የአሜሪካው ልዩ ልዑክ በኢትዮጵያ ላይ ያደረባቸው ስጋት

የፎቶው ባለመብት, AFP/GETTY IMAGES
በትግራይ እየተፈፀሙ ያሉ ጭካኔዎች እንዲሁም የሰብዓዊ ሁኔታዎች ደረጃ ተቀባይነት እንደሌለው የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ጄፍሪ ፌልትማን አስታውቀዋል።
የአፍሪካ ቀንድ አገራትን ጨምሮ በሱዳንና ግብፅ ጉብኝት ያደረጉት ልዩ ልዑኩ በትግራይ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደረስና አሰቃቂ ብለው የጠሩት ግጭት እንዲቆም፤ የሚያስፈልገው አስቸኳይ ህይወት የማዳን ተግባር እንዲከናወን አገራቸው አሜሪካ ከተለያዩ አለም አቀፍ አጋሮች ጋር በመሆን ትሰራለች ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የፈፀሙ አካላትም ተጠያቂ የሚሆኑበትንም መንገድ አገራቸው እንደምትተባበር ገልፀዋል።
ልዩ ልዑኩ የአፍሪካ ቀንድ አገራትን ጨምሮ በግብፅና በሱዳን ከሚያዝያ 26፣ 2013 ዓ.ም ጀምሮ ያደረጉትን የመጀመሪያ ጉብኝት በትናንትናው ዕለት ግንቦት 5፣ 2013 ዓ.ም አጠናቀዋል።
የመጀመሪያ ጉብኝታቸው መጠናቀቁን ተከትሎ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በድረ ገፁ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ በትግራይ የተከሰተው ቀውስ በመላው አገሪቷ ትርጉም ያለው ለውጥ እንዳያመጡ የተደቀኑ ዘርፈ ችግርች ማሳያ ነው በማለትም ልዩ ልዑኩ መቃኘታቸውን አስፍሯል።
ሉዓላዊነቷ የተከበረና አንድነቷ የፀና ኢትዮጵያን ማየት የአሜሪካ ፍላጎት መሆኑን ጠቅሰው ነገር ግን በአገሪቷ ውስጥ ያለው ጫፍና ጫፍ የደረሰው የብሄር ፅንፈኝነትና ፖለቲካዊ ውጥረት ስጋት እንዳሳደረባቸው መናገራቸውን መግለጫው አስፍሯል።
በመግለጫው ልዩ ልዑኩ ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድና ሌሎች ባለስልጣናት ጋር መወያየታቸውን ገልፆ አገሪቷ የተደቀኑባት ችግሮች ሁሉንም ባማከለ መልኩ ሊፈታ እንደሚችል ጠቁሟል።
አገሪቷ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቶች ወደሚከበሩባት ብሄራዊ መግባባት መገንበት እንደሚቻል የጠቆመው መግለጫው ከዚህም ጋር ተያይዞ የኤርትራ ሰራዊት በኢትዮጵያ መቆየት ለነዚህ ግቦች መሳካት ተቃርኖ ነው ብሎታል።
ይህንንም አስመልክቶ ልዩ ልዑኩ ፌልትማን ከኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ጋር ባደረጉት ቆይታ የኤርትራ ሰራዊት በአስቸኳይ ከኢትዮጵያ መውጣት ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ጉዳይ መሆኑን መንገራቸውን መግለጫው አስምሯል።
አገራቸው አሜሪካ ትስስር ያላቸውን ቀጣናዊ ቀውሶችን በመፍታት ረገድ እንዲሁም የህዝቦች ድምፅ የሚሰማበትና መንግሥታት ለህዝባቸው ተጠያቂ የሚሆኑበት ስርዓት እንዲዘረጋና በአጠቃላይ የበለፀገችና የተረጋጋች የአፍሪካ ቀንድ እንዲፈጠር ድጋፍ እንደምታደርግ አስረድተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በሱዳን ላለው የሽግግር መንግሥት አሜሪካ አጋርነቷን እንደምታሳይ የጠቆመው ይህ መግለጫ በኢትዮጵያና በሱዳን ድንበር ያለው ግጭትና የህዳሴ ግድብ ውዝግብ ከአብዮቱ በኋላ የተፈጠረውን ሂደት እንዳያበላሸው ከአለም አቀፍ አጋሮች ጋር መፍትሄ ለመሻት እንሰራለን ብለዋል።
ልዩ ልዑኩ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ከሚወዛገቡት ሶስቱ አገራት ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን መሪዎች ጋር መክረዋል። ግብፅና ሱዳን ከሚያነሷቸው የግድቡ ደህንነትና አጠቃላይ አሰራር እንዲሁም ከውሃ ደህንነት ጋር ተያይዞ ያላቸውን ስጋትና ኢትዮጵያ ያላት የልማት ጥያቄ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር በሚደረገው ድርድር ይፈታል ብለዋል።
ተቋርጦ የነበረው የሶስትዮሽ ድርድሩም በአስቸኳይ እንዲጀመር ጥሪ አቅርበዋል።
በሶስቱ አገራት በአውሮፓውያኑ 2015 የተፈረመው የመርሆች መግለጫ ስምምነት እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት ባለፈው አመት ክረምት ላይ ያወጣው መግለጫ ለድርድሩ መስረት እንደሆነ የጠቆመው መግለጫው አሜሪካም ሽምግልናው ፍሬያማ እንዲሆን ፖለቲካዊም ሆነ ቴክኒካል ድጋፏን ትሰጣለች ብሏል።
ልዩ ልዑኩ የአሜሪካን ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከንን በመወከል የሚደረገውን ዲፕሎማሲያዊ ሂደት ለማሳለጥ ወደ ቀጠናው በቅርቡ እንደሚመለሱ ተመልክቷል።












