በአፍሪካ ሕብረት ለሚመራው ድርድር አሜሪካ ድጋፍ አደርጋለሁ አለች

ፌልትማን ከኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች ጋር

የፎቶው ባለመብት, FBC

የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ጄፈሪ ፌልትማን አገራቸው በአፍሪካ ሕብረት መሪነት ሦስቱ አገራት ለሚያደርጉት ድርድር አሜሪካ ድጋፏን ለማድረግ ቁርጠኛ ነኝ አሉ።

አምባሳደሩ ይህን ስለማለታቸው የተሰማው ዛሬ ከውሃ፣ ኢነርጂ እና መስኖ ሚንስትሩ ዶ/ር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ ጋር ከተወያዩ በኋላ ነው።

በቀጠናው በሚገኙ አገራት ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት አምባሳደር ፌልትማን ዛሬ ከኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ተደራዳሪ ቡድን አባላት ጋር ውይይት ማድረጋቸው ተዘግቦ ነበር።

ዶ/ር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ ከአምባሳደር ፌልትማን ጋር መወያየታቸውን በትዊተር ገጻቸው ላይ ገልጸው፤ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ደረጃን በተመለከተ እና በአፍሪካ ሕብረት ስለሚመራው የድርድር ሂደት ዙሪያ ግልጽ ውይይት ማድረጋቸውን አስፍረዋል።

አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን አገራቸው አድልዎ የሌለበት ድጋፍ እንደምታደርግ እና ሦስቱ አገራት በአፍሪካ ሕብረት መሪነት ሁሉን ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት እንዲደርሱ ቁርጠኛ መሆኗን መናገራቸውን ገልጸዋል።

የአባይ ወንዝ ለኢትዮጵያ እንዴት ጥቅም ላይ እንደሚውል እና ወደፊት በድርድሩ እንዴት ከስምምነት መድረስ እንደሚቻል ማብራሪያ መስጠታቸውን ገልጸዋል።

አምባሳደር ፌልትማን በተለያዩ በቀጠናው በሚገኙ አገራት ከሚያደርጉት ኦፌሴላዊ ጉብኝት በተጨማሪ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቢሮዎች፣ የአፍሪካ ህብረት የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም ከፖለቲካ አመራሮችና ከሰብአዊ እርዳታ ተቋማት ሃላፊዎች ጋር ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ልዩ መልዕክተኛው በአፍሪካ ሃገራት ጉብኝት እያደረጉ ያሉት ሃገራቸው በአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ፣ የጸጥታና ሰብአዊ ችግሮች በዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንዲፈቱ ያላትን ቁርጠኝነት ለማረጋገጥና በቀጠናው ያላትን የፖሊሲ ትብብር ለማጠናከር ነው ተብሏል።

አምባሳደር ፌልትማን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው በፕሬዝደንት ጆ ባይደን በቅርቡ መሾማቸው ይታወሳል።

ልዩ መልዕክተኛ አዲስ አበባ ከመግባታቸው በፊት በግብጽ፣ ሱዳን እና ኤርትራ ተገኝተው ከየአገራቱ መሪዎች ጋር መወያየታቸው አይዘነጋም።

አምባሳደር ፌልትማን ለሁለት ቀናት ሱዳን ከቆዩ ወደ አስመራ አቅንተው ከፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ረዘም ላለ ሰዓት መወያየታቸውን የኤርትራ ማስታወቂያ ሚንስትር የማነ ገብረመስቀል አስታውቀው ነበር።

አራት ሰዓት በቆየው ውይይት ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ በአፍሪካ ቀንድ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ኤርትራ ከአሜሪካ ጋር አብራ ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኗን ተናግረዋል ሲሉ የማስታወቂያ ሚንስትሩ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

አምባሳደሩ ከዚህ በተጨማሪ ወደ ግብጽ አምርተው ከፕሬዝደንት አብዱል ፈታህ አል-ሲሲ፣ ከውጪ ጉዳይ ሚንስትሩ ሳሚህ ሽኩሪ እና ከሃገሪቱ የውሃ ሚንስትር ጋር ስለመገናኘታቸው ተዘግቧል።

በውይይታቸው ወቅት አል-ሲሲ ግብጽ ከአባይ ውሃ የምታገኘው ድርሻ መቀነስን አትታገስም በማለት ስለመናገራቸው ዋሽግተን ፖስት ዘግቧል።

አምባሳደር ፌልትማን ከግብጽ ባለስልጣናት ጋር በነበራቸው ቆይታ የጆ ባይደን አስተዳደር በቀጠናው ላሉ አንገብጋቢ ጉዳዮች መፍትሄ ለመስጠት ትኩረት ያደርጋል ሰለማለታቸው ዋሽንግተን ፖስት ምንጮቹን ጠቅሶ ጨምሮ ዘግቧል።

ጄፍሪ ፌልትማን

የፎቶው ባለመብት, AFP/Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጄፍሪ ፌልትማን

ፌልትማን ማን ናቸው?

ጄፍሪ ፌልትማን በሹመታቸው ወቅት በተለይ በኢትዮጵያና በዙሪያዋ ስላሉ ሁኔታዎች የተለየ ትኩረት እንደሚሰጡ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ አስታውቆ ነበር።

ፌልትማን በድርድርና የሽምግልና ጉዳዮች ላይ ጥናትን በማካሄድና በአደራዳሪነትም ከፍ ያለ ልምድ እንዳላቸው ይነገራል።

ፌልትማን በፖለቲካዊና በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቀድሞውንና የአሁኑን ዋና ጸሐፊዎች ባን ኪሙን እና አንቶኒዮ ጉቱሬዝን ያማከሩ ሲሆን፤ ለጸጥታው ምክር ቤት በሠላምና በደኅንነት ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያዎችን በመስጠት ይታወቃሉ።

በተባበሩት መንግሥታት ቆይታቸው ወቅትም በልዩ መልዕክተኝነት አገልግለዋል፤ በተጨማሪም በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ውስጥ ለ26 ዓመታት ያገለገሉት ፌልትማን በሊባኖስ፣ በኢራቅ፣ በእስራኤል፣ በቱኒዚያ፣ በሃንጋሪና በሄይቲ ከፍተኛ ዲፕሎማት ሆነው አገልግለዋል።