በነቀምት ሆቴል ላይ በተወረወረ ቦምብ የሰው ህይወት ሲጠፋ፣ አስር ሰዎች ቆሰሉ

የፎቶው ባለመብት, Nekemte Communication
በምዕራብ ኦሮሚያ በምትገኘው የነቀምት ከተማ ሚያዝያ 2/2013 ዓ.ም በአንድ ሆቴል ላይ በተወረወረ የእጅ ቦምብ የአንዲት ግለሰብ ህይወት ሲጠፋ አስር ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱ ተነገረ።
ቦምቡ የተወረወረው ሆቴሉ ውስጥ በነበሩ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ላይ መሆኑም ተገልጿል።
የኦሮሚያ ልዩ ኃይል የነቀምት ሬጅመንት አዛዥ ኮማንደር ግርማ አብዲሳ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል አራቱ የፀጥታ ኃይል አባላት ሲሆኑ የተቀሩት ስድስቱ ደግሞ ሲቪሎች ናቸው ብለዋል።
ኮማንደሩ እንደሚያስረዱት ጥቃቱ የተፈፀመው ሚያዝያ 2 ቀን ቅዳሜ ምሽት በአንድ ግለሰብ ንብረት በሆነ ሆቴል ላይ ነው።
"የፀጥታ ኃይሎች ሲቪል ለብሰው እንደ ማንኛውም ተጠቃሚ በሆቴሉ ውስጥ እየተገለገሉ ነበር። በአጠቃላይ አስር ሰው ነው የተጎዳው፤ ከነዚህም መካከል አራቱ የኦሮሚያ ፖሊስና ልዩ ኃይል አባላት ናቸው" ብለዋል።
በጥቃቱ ህይወቷ ያለፈው በሆቴሉ ውስጥ የነበረች ሲቪል ሴት መሆኗን ኃላፊው ገልፈዋል።
ይህንን ጥቃት ስለፈፀመው አካል በተመለከተም ኮማንደር አብዲሳ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ናቸው ሲሉ ለቢቢሲ አስረድተዋል።
"ሌላ የሚጠረጠር አካል የለም። በአሁኑ ወቅት የኦሮሞ ሕዝብ ጠላት ኦነግ-ሸኔ ነው። ይህንን በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ። ከዚህ ቀደምም ቦምብ እየወረወሩ፣ መሳሪያ እየተኮሱ ሰዎች ሲገድሉ የከረሙት ኦነግ ሸኔዎች ናቸው።"
ኮማንደሩ ከሰሞኑ ጥቃቶች ጋብ ብለው የነበሩ ቢሆንም አሁን ግን እየተባባሰ መሆኑን ጠቁመዋል። "ኦነግ-ሸኔ የሚያደርሰው ጥቃት ትንሽ ጋብ ብሎ ነበር። አሁን ደግሞ እንደ አዲስ እየተነሳባቸው ነው" ብወለዋል።
ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ በጸጥታ ኃይሎች በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ስር እንደዋሉም አመልክተዋል።
"ከቅዳሜ ምሽት ጀምረን ብዙ ሰዎች በቁጥጥር ስር አውለናል። ተይዘው የተለቀቁ ሰዎች አሉ። አሁንም የምንፈልጋቸው ሰዎች አሉ" ብለዋል።
በሆቴሉ ላይ በተፈጸመው ጥቃት በሰው ላይ ከሰደሰው ሞትና የመቁሰል አደጋ በተጨማሪ በንብረትም ላይ ጉዳት መድረሱን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
መንግሥትና የጸጥታ አካላት በምዕራብ ኦሮሚያ ለሚፈፈሙ ጥቃቶች ተጠያቂ የሚያደርጉት ኦነግ-ሸኔ እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራ ቡድን ሲሆን በአካባቢው በተደጋጋሚ በሠላማዊ ሰዎች ላይ ከሚፈጸሙ ጥቃቶች ጋር ስሙ ይነሳል።
በቅርቡም በምዕራብ ወለጋ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች በቡድኑ ተፈጸሙ በተባሉ ጥቃቶች በርካታ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።












