒያን፣ ሱዩዝ ካናልን፣ ቀይ ባሕርን ዘልቆ ሕንድ ውቅያኖስ መድረስ የሚቻልበት ብቸኛ መስመር ነው፤ ይሄ፡፡
ታዲያ በዚህ ቁልፍ ቀጠና ኃያልነቱን ማሳየት የማይሻ ኃያል አገር ከየት ይኖራል?
ለዚህ አንድ ማሳያ ጂቡቲን ናሙና አድርገን እንውሰድ፡፡
የመዳፍ ያህል ከምትሰፋው ጂቡቲ ኩርማን መሬቷ ላይ እነማን ከትመዋል የሚለውን ማየት ብቻ ብዙ ይነግረናል፡፡
ፈረንሳይ፣ አሜሪካ፣ ጃፓን እና ቻይና አሉ፡፡ ሕንድና ሩሲያም መጣን እያሉ ነው፡፡
የኳታር፣ ቱርክ፣ ኢራን ተቧድኖም ቢሆን ለዚህ ቀጠና ያላቸው መቋመጥ አልቀዘቀዘም፡፡
ተፈጥሮ በቀይ ባሕር ሰፈር ያስቀመጠቻቸው አገራት ብቻ ሳይሆኑ ራቅ ያሉትም ቢሆን የንግድ መርከባቸው በዚህ ማለፉ ስለማይቀር የአካባቢው ሰላምና ፀጥታ ልክ እንደ ደጃቸው ያሳስባቸዋል፡፡
የቀይ ባሕር ደቡባዊ በር፣ ባብ- አል-ማንደብ፣ አንዳች እክል ቢገጥመው የብዙ አገሮች ጉሮሮ ላይ አጥንት የመሰንቀር ያህል ከባድ ነው፡፡
የሩቅ ኃያል አገራትን በአካባቢው የሚያሳዩትን የቅርምት ፍላጎትን በማገናዘብ ይመስላል የቀይ ባሕር ኩታ ገጠም አገራት ከፈረንጆቹ 2018 ጀምሮ በጋራ ለመቆም ማውጠንጠን የጀመሩት፡፡
ነገሩ ከላይ ከላዩ ሲታይ ከሩቅ የሚመጣን ጉልበተኛ አብሮ ለመመከት ያለመ ይመስላል፡፡
ምክክሩ እየጎለበተ መጥቶ አአአ 2019 ቅርጽ እየያዘ መጣ፡፡ በ2020 ደግሞ ተመሠረተ፡፡
ለጋራ ጥቅምም፣ ለጋራ ስጋትም ሰብሰብ ብንል ነው የሚሻለው በሚል ከሁለት ዓመት በፊት ጉባኤ ተቀመጠው የቀይ ባሕር የትብብር መድረክን ስምንቱ አገራት መሠረቱ፡፡
አቶ ነአምን አሸናፊ የአፍሪካና ኦሪየንታል ጥናት ዘርፍ ተመራማሪ ናቸው፡፡
እሳቸው ይህ መድረክ በሳዑዲና በግብፅ ጽኑ ፍላጎት እንጂ በአባል አገራት ሙሉ ፍቃድ የተመሠረተ እንዳልሆነ ይሰማቸዋል፡፡
ለዚህ የሚያነሱት አንዱ ምክንያት ቀሪ አባላቱ ያላቸው አሁናዊ ቁመና ነው፡፡
"ከግብፅ ውጪ አብዛኞቹ አገራት በራሳቸው ለመቆም የሚችሉ አይደሉም፤ ይልቅ ሳዑዲን የማጀብ ሚና ነው ያላቸው" ይላሉ፡፡
ይህን ሲሉ ምን ማለታቸው ነው? ቆየት ብለው ያስረዱናል? አሁን አንድ ጥያቄ እናንሳ፡፡
መድረኩ ኢትዮጵያን ለምን አገለለ ብለን እንጠይቅ፡፡ ይህ ጥያቄ የእኛ ብቻ ሳይሆን ተወካዮች ምክር ቤትም ያነሳው ጥያቄ ነው፡፡
የግብፅ ኢትዮጵያን የማግለል አሻጥር ይሆን?
በዚህ መድረክ ላይ ሁለት ቁልፍ አገሮች ገሸሽ ተደርገዋል፡፡ እንዲያውም ሦስት አገሮች፡፡ እስራኤል፣ ኢምሬትስና ኢትዮጵያ፤ ለምን?
ኢትዮጵያስ ለምን የበዛ ቅሬታ ገባት?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሳምንታት በፊት በተወካዮች ምክር ቤት በቀረቡ ጊዜ ዶ/ር ቶፊቅ አብዱላሒ ከተባሉ እንደራሴ ተያያዥ ጥያቄ ተነስቶላቸው ነበር፡፡
"ቀይ ባሕር ለእኛ ብቸኛው መግቢያ መውጫችን ነው፡፡ ሳዑዲ እና ግብፅ ሆን ብለው ሲያገሉን እኛስ ምን እያደረግን ነው?" የሚል ጥያቄ አንስተው ነበር፡፡
እንደራሴው ዶ/ር ቶፊቅ ጥያቄያቸውን ሲያጠናክሩ፣ ከስምንቱ አባል አገራት አራተቱ የኢጋድ አባላት ሆነው እንዴት ይህን አግላይነት ማስቆም አቃተን? ብለዋቸው ነበር ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥቅል የሆነ፣ የብልጽግና ተስፋን ያዘለ፣ በተረትና ምሳሌ የታጀለ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

"ወፏ የተሰበረ ቅርንጫፍ ላይ የምታርፈው ዛፉን ተማምና አይደለም፤ የምትበርበትን ክንፍ ተማምና ነው፡፡ ኢትዮጵያ ዛሬ ቀይ ባሕር ትላለች፤ አትጠራጠሩ ከ10፣ ከ15 ዓመት በኋላ በሌሎች ራቅ ባሉ አገሮችም ጥቅም አለኝ ትላለች፡፡ ድሃ ሆነን አንቀርም፤ መቶ ምናምን ሚሊዮን ሕዝቦች ነን፡፡ ኩሩ ሕዝብ ነን፡፡…የእኛ ተጽእኖ እዚች የቀይ ባሕር ሰፈር የሚቀር አይመስለኝም" ብለዋል፡፡
ምላሻቸው በተጨባጭ በዲፕሎማሲ ምን እየተሠራ እንደሆነ ምንም ፍንጭ የሚሰጥ አልሆነም፡፡
የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ካሉ ከቀናት በኋላ ኢትዮጵያ ከመድረኩ መገለሏ የፈጠረባትን ቅሬታ ገልጠዋል፡፡
አቶ ነአምን የኢትዮጵያን ገሸሽ መደረግ ከግብፅ ጋር ሊተሳሰር የሚችልበትን ሰበዝ መዘው ያወጣሉ፡፡
"ውስጡ ሲፈተሸ ጠንሳሾቹ እነማን ናቸው? ብሎ መጠየቅ ግማሽ ምላሽን ይሰጣል" የሚሉት የቀጠናው ተንታኝ፣ ከጠንሳሾቹ መሀል ግብፅ ዋንኛዋ ናት፡፡
ይህን ሐሳብ በ2018 ከነበረበት ያንቀሳቀሰችው ደግሞ ግብፅ ናት፡፡ ግብፅ በማንኛውም መድረክ ኢትዮጵያን ከዲፕሎማሲና ኢኮኖሚያዊ ከባቢ ማራቅ ነው የምትሻው" ይላሉ፡፡
ቀሪዎቹ ስድስት አባል አገራት ደካማ የሚባሉ ከመሆናቸው አንጻር ከሳዑዲ ጋር ትከሻ ለትከሻ መታከክ የምትችለው ግብፅ፣ በዚህ መድረክ ሚናዋ የጎላ እንደሚሆን አይጠረጠርም፡፡
"ከአባል አገሮቹ አንጻር ከሳዑዲ ቀጥሎ አጀንዳዋን ማስፈጸም የምትችለዋ ብቸኛ አገር ግብፅ ትሆናለች። ግብፅ ደግሞ ኢትዮጵያን የማግለል አጀንዳዋ የሚታወቅ ነው" ይላሉ አቶ ነአምን፡፡
ኢትዮጵያና ግብፅ የዓባይን ጉዳይ ተከትሎ በርካታ ተቃርኖ ውስጥ ያሉ ሆነው አንድ መድረክ ሊጋሩ የሚችሉበት ዕድል በሐሳብ ደረጃ ተነስቶ ከነበረም ልታከሽፈው የምትችለው ግብፅ አንጂ ሌላ አይሆንም፡፡
ዲና ሙፍቲ (አምባሳደር) ይህን ኢትዮጵያን የማግለሉን ነገር አገራቸው እንደማትቀበለው ገልጠዋል፡፡ እሳቸውም ቢሆን በዲፕሎማሲ ደረጃ ምን እየተሠራ እንደሆነ አልጠቀሱም፡፡
የሕዝብ እንደራሴው ዶ/ር ቶፊቅ እንዳነሱት ከአባል አገራት አራቱ የኢጋድ አባል ሆነው፤ ኢትዮጵያ በኢጋድ ውስጥ እጇ ረዥም ሆኖ በዚያ በኩል በር ለማንኳኳት እንዴት እንዳልተሞከረም ግልጽ አይደለም፡፡
"አረቦቹ ይህን የሚስቱት አይመስለኝም፤ ነገሩ የተጽእኖ ከባቢን የመፍጠርና የማስፋት ሙከራ ነው፡፡ ጥያቄው መሆን ያለበት ኢትዮጵያ ይህን ከበባ ለመቀልበስ ከወዲሁ ምን እያደረገች ነው የሚለው ነው" ይላሉ አቶ ነአምን፡፡
እንደሚፈራው ግብፅ ኢትዮጵያን ከቀጠናው ጂኦፖለቲክስ ተጽእኖ የማክሰምና የማኮስመን ጉዞ ጀምራ ከሆነ ይህ የቀይ ባሕር ፎረም የመግቢያ ሽንቁሯ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት አለ፡፡
መድረኩ ወደ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት የመለወጥ ዕድል አለው?
ስጋታችንን ከፍ እናድረገው፡፡ ኢትዮጵያ ቀስ በቀስ ቀለበት ውስጥ እየገባች ይሆን?
ዛሬ ሩሲያን ወደ ጦርነት ያስገባት አንድ ምክንያት በረዥም ዘመናት ውስጥ ቀስ በቀስ ከበባ ውስጥ መግባቷ ነው የሚሉ ተንታኞች ጥቂት አይደሉም፡፡
አነዚህ ተንታኞች የዩክሬን ወረራን የሚነቅፉትን ያህል ላለፉት በርካታ አሥርታት ኔቶ ሩሲያ አንገት ላይ ሸምቀቆ እያጠበቀ ቆይቷል ይላሉ፡፡
እርግጥ ነው ኔቶን ከቀይ ባሕር ምክክር መድረክ ጋር ማነጻጸር ስሜት አይሰጥም፡፡
በዓላማም፣ በተልዕኮም፣ በግብርም የሚያመሳስላቸው ነገር የለም፡፡
በዚያ ላይ የቀይ ባሕር መድረክ ገና ዳዴ እያለ ያለ ነው፡፡
በዚያ ላይ የመድረኩ ዓላማ ተብለው የተቀመጡት የባሕር ውንብድናን መከላከል፣ ከስፍራው የሚገኝ ጥቅምን ማጎልበትና መጋራት፣ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያንና የሰው ዝውውርን መቆጣጠር ናቸው፡፡
እርግጥ ነው እነዚህ ፍላጎቶች አንድ በአንድ እየተነሱ ቢታዩ ሁሉም የምዕራብ አገራት የጋራ ስጋቶች ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡
የባሕር ውንብድና ለአሜሪካና ምዕራብ አገራት ብቻም ሳይሆን ለምሥራቁም ስጋት ሆኖ የቆየ ነው፡፡
ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ተቀዳሚ የአውሮፓ ራስ ምታት ነው፡፡
በተጨማሪም፣ በዚህ አካባቢ ሰፋፊ የጋዝ ኃይል ማስተላለፊያዎች ግንባታን ጨምሮ ቻይና እፈጥረዋለሁ የምትለው ሰፊ የአውራ ጎዳና ቀለበት ወደፊት ቀጠናውን የላቀ የንግድ ትስስር የስበት ማዕከል ማድረጉ አይቀርም፡፡
ያ ጊዜ ሲመጣ የአካባቢው አገራት ከሩቅ በሚመጡ ቻይና፣ ሕንድና አሜሪካንን የመሰሉ ኃያላን የንግድ ብልጫቸው እንዲወሰድባቸው አይሹም፡፡
ይህም የትብብር መድረኩን ለመፍጠር ሌላ ምክንያት ሆኖ ይሆናል፡፡
ነገር ግን ሄዶ ሄዶ ይህ መድረክ ወደ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ቢያድግስ? ጊዜውን ያልጠበቀ ስጋት ነው?
አቶ ነአምን አሸናፊ እንደሚሉት ይህን መድረክ ለመፍጠር ከታለመ ዘመን የለውም፡፡
በሐሳብ ደረጃ ከኤርትራ ጀምሮ ግብፅና ሳዑዲ በተለያየ ጊዜና ሁኔታ ትልሙ ነበራቸው፡፡
"በሳዑዲ አጋፋሪነት በ2020 ተመሠረተ እንጂ ግብፅና ሳዑዲ ከ2018 ጀምሮ ሲነጋገሩበት የነበረ ጉዳይ ነው፡፡ ከ1970ዎቹ ጀምሮ ይብዛም ይነስ ሙከራዎች ነበሩ" ይላሉ፡፡
ይህ ማለት ግን ወደላቀ ኅብረት አያድግም ማለት ነው?
"ለምን ተመሠረተ የሚለውን ለመረዳት በቀጠናው ያለውን ካባቢያዊ ተጽእኖ ፈጣሪ የመሆን እሽቅድምምን መረዳት ይገባል" እንደ አቶ ነአምን፡፡
ይህም በዋናነት የሚገለጸው በተባበሩት አረብ ኢምሬትስና በሳዑዲ መካከል ያለ ውስጣዊ ትግል ነው፡፡
ይህ ሌላ ጥያቄን ያጭራል፡፡ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ከመድረኩ ለምን ተዘነጋች?
ለአቶ ነአምን ይህ ሌላ መሠረታዊ ነጥብ ነው፡፡
እንዴት የተባበሩት አረብ ኢምሬት በዚህ መድረክ ተዘነጋች፡፡
ተዘንግታ አይደለም፡፡
የገልፍ አገራት ኳታርን ያገለሉ ጊዜ ግብጽ፣ ሳዑዲና የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ናቸው የኳታርን መንግሥት የነጠሉት፤ የአየር ክልል በመዝጋት፣ ምጣኔ ሃብታዊ ተጽእኖ በመፍጠር፡፡
ይህ በጋራ የቆሙበት ጊዜ ነው፡፡ ይህን ኅብረታቸው ካጸኑ ብዙ አልቆዩም፡፡
ታዲያ ይህ የቀይ ባሕር መድረክ ሲቋቋም እንዴት ኢምሬቶች ሳይጋበዙ ቀሩ?
ኢምሬቶችን ካነሳን ሌላም ጥያቄ ማንሳት ይቻላል፡፡
የኢምሬቶች ሚና በቀጠናው ወደር የለውም፡፡
"ዲፒዎርልድ በጂቡቲ እና በሶማሊላንድ ወደቦችን የሚያስተዳድር እጅግ ግዙፍ ድርጅት ነው፡፡ ኢምሬቶች በሁሉም የቀጠናው አገራት ውስጥ ይነስም ይብዛ እዚያም እዚህም ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች አሏቸው፡፡"
ታዲያ በዚህ ቀጠና ውስጥ ኢምሬቶችን ያላካተተ መድረክ እንዴ ተመሠረተ?
"ለዚህም ነው እኮ የዚህ መድረክ ግብ፣ መሥራቾቹ እንደሚሉት የንግድ ትብብር ነው ብሎ ለማመን የሚያስቸግረው" ይላሉ አቶ ነአምን፡፡
"ከትብብር ይልቅ እሽቅድምድም ነው የሚታየኝ" የሚሉት የአካባቢው ተንታኝ ፤ ሳዑዲና ኢምሬቶች አካባቢውን በይበልጥ ለመቆጣጠር ሩጫ ላይ መሆናቸውን ያሰምሩበታል፡፡
"የንግድ ትብብር መድረክ ነው የሚሉት ለወጉ ያህል (face value) ነው፡፡ ነገሩ ትብብር ሳይሆን ፉክክር ነው፡፡ ፉክክሩም የነዳጅ ገንዘብ ያላቸው የሁለት አገራት ብቻ ነው፡፡"
ይህ ፉክክር እያየለ ከሄደ ምን ሊከሰት ይችላል? ኢምሬትስ ጉዳዩን በቸልታ ታየዋለች?
አቶ ነአምን እንደሚገምቱት የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ኢምሬቶችም ተገዳዳሪ ሆነው ይቀርባሉ፡፡
"ምናልባትም ሰፊ ሕዝብ ያላትን ኢትዮጵያን አካተው ሳዑዲን የሚገዳደር ሌላ ተፎካካሪ ኅብረት (Block) መፍጠራቸው የማይቀር ነው፡፡"
የቀይ ባሕር መድረክ ወዴት ሊያድግ ይችላል?
አቶ ነአምን ገና ከመነሻው የመድረኩ ጥንካሬና የዓላማ ግልጽነት ላይ ጥያቄ አላቸው፡፡
ለምሳሌ አስራኤል የለችበትም የሚሉት ባለሙያው፣ እስራኤል የቀይ ባሕር አካል ሆና፣ ኢትዮጵያ የአካባቢው ተጽእኖ ፈጣሪ ሆና ሁለቱ ቸል ሊባሉ የሚቸሉ አገራት አልነበሩም ይላሉ፡፡
"ዋና ተዋናዮቹን የቀጠናውን ተዋናዮች ያገለለ የትብብር መድረክ መሆኑ የሚነግረን አንድ ነገር ቢኖር የአንድን አገር ሕልም ለማስፈጸም የቆመ መሆኑን ነው" ይላሉ አቶ ነአምን፡፡
ወደ ጦር ቃል ኪዳን የማደግ ዕድል አለው ወይ? ተብለው ሲጠየቁ ነገሩ ሩቅ ይሆንባቸዋል፡፡
ያለ ምክንያት አይደለም ታዲያ፤ የአባል አገራቱን ስብጥርና ድኩማንነት በማሰላሰል እንጂ፡፡
"ሱዳን ቀውስ ላይ ናት፣ ኤርትራ ከዓለም የተገለለች ናት፣ ሶማሊያ እና የመን የት እንዳሉ ይታወቃል፣ ቀሪዎቹ ዮርዳኖስና ግብፅ ናቸው፤ እንኳንስ ሊጠናከሩ እርስ በርስ ቁርሾ ያለባቸው ናቸው፡፡ በአጭሩ ሳዑዲን ማጀብ ካልሆነ እነዚህ አገራት ሌላ ምን የረባ ሚና ሊኖራቸው ይችላል?" ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡
"ኔቶን የመሰሉ ድርጅቶች ሲመሠረቱ እኮ በግልጽ የተበየነ ዓላማና አንድ የጋራ ትልም ይዘው ነው፡፡ ይህ መድረክ ትልም ካለው የሳዑዲን ትልም ይዞ ነው የተነሳው፡፡"













