በሕወሓትና 'ሸኔ' ላይ አቃቤ ሕግ አደረግኩት ያለው ምርመራ ምን ያሳያል?

ጠቅላይ አቃቤ ህግ

የፎቶው ባለመብት, Attoreny General

ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በቅርቡ ሽብርተኛ ተብለው የተፈረጁትን ህወሓት እና ሸኔ በተመለከተ ትናንት መግለጫ ሰጥቷል።

በዚህ ሰፋ ባለ መግለጫው ባለፉት ሶስት ዓመታት ሰላማዊ ዜጎች ላይ ባነጣጠሩ ጥቃቶች የበርካታ ዜጎች ሕይወት መጥፋቱን፣ መፈናቀላቸውን እንዲሁም ንብረት መውደሙን ጠቅሶ እነኚህ ጥቃቶች ህብረተሰቡ በነጻነት እንዳይኖር እንዲሁም ዜጎች እርስ በእርስ እንዳይተማመኑ በማድረግ የመንግስትን ህልውና አደጋ ላይ ለመጣል ታቅደው ሲፈፀሙ የነበሩ መሆኑን ከተለያዩ ማስረጃዎች ለመረዳት ተችሏል ብሏል።

ጥቃቶቹ በተለያዩ ቡድኖች የተፈፀሙ ቢሆንም ከጀርባቸው ግን በዕቅድ፣ በገንዘብ፣ በሀሳብ እንዲሁም የሚድያ ሽፋን በመስጠት የመሪነት ሚናውን ሲጫወቱ የነበሩ ቡድኖች አሉ ብሏል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በመግለጫው።

መሥሪያ ቤቱ አክሎ የውጭ ኃይሎች እነዚህን ቡድኖች ተጠቅመው ኢትዮጵያን የማመሰቃቀልና የማፍረስ ፍላጎታቸውን እያሰረፁ እንደሆነ ማሳያዎች አሉ ይላል።

ጠቅላይ አቃቤ እነዚህ ድርጊቶች የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 3 ስር ስለሽብር የወንጀል ድርጊት የተሰጠውን ትርጓሜ ሙሉ ለሙሉ የሚያሟሉ ናቸው ይላል በመግለጫው።

መሥሪያ ቤቱ አክሎ ድርጊቱን የፈፀሙትን በተናጠል ተጠያቂ ከማድረግ ይልቅ ድርጅቶቹን በሽብርተኝነት በመሰየም በህጉ በተቀመጠው አግባብ የሽብር ወንጀል ድርጊትን በተሻለ ሁኔታ ለመቆጣጠር እና ለመከላከል ይቻላል ይላል።

ሕወሓት በለውጥ ምክንያት ከሥልጣን ከተነሳ በኋላ 'ጥቅማቸው የተነካባቸው ከፍተኛ አመራሮች ለውጡ ያመጣውን መንግሥት በማንኛውም መንገድ ከሥልጣን ለማስወገድ' መንቀሳቀሳቸውን መግለጫው አትቷል።

በዚህም መሠረት ሕወሓት 2011 ዓ.ም የ “ትግራይ ማዕከላዊ ወታደራዊ ኮማንድ” በማለት ሕገወጥ የታጠቀ ሃይል እንዲደራጅ በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ወስኗል ይላል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ።

ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በመግለጫው ሕወሓት በጡረታ በተገለሉ ጄኔራሎች እና ኮሎኔሎች እገዛ የትግራይ መከላከያ ሃይል የተባለ ወታደራዊ ሃይል እንደገነባ ያትታል።

መግለጫው አክሎ 'ይህ ኃይል ከፍተኛ ወታደራዊ ሥልጠና በመስጠት ለጦርነት ሲዘጋጅና ሲደራጅ ነበር' ይላል።

ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ሕወሓት ኅይሉን በተለያዩ መዋቅሮች አደራጅቶ እንደነበርና ደረጃ 1 ሚሊሻ የሚባለው ሰራዊት እድሜያቸው 40 ዓመት ያልበለጡ፣ ሙሉ ጤነኛ የሆኑ እና ጦርነት ላይ ለመሳተፍ የሚችሉ አባላትን የያዘ እንደሆነ ይገልፃል።

የተደራጀዉ ወታደራዊ ሃይል በማንኛዉም ሁኔታ የክልል መንግስታት ሊታጠቁ የማይገባውን መካናይዝድ እና የቡድን መሳሪያ ስልጠና በመስጠት ለጦርነት ዝግጅት ሲያደርግ እንደነበርና ይህ ዝግጅት ለሕወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እያቀረበ ይገመገም እንደነበር ከወንጀል ምርመራው ሂደት ማረጋገጥ ተችሏል ይላል መግለጫው።

ሕወሓት የፌዴራል መንግስትን ለመጣል ከነበረው ጽኑ ምኞት በመነሳት ከወታደራዊ ሃይል ዝግጅቱ ጎን ለጎን ህዝቡ ለጦርነት እንዲዘጋጅ ያደርግ እንደነበርና በክልሉ ይገኝ የነበረው የሃገር መከላከያ ሰራዊት በሚፈለገው ልክ መንቀሳቀስ እንዳይችል በየቦታዉ ኬላዎችን በማቋቋም የሃገር መከላከያ ሰራዊት ፍተሻ እንዲካሄድበት አድርጓል ይላል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ።

አሁን በሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀው ሕወሓት ለዓላማው ማስፈፀሚያ ይሆነው ዘንድ የአፋር አብዮታዊ ዲሞክራሲ አንድነት ግንባር (አርዱፍ) ለተባለ ፓርቲ የበጀትና የጦር መሳርያ ድጋፍ ሲያደርግ ነበር ይላል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በዝርዝር ባወጣው መግለጫ።

መሥሪያ ቤቱ፤ ሕወሓት የአማራ ክልልን ሰላም ለማደፍረስም ከተለያዩ አካላት ጋር ስምምነት አድርጎ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቆይቷል ሲልም ይወቅሳል።

በዚህም መሠረት የቅማንት ህዝብን ደህንነት ለመጠበቅ በሚል ከፍተኛ ገንዘብ እና የጦር መሳርያ በመመደብ በአካባቢዉ ላይ የሚነሳ ግጭትን በመሳርያ እና ገንዘብ ሲደግፍ እንዲሁም በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን አካባቢ የሚኖር ህዝብ ከአፋር ህዝብ ጋር እንዲጋጭ ግጭት ለማባባስ አስቦ ከ100 በላይ ክላሽንኮቭ መሳርያ ለማስታጠቅ ሙከራ አድርጎ በፀጥታ ሃይሎች ክትትል ውጥኑ ሳይሳካለት ቀርቷል ይላል አቃቤ ሕግ።

ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ በጋምቤላ እና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዉስጥ ህዝባዊ ግጭት እንዲነሳ በማሰብ በክልሎቹ ለሚንቀሳቀሱ ሁለት ድርጅቶ መሳርያ እና ገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ግጭት ለመቀስቀስ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል ሲል መግለጫው ያብራራል።

የአቃቤ ሕግ መግለጫ አክሎ በኦሮሚያ ክልል ከሚንቀሳቀሰዉ በተለምዶ “ሸኔ” ተብሎ የሚጠራው ቡድን ጋር ዉይይት በማደርግ ቡድኑን በገንዘብ እና በመሳርያ በመርዳት የቡድኑን ታጣቂዎች በክልሉ ዉስጥ የሰዉ ህይወት እንዲያጠፉ፣ ንብረት ላይ ጉዳት እንዲያደርሱ እና ዜጎች እንዲፈናቀሉ አድርጓል ይላል።

መግለጫው አክሎ ወደ ሰላማዊ ትግል እንዲገባ ጥሪ ተደርጎለት ፈቃደኛ ያልሆነው በተምዶ "ሸኔ" ተብሎ የሚጠራው ቡድን በኦሮሚያ የተለያዩ ዞኖች እና ወረዳዎች ዉስጥ እንዲሁም ከክልሉ ውጪ በመንቀሳቀስ ሰላማዊ ህብረተሰብን በመግደል እና ከቤት ንብረት በማፈናቀል የሽብር ወንጀል ፈፅሟል ይላል።

የአቃቤ ሕግ መግለጫ እንደሚለው ቡድኑ በፈፀመው የሽብር ተግባር በ2013 ዓ.ም ብቻ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ 463 ሰዎች ላይ አደጋ ደርሷል፡፡ 112 የፖሊስ አባላት፣ 57 ሚሊሻ አባላት እና 18 በተለያየ ደረጃ ላይ ያሉ አመራሮች ህይወት አልፏል፤ 160 መኖርያ ቤቶች 44 ተሽከርካሪዎች እና 84 የመንግስት መስርያ ቤቶች ተቃጥለዋል፡፡

መለግጫው በተጨማሪ ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም በምዕራብ ወለጋ ጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ቃንካ ቀበሌ ንፁሃን ዜጎች ላይ በፈጸመው ጥቃት 36 ንፁሃን ዜጎችን በመግደል እና በርካታ ቤቶች በማቃጠል ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ሰዉ ከአካባቢዉ እንዲፈናቀል አድርጓል ብሏል።

በዚህም መሠረት ሁለቱ ድርጅቶች ማለትም ሕወሓትና በተለምዶ ሸኔ ተብሎ የሚጠራው ቡድን በሕዝብ እንራሴዎች ምክር ቤት አሸባሪ ተብለው እንዲጠሩ መወሰኑን ያወሳል።