"በደምቢ ዶሎ ከፍርድ ውጭ የተፈጸመው ግድያ አሳሳቢ ነው"- ኢሰመኮ

አማኑኤል ወንድሙ

የፎቶው ባለመብት, DEMBI DOLO CITY ADMINISTRATION COMMUNUCATION

በቄለም ወለጋ ዞን ደምቢ ዶሎ በወንጀል የተጠረጠረውን አማኑኤል ወንድሙ ከፍርድ ውጭ የተፈፀመበት ግድያ እንዳሳሰበው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገለጸ፡፡

ኮሚሽኑ ይህንን ያሳወቀው በዛሬው ዕለት ግንቦት 4፣ 2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ነው።

ማክሰኞ ዕለት በምዕራብ ኦሮሚያ ቄለም ወለጋ ዞን ደምቢ ዶሎ ከተማ አማኑኤል ወንድሙ የተባለ ተጠርጣሪ ወጣት በአደባባይ በመንግሥት ኃይል መገደሉን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የአካባቢ የመንግሥት ባለስልጣናትም የወጣቱን መገደል አረጋግጠው፤ ወጣቱ ለሕዝብ እንዲታይ ተደረገ እንጂ "በአደባባይ አልተገደለም" ሲሉ አስተባብለዋል።

የአካባቢው የመንግሥት ባለሥልጣናት ወጣት አማኑዔል 'የአባ ቶርቤ' ቡድን አባል በመሆኑ 'እርምጃ ተወስዶበታል' በማለት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ኮሚሽኑ በመግለጫው ምን አለ?

በቄለም ወለጋ ዞን ደምቢ ዶሎ በወንጀል ተጠርጥሯል የተባለው አማኑኤል ወንድሙ ከፍርድ ውጭ የተፈፀመበት ግድያና (extrajudicial killing) በአደባባይ ለህዝብ እንዲታይ የተደረገበት መንገድ እንዳሳሰበው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገልጿል፡፡

ኮሚሽኑ ማንኛውንም ከፍርድ ውጭ የሚካሄዱ ግድያዎችን የሚያወግዝ መሆኑን አስታውቆ ሁሉም የሕግ አስፈፃሚ አካላት ሕጋዊ መንገዶች ብቻ አንዲተገብሩ መልዕክቱን አስተላለፏል፡፡

"ከፍርድ ውጭ የሚካሄዱ ግድያዎች ህዝቦች በሕግ የበላይነት ላይ ዕምነት እንዲያጡ እና በዚህ ረገድ የተገኙ ስኬቶች እንዲቀለበሱ ያደርጋሉ ብሏል፡፡

ባለሥልጣናት ጉዳዩን በአፋጣኝ እንዲመረምሩ እና ተገቢ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ኮሚሽኑ ጠይቋል።

ኮሚሽኑ ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተለ ስለ ውጤቱን ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

የአካባቢው የመንግሥት ባለሥልጣናት ወጣት አማኑዔል 'የአባ ቶርቤ' ቡድን አባል በመሆኑ 'እርምጃ ተወስዶበታል' በማለት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የደምቢ ዶሎ ከተማ ኮሚዩኒኬሽን ጽ/ቤት በበኩሉ ሰዎችን ሲገድል በነበረው እና 'የአባ ቶርቤ' ቡድን አባል በሆነው ግለሰብ ላይ እርምጃ ተወሰደ ሲል በፌስቡክ ገጹ ላይ ጽፏል።

የከተማው ጽ/ቤት በፌስቡክ ገጹ ላይም ወጣቱ ከመገደሉ በፊት የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል አትሟል።

በአካባቢው በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው የ"ሸኔ" ቡድን እንደሚንቀሳቀስ ይነገራል።

በምዕራብ ኦሮሚያ በተለያዩ አካባቢዎች ቡድኑ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት በማድረስ በተደጋጋሚ ይወነጅላል።

በቪዲዮው ላይ ምን ይታያል?

በዚህ የፌስቡክ ገጽ ላይ ወጣቱ ከመገደሉ በፊት ለቀረቡለት ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጥ ይታያል። ቪዲዮን እየቀረጸ የሚገኘው ሰው የወጣቱን ስም እና የትውልድ ስፍራውን ይጠይቀዋል።

እጁ ወደ ኋላ የታሰረው ወጣት አንገቱ ላይ ሽጉጥ ተንጠልጥሎ ይታያል። በወጣቱ እግር ላይ እና በዙሪያው ደም የሚታይ ሲሆን ልብሱም በጭቃ ተለውሷል።

አደባባይ ፊትለፊት የቆመው ወጣት ስሙ አማኑኤል ወንድሙ ከበደ እንደሚባል እና ትውልዱ ደምቢ ዶሎ ከተማ 07 ተብሎ በሚጠራ ስፍራ እንደሆነ ይናገራል።

በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ የደንብ ልብስ በለበሱ የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎ ተከቦ ይታያል።

ወጣቱ ለምን ተገደለ?

የከተማው ኮሚውኒኬሽን ጽ/ቤት እንደሚለው ከሆነ ይህ ወጣት የመንግሥት ባለስልጣናት በመግደል የሚታወቀው "አባ ቶርቤ' የተሰኘው ህቡዕ ቡድን አባል ነበር።

ወጣቱ ትናንት በቁጥጥር ሥር ከመዋሉ በፊትም ንጋት ላይ ገመቹ መንገሻ የተባለ ግለሰብ በጥይት መትቶ ለማምለጥ ሲሞክር "በጸጥታ ኃይሎች ጠንካራ ትስስር እግሩን ተመትቶ ተይዟል" ብሏል።

ከዚህ በተጨማሪም ከቀናት በፊት በደምቢዶሎ ከተማ የኦሮሚያ ብሮድካስቲን ኔትዎርክ ጋዜጠኛ የነበረውን ሲሳይ ፊዳ የገደለው የአባ ቶርቤ ቡድን ነው ሲል አክሏል።