የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት "ህወሓት" እና "ሸኔ"ን በሽብርተኝነት ፈረጀ

ምክር ቤት

የፎቶው ባለመብት, HPR

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት "ህወሓት" እና "ሸኔ" በሽብርተኝነት እንዲፈረጁ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ አፀደቀ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት "ህወሓት" እና "ሸኔ" በሽብርተኝነት እንዲፈረጁ የቀረበለትን ሀሳብ በአንድ ድምፀ ተዐቅቦ አጽድቋል።

5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 13ኛ መደበኛ ስብሰባ በመካሄድ ላይ ነው፡፡

ባሳላፍነው ሳምንት የሚንስትሮች ምክር ቤት ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ እና ሸኔ በሽብርተኝነት እንዲፈረጁ የውሳኔ ሃሳብ አስተላልፎ እንደነበረ ይታወሳል።

ዛሬ ስብሰባውን እያደረገ የሚገኘው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለቱ ቡድኖች በሽብርተኝነት እንዲፈረጁ የቀረበለትን የውሳኔ ሀሳብ በሙሉ ድምፅ ማጽደቁን ምክር ቤቱ በፌስቡክ ገፁ ላይ አስታውቋል።

line

በአሸባሪነት የተፈረጁት 'ሸኔ' እና ህወሓት ማን ናቸው?

ሸኔ

የሚንስትሮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ እንዲፈረጅ ሃሳብ ያቀረበው "ሸኔ" ቡድንን ነው።

በአሁኑ ወቅት በተለይ በምዕራብ ኦሮሚያ በስፋት ስለሚንቀሳቀሰው እና የመንግሥት ባለስልጣናት፤ 'ኦነግ ሸኔ' ብለው ስለሚጠሩት ታጣቂ ቡድን የሚታወቀው የሚከተለውን ነው።

መንግሥት በተለይ የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት 'ኦነግ ሸኔ' በሚል የሚጠሩት ታጣቂ ኃይል ራሱን "የኦሮሞ ነጻነት ጦር" በማለት ይጠራል።

'የኦሮሞ ነጻነት ጦር' ለበርካታ አስርት ዓመታት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ፓርቲ የጦር ክንፍ ሆኖ ቆይቷል።

የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህምድ ወደ ስልጣን መምጣትን ተከትሎ የኦነግ አመራሮች ወደ አገር ከገቡ በኋላ የኦሮሞ ነጻነት ጦር (መንግሥት ኦነግ ሸኔ የሚለው ቡድን) ከፓርቲው ተገንጥሎ በትጥቅ ትግሉ እንደሚቀጥል ይፋ አደረገ።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሊቀ-መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ የኦሮሞ ነጻነት ጦር (ኦነግ ሸኔ) በእርሳቸው እንደማይታዘዝ ይፋ አድርገው ነበር።

ስለ 'ሸኔ' መንግሥት የሰጠው ማብራሪያ

ከውሳኔው በኋላ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ጌድዮን ጢሞቲዮስ [ፒኤችዲ] ሸኔ ስለተሰኘው ስያሜ ለመገናኛ ብዙሃን ማብራሪያ ሰጥተዋል።

"በተለምዶ 'ሸኔ' የሚባለው እራሱን ደግሞ 'የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት' ብሎ የሚጠራው ቡድን ነው። በምዕራብ ኦሮሚያ ፣ በሌሎችም ክልሎች እየተንቀሳቀሰ ጥቃት የሚያደርስ ድርጅት ነው። እራሱ ለእራሱ የሰጠውን ስያሜ ግን እኛ የምናፀድቅበት ምክንያት የለንም ፤ ተገቢም አይሆንም ብለን እናምናለን" ብለዋል አቃቤ ሕጉ።

ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ አክለው ይህ ቡድን ከዚህ በፊት እንደ 'ህወሓት' ተመዝግቦ ፣ ህጋዊ እውቅና ፣ ህጋዊ ሰውነት እና ሰርተፊኬት ኖሮት የሚያውቅ አይደለም። እሱ እራሱን በአንድ ስያሜ ይሰይማል ፤ አንዳንዶች በሌላ ስም ይጠሩታል በተለምዶ 'ኦነግ ሸኔ' ይባል ነበር ስለዚህ በተለምዶ ከሚጠራበት 'ኦነግ ሸኔ' ወይም 'ሸኔ' ከሚባለው 'ሸኔ' የሚለውን መርጠናል" ብለዋል።

"እዚህ ጋር ግልፅ መሆን ያለበት በአዋጁ አንቀፅ 23 መሰረት ስያሜውን ብትለዋውጥ ያው ቡድን ያው ስብስብ እስከሆነ ድረስ በውሳኔ ሀሳቡ የተገለፀው ስብስብ እስከሆነ ድረስ ስያሜ መለዋወጥ የሚያመጣው ለውጥ የለም፤ ውሳኔ ሀሳቡ ተፈፃሚ ይሆንበታል። አይ እኔ እራሴን የምጠራው እንዲህ ብዬ ነው ፤ እንዲያ ብዬ ነው የሚለው ማምለጫ ሊሆን አይችልም" ሲሉም አብራርተዋል።

ጠቅላይ አቃቤ አክለው "ሕጉ ኦነግ የሚባል በምርጫ ቦርድ የተመዘገበ ሕጋዊ ሰውነት ያለው ድርጀት አለ። ስለዚህ ከሱ ጋር ማምታታት ሊፈጥር ይችላል። ሸኜ የሚለው ብዙ ሰውም ስለሚያውቀው በዚያ እንዲሰየም ተደርጓል" ብለዋል.

ሸኔ የሚለው መጠሪያ ከየት መጣ?

ሸኔ- ማለት 'ሸን' ከሚለው የኦሮምኛ ቃል የመጣ ነው። 'ሸን' ማለት አምስት ማለት ነው። 'ሸኔ' ማለት ደግሞ አምስቱ እንደማለት ነው።

በኦሮሞ ነጻነት ግንባር ፓርቲ አደረጃጀት ውስጥ አምስት አባላት ያሉት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ 'ጉሚ ሸኔ' ተብሎ ይጠራል። ጉሚ ሸኔ ማለት 'አምስት አባላት ያሉት ጉባኤ' እንደማለት ነው። ፓርቲው ግን ከ5 በላይ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አባላት ሊኖረው ይችላል።

ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው ቡድን መሪ እንደሆነ የሚታመነው ኩምሳ ድሪባ በትግል ስሙ በስፋት የሚታወቀው ጃል [ጓድ] መሮ፤ ለኦሮሞ ነጻነት እንታገላለን ይላል።

በተለያዩ ወቅቶች መንግሥት በዚህ ቡድን ላይ በሳምንታት ውስጥ 'እርምጃ' እወስዳለሁ ቢልም፤ በቡድኑ አባላት ተፈጽመዋል በሚባሉ ጥቃቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ተገድለዋል በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ተፈናቅለዋል።

መንግሥት ኦነግ ሸኔ ብሎ የሚጠራው ቡድን በርካታ የመንግሥት ባለስልጣናት እና የፖሊስ አባላት ላይ ግድያ እና የባንክ ዝርፊያ መፈጸሙን ይገልጻል።

መንግሥት ከዚህ ቀደም ይህ ቡድን በህወሓት ድጋፍ እንደሚደረግለት እና በትግራዩ ግጭትም ለህወሓት ወግነው ሲዋጉ ነበሩ ያላቸውን 'የኦነግ ሸኔ' ታጣቂዎችን መማረኩን አስታውቆ ነበር።

ኦነግ-ሸኔ የሕዝብ 'ጠላት ነው'

የቦረና አባ ገዳ የሆኑት ኩራ ጃርሶ ኦነግ-ሸኔን የሕዝብ ጠላት ነው ሲሉ ቡድኑን ማውገዛቸው ይታወሳል።

አባ ገዳ ኩራ በታጣቂ ቡድኑ በሚፈጸሙ ጥቃቶች ሠላማዊ ሰዎች በመገደላቸው ቡድኑን ጠላት ብሎ መፈረጁ እንዳስፈለጋቸው ተናግረዋል።

የቦረና አባ ገዳ በማኅበረሰባቸው ዘንድ ከፍተኛ ተሰሚነት ያላቸው ሲሆኑ የሚያስተላልፉትም መልዕክት ተጽዕኖ ፈጣሪ ነው።

ህወሓት

ህወሓት በሽምቅ ውጊያ ወደ አገር መሪነት ከዛም ወደ የክልል አስተዳዳሪነት በመጨረሻም ወደ ሽምቅ ወጊያ ተመልሷል።

ለሦስት አስርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ በአገሪቱ የፖለቲካ መድረክ ላይ ዋነኛው ተዋናይ ሆኖ የቆየው ህወሓት ባለፈው ጥቅምት ከተከሰተው ግጭት ጋር በተያያዘ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕጋዊ ሰውነቱን አጥቶ እንዲሰረዝ ተደርጓል።

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የንጉሡ አስተዳደር ወድቆ ወታደራዊው መንግሥት ወደሥልጣን መውጣቱን ተከትሎ ነበር የካቲት 11/1967 ዓ.ም የትጥቅ ትግል መጀመሩን ያስታወቀው።

ለህወሓት የትጥቅ ትግል መነሻ የሆነው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ያቋቋሙት ማገብት (ማህበረ ገስገስቲ ብሔረ ትግራይ) የተባለው መደበኛ ያልሆነ ቡድን ነበር።

ማገብት በስምንት አባላት የተመሠረተ ሲሆን ከእነዚህም መካከል በሪሁ በርሀ (አረጋዊ በርሄ ዶ/ር)፣ አምባዬ መስፍን (ስዩም መስፍን) እና አመሃ ፀሃዬ (አባይ ፀሃዬ) ተጠቃሽ ናቸው።

ከደርግ ጋር የሚደረገው ጦርነት ወደ ሌሎቹ የአገሪቱ ክፍሎች ሲሸጋገር በየአካባቢዎቹ ያሉትን ሕዝቦች ይወክላሉ የተባሉ ድርጅቶችን ማቀፍ እንዲሁም ሊወክሉ ይችላሉ የሚባሉ እንዲቋቋሙ ህወሓት ጉልህ ሚና ተጫውቷል።

ይህንንም ተከትሎ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢህዴን)፣ ከኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) እና ከደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ጋር በመጣመር ኢሕአዴግ የተባለውን ግንባር ፈጠረ።

በህወሓት የበላይነት ይመራ የነበረው ኢሕአዴግ የደርግ መንግሥትን ከሥልጣን ካስወገደ በኋላ ለ27 ዓመታት አገር መምራት ችሏል።

ጠቅላይ ሚኒስተር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ግን በግንባሩ ውስጥ ለዓመታት የቆየው ቅሬታ ስር እየሰደደና እየጎላ መጣ።

በመጨረሻም ኢህአዴግ ከስሞ የብልጽግና ፓርቲ ሲተካው ህወሓት በአዲሱ ስብስብ ውስጥ ላለመግባት ከመወሰኑ ባሻገር "ውህደቱ ሕጋዊ አደለም'' በማለት ተቃውሞውን አስምቶ ነበር።

ህወሓት ከፍተኛ አመራሮቹን ይዞ ወደ ትግራይ ካቀና በኋላ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር የነበረው ግንኙነት ከመሻከር አልፎ ወደ ግጭት አምርቷል።

ከ6 ወራት በፊት በተጀመረው ጦርነት የፌደራሉ መንግሥት 'ህወሓት አብቅቶለታል' ሲል አውጇል።

የቡድኑ ፖለቲካዊና ወታደራዊ አመራሮች በተለያዩ ከፍተኛ ወንጀሎች ተጠርጥረው የእስር ማዘዣ ከወጣባቸው ወራት ተቆጥረዋል።

በርካታ የህወሓት አመራሮች በጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውና ሌሎች ደግሞ መገደላቸው የአገሪቱ ሠራዊት መገለጹ ይታወሳል።