የእስራኤልና ፍልስጥኤም ግጭት ከዬት ወደዬት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከሰሞኑ በእየሩሳሌም በተነሳው ግጭት በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጥኤማውያን ተጎድተዋል። 20 የሚሆኑ የእስራኤል ፖሊሶችም እንዲሁም በግጭቱ ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሏል።
ለወራት ያህል ተፋጠው የነበሩት እስራኤልና ፍልስጥኤም ለአስርት አመታት ያህልም በማያባራ ግጭት ውስጥ ናቸው።
እንዴት ተጀመረ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከመቶ አመት በላይ ያስቆጠረው ጉዳይ
ፍልስጥኤም ተብሎ የሚታወቀውን መካከለኛ ምስራቅ ይገዛ የነበረው የኦቶማን ኢምፓየር በአንደኛው አለም ጦርነት በብሪታንያ ተሸነፈ። ብሪታንያም ግዛቱን ተቆጣጠረች።
በቦታውም ይኖሩ የነበሩት በዋነኝነት አረቦች ሲሆን አነስ ያለ ቁጥር ያላቸው ይሁዳውያን ነበሩ።
በሁለቱ ህዘቦች መካከል ያለው ውጥረት መነሻም አለም አቀፉ ማህበረሰብ በተለያዩ አገር የነበሩ ይሁዳውያን ወደ ፍልስጥኤም እንዲመለሱ መሆኑ ነበር።
ይህንንም ስራ በበላይነት የምትሰራው ብሪታንያ ሆነች።
ይሁዳውያን መሬቱ የጥንት መኖሪያችን ብለው የሚያስቡ ሲሆን ለፍልስጥኤማውያንም እንዲሁ ግዛታችን የኛ ነው በሚል ውሳኔውን ተቃወሙ።
በአውሮፓውያኑ 1920-40ዎቹ ወደ ፍልስጥኤም የሚመጡ ይሁዳውያን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨመረ። አብዛኛዎቹ በሁለተኛው አለም ጦርነት አውሮፓ ውስጥ የነበረውን ጭፍጨፋን አምልጠው የተረፉ ናቸው።
በይሁዳውያንና በአረቦቹ መካከል የነበረው ፍጥጫ እንዲሁም የብሪታንያ ግዛት ተቃውሞ ታክሎበት ሁኔታዎች መጋጋል ጀመሩ።
በአውሮፓውያኑ 1947 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፍልስጥኤም ለሁለት እንድትከፈልና የይሁዳውያንና የአረብ ግዛቶች እንዲመሰረቱ እንዲሁም እየሩሳሌም አለም አቀፍ ከተማ እንድትሆን ውሳኔ አስተላለፈ።
ውሳኔው በአይሁድ መሪዎች መካከል ተቀባይነት ቢያገኝም በአረቦች መካከል ግን ውድቅ ተደረገ እንዲሁም ተግባራዊ አልሆነም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የእስራኤል መፈጠርና "ከፍተኛው ጥፋት"
ችግሩን መፍታት ያልቻሉት እንግሊዛውያን በአውሮፓውያኑ 1948 ለቀው ሲወጡ የአይሁድ አመራሮች የእስራኤል ሃገር ምስረታን አወጁ።
ሁኔታውን በርካታ ፍልስጥኤማውያን ተቃወሙት፤ ጦርነትም ተከተለ። የአካባቢው አረብ አገራት ወታደሮችም ተሳተፉበት።
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጥኤማውያን ከቤታቸው ተፈናቀሉ፤ የተወለዱበትን ቀዬ ለቀው ወጡ። ይህም ሁኔታ አል ናቅባ ወይም ከፍተኛ ጥፋት ተብሎ ይጠራል።
ጦርነቱ ቆሞ በአመቱ የተኩስ አቁም ስምምነት ሲፈረም እስራኤል በርካታ ግዛቶችን ተቆጣጠረች።
ዮርዳኖስ ዌስት ባንክ የሚባለውን ግዛት እንዲሁም ግብፅ ጋዛን ተቆጣጠሩ።
እየሩሳሌምም በምዕራብ በኩል በእስራኤል ኃይሎች ቁጥጥር ስትገባ በምስራቅ በኩል ደግሞ የዮርዳኖስ ኃይሎች ተቆጣጠሯት።
የሰላም ስምምነትም መደረስ ስላልተቻለ ሁሉም ወገኖች እርስ በርስ መወነጃጀላቸውን ቀጠሉ፤ በመጪዎቹ አስርት አመታትም በርካታ ጦርነቶች ተደረጉ።
በቀጣዩና በአውሮፓውያኖቹ 1967 በተደረገው ጦርነት እስራኤል ምስራቅ እየሩሳሌምን፣ ዌስት ባንክን እንዲሁም አብዛኛውን የሶሪያ የጎላን ሃይትን፣ ጋዛንና የግብፅን ሲናይ ፔኒንሱላን ተቆጣጠረች።
በርካታ የፍልስጥኤም ተፈናቃዮቻቸውና ልጆቻቸው በአሁኑ ወቅት በጋዛና በዌስት ባንክ እንዲሁም በጎረቤት አገራት ዮርዳኖስ፣ ሶሪያና ሊባኖስ ይኖራሉ።
ፍልስጥኤማውያን ተፈናቃዮችም ሆኑ ልጆቻቸው ወደ አገራቸውም ሆነ ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ እስራኤል አልፈቀደችላቸውም። እስራኤል እንደምትለው ፍልስጥኤማውያኑ ለእስራኤል አገር ሆና መመስረት አደጋ ደቅነዋል ትላቸዋለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እስራኤል አሁንም ቢሆን ዌስት ባንክን እንደያዘች የምትገኝ ሲሆን ከጋዛ ወጥቻለሁ ብትልም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በበኩሉ ግዛቱ በእስራኤል ቁጥጥር ስር ነው ይላል።
እስራኤል መላው እየሩሳሌም መዲናዬ ናት የምትል ሲሆን ፍልስጥኤማውያን በበኩላቸው ምስራቅ እየሩሳሌም የወደፊቷ ፍልስጥኤም መዲና ናት ይላሉ።
እስራኤል መላው እየሩሳሌም የኔ ናት የሚለውን የይገባኛል ጥያቄ እውቅና ከሰጡ ጥቂት አገራት መካከል አሜሪካ አንዷ ናት።
በባለፉት አምሳ አመታትም እስራኤል በነዚህ ቦታዎች ቤቶች የሰራች ሲሆን 600 ሺህ የሚሆኑ ይሁዳውያንም ይኖራሉ።
ፍልስጥኤማውያን የአለም አቀፍ ህጎችን በመጥቀስ የእስራኤል ድርጊት ህገወጥ ነው ለሰላሙም እንቅፋት ነው ቢሉም እስራኤል ይህንን ትክዳለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአሁኑ ወቅት ምን እየተከናወነ ነው?
በእስራኤልና በፍልስጥኤማውያን መካከል ከፍተኛ ውጥረት ያለ ሲሆን በተለይም በምስራቅ ኢየሩሳሌም፣ በጋዛና በዌስት ባንክ በሚኖሩት መካከል ደግሞ ሁኔታው የከፋ ነው።
ጋዛን እያስተዳደራት ያለው የፍልስጥኤማውያኑ ታጣቂ ቡድን ሃማስ ሲሆን ከእሰራኤል ጋር በርካታ ጊዜያት ተዋግቷል።
እስራኤልና ግብፅ በጋራ ለሃማስ የጦር መሳሪያ እንዳይደርስ በሚል የጋዛ ድንበርን ይቆጣጠራሉ።
እስራኤል በጋዛና ዌስት በምታደርገው ድርጊትና ክልከላዎች በርካታ ፍልስጥኤማውያን እየተሰቃዩ እንደሆነ ይናገራሉ።
እስራኤል በበኩሏ ይህንን የምትፈፅመው ራሷን ከፍልስጥኤማውያን ጥቃት ለመከላከል ነው ትላለች።
በቅርቡም የረመ ን ፆም መግባቱን ተከትሎ በፖሊስና በፍልስጥኤማውያን ያለው ግጭት ተባብሶ ነበር።
በተለይም በምስራቅ እየሩሳሌም የሚኖሩ ፍልስጥኤማውያን ከቤታችሁ እናስወጣችኋለን የሚለው ማስፈራሪያ በርካቶችን አስቆጥቷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዋነኛ ችግሮቹ ምንድን ናቸው?
እስራኤልና ፍልስጥኤማውያን የማይስሟሙባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ።
ከነዚህም መካከል የተፈናቃይ ፍልስጥኤማውያን እጣ ፈንታ፣ በእስራኤል ቁጥጥር ስር ያለው ዌስት ባንክ የሰፈሩት ይሁዳውያን እዚያው ይቆዩ ወይስ ወደሌላ ቦታ ይሂዱ እንዲሁም እየሩሳሌምን የመጋራት ጥያቄዎች ይገኙበታል። ከሁሉም በላይ ግን ፍልስጥኤም ከእስራኤል ጎን ለጎን ሃገር ሆና ትመስረት የሚለው ዋነኛ ጥያቄ ነው።
የሰላም ውይይት ጉዳዮች ለባለፉት 25 አመታት የተነሱ ሲሆን እስካሁን ግጭቶቹን መፍታት አልቻሉም።
የወደፊቱ ምንን ይዞ ይመጣ ይሆን?
በአጭሩ የእስራኤልና የፍልስጥኤም ሁኔታ ባጭሩ አይቋጭም።
በቅርቡ በተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተዘጋጅቶ የመጣውና በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ "የክፍለ ዘመኑ ስምምነት" የተባለው የሰላም እቅድ በፍልስጥኤማውያን ለአንድ ወገን ያደላ በሚል ውድቅ ተደርጓል።
ለወደፊቱም የሚመጡ የሰላም ስምምነቶች ሁለቱ አካላት የሚስማሙበትና ውስብስብ ችግሮችን የሚፈቱ መሆን አለባቸው።
እስከዚያ ድረስ ግጭቱ የሚቀጥል ይሆናል።












