ምርጫ 2013፡ የድምጽ መስጫ ቀን ላይ ለውጥ ሊኖር ይችላል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, NEBE/FB
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ በርቱካን ሚደቅሳ የ2013 አጠቃላይ ምርጫ የመራጮች ድምጽ መስጫ ቀን ላይ ለውጥ ሊደርግ እንደሚችል ተናገሩ።
የቦርዱ ሰብሳቢዋ የስድሰተኛው ሃገራዊ ምርጫ የድምጽ መስጫ ቀን "አስፈላጊ ከሆነ የተወሰኑ ቀናት ወደፊት ወደ ኋላ ሊል" ይችላል ሲሉ ተናግረዋል።
ሰብሳቢዋ ቦርዱ በጉዳዩ ላይ እስካሁን የወሰነው ምንም ዓይነት የቀን ለውጥ አለመኖሩን አረጋግጠው፤ በመራጮች ምዝገባ እና በድምጽ መስጫ ቀናት መካከል መከናወን ያለባቸው ተግባራት መኖራቸውን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ በአንድ ዓመት የተራዘመውን አጠቃላይ ምርጫ ግንቦት 28 እና ሰኔ 5 ለማድረግ አቅዳለች።
ባሳለፍነው ቅደሜ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት፤ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢዋ ብርቱካን ሚደቅሳ የሎጂስቲክ እና የደህንነት ጉዳዮችን እንደምክንያት በመጥቀስ፤ የድምጽ መስጫው ቀን "አስፈላጊ ከሆነ የተወሰኑ ቀናት ወደፊት ወደ ኋላ ሊል ይችላል ብዬ እገምታለሁ" ሲሉ ተናግረዋል።
ቦርዱ እስካሁን ድረስ ከ31 ሚሊዮን በላይ መራጮች መመዝገባቸውን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
የምርጫ ቁሳቁሶችን ማከፋፈል፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላ እና ስልጣና እንዲሁም የፓርቲዎች ግብዓት ማግኘት የሚሉት ተግባራት የመራጮች ምዝገባ ተጠናቆ እስከ ድምጽ መስጫ እለት የሚተገበሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።
"እነዚህን አይተን በሁለቱ መካከል ለማስገባት እንሠራለን። የሚያስፈልገው ነገር የሚወስደው ጊዜ ከታወቀ በኋላ አስፈላጊ ከሆነ የተወሰኑ ቀናት ወደፊት ወደ ኋላ ሊል ይችላል ብዬ እገምታለሁ" ብለዋል።
በአዲስ አበባ እና በሌሎች ህዝብ በብዛት የሰፈረባቸው ቦታዎች የምርጫ ጣቢያ አለመኖሩን ያረጋገጡት የቦርዱ ሰብሳቡቢ "ይህ የአሰራር ክፍተት ነው። ችግር በመሆኑ ኃላፊነትም የወሰድንበትም ጉዳይ ነው" ብለዋል።
የሕዝብ ቆጠራ አለመደረጉ እና ያለው መረጃ የቆየ መሆኑ የመራጮች ምዝገባ ግምት አስቸጋሪ ማድረጉን በምክንያትነት አስቀምጠዋል።
ችግሩን ለመቅረፍ እየተሠራ መሆኑን በመጠቆም "አዲስ አበባ ላይ ብዙ ቦታዎች ላይ በተለይም ኮንዶሚኒየም አካባቢዎች ላይ ከህዝብ ቁጥር አንጻር ያለመመጣጠን ነበር። በቀረው ጊዜ ብዙ ሰው እንመዘገባል ብለን እንገምታለን። የተሻለ ምዝገባ እንጠብቃልን" ብለዋል።
የመራጮች ምዝገባ የተራዘመባቸው ስፍራዎች
የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢዋ ብርቱካን፤ በደህንነት ስጋት የመራጮች ምዝገባ ዘግይቶ በነበረባቸው አካባቢዎች የመራጮች ምዝገባ መጀመራቸውን ተናግረዋል።
በኦሮሚያ በአራቱ የወላጋ ዞኖች፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ካማሺ እንዲሁም በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ምዝገባ መጀመሩን ተናግረዋል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ መተከል ዞን በተመለከተም "በመተከል ዙሪያ ቦርዱ በትኩረት እየተከታተለው ነው። የደህንነት እና የተፈናቃዮች ሁኔታን ከግምት በማስገባት ምዝገባ ለማስጀመር እያየነው እንገኛለን" በማለት እስካሁን መተከል ላይ የመራጮች ምዝገባ አለመጀመሩን ተናግረዋል።
በሰሜን ሸዋ ዞን አጣዬ 3 የምርጫ ክልሎችም አሁንም ምዝገባ አልመጀመሩን ጠቅሰው ከአባቢው የተፈናቀሉ ወደቦታቸው ስላልተመለሱ እና የደህንንነት ስጋት በመሆኑ ምዝገባ አለመጀመሩን አስረድተዋል።
በደቡብ ክልል ደግሞ የሱርማ ልዩ እና ዲዚ ልዩ እስካሁን ምዝገባ አለመጀመሩ እንዲሁም በሶማሌ ክልል የምርጫ ምዝገባ ግድፈት ተፈጸሞባቸዋል በተባሉ አካባቢዎች ቦርዱ ምዝገባውን መታገዱን አስታውቀዋል።
የአውሮፓ ሕብረት ታዛቢዎቸን አልክም ስለማለቱ
የአውሮፓ ሕብረት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር መግባባት በለመቻሉ የምርጫ ታዛቢዎቹን እንደማይልክ ባሳለፍነው ሳምንት ማስታወቁ ይታወሳል።
የአውሮፓ ሕብረት ታዛቢዎችን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ "የውጭ ታዛቢዎች ሁለት ደረጃዎች አሉት። የመጀመሪያው ከመንግሥት ጋር የሚያልቅ ነው። . . . በውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የሚጠናቀቅ ነው። [ሁለተኛው] በውጭ ጉዳይ ማረጋገጫ መሠረት ዕውቅና በመስጠት እናሰማራለን። አውሮፓ ህብረት ታዛቢዎችን ባለመላኩ ቦርዱ አዝኗል። ከእኛ በፊት ከመንግሥት ጋር ያለውን ግንኙነት ሳይጨርስ ነው ይህ ነገር የተፈጠረው። ቢመጡ እንደምንወድ ለሂደቱም የሚጨምረው ነገር እንዳለ አረጋግጠንላቸው ነበር። በእነሱም በኩል ተመሳሳይ ግምት እና እምነት ነበር። . . . ቢመጡ መልካም ነበር። ከዚህ ያለፈ ሃሳብ መስጠትል አልችልም" ብለዋል።
ኢትዮጵያ ምርጫ ለመታዘብ ካቀደው የአውሮፓ ሕብረት ጋር ያልተስማማቸው ሕብረቱ ሉዓላዊነትን የሚጻረር ጥያቄን በማቅረቡ ነው ሲሉ የውጪ ጉዳይ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ መናገራቸው ይታወሳል።
ሕብረቱ ኢትዮጵያ የሌላትን የኮሚኒኬሽን ስርዓት ወደ አገር ውስጥ ይዞ መግባትን እንደ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጡ እና የምርጫ ውጤትን ይፋ የማድረግ እኔ ነኝ ማለቱን ተከተሎ ከስምምነት መድረስ አለመቻሉን የውጪ ጉዳይ ቃል አቀባይ ተናግረዋል።












