የኮቪድ-19 ጫና በረመዳን ወቅት እንዳይበረታ የሙስሊም ወጣቶች ጥረት

ሳላሃዲን ሰኢድ ይባላል። የምሥራቋ ፈርጥ ድሬዳዋ ነዋሪ ሲሆን በንግድ ሥራ ይተዳደራል። ሳላሃዲን ባለፈው ዓመት የድሬዳዋ የወጣቶች ጀማ (ማኅበር) ሰብሳቢ ነበር።
በ2012 የኮሮናቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ በተነገረ በጥቂት ወራት ውስጥ ረመዳን መግባቱን ተከትሎ የድሬደዋ ሙስሊም ወጣቶች ማኅበር ልዩ ልዩ ሥራዎችን ሲሰራ ነበር።
በወቅቱ ታውጆ በነበረው የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ምክንያት የሐይማኖት ተቋማት በአብዛኛው ተዘግተው ከርመዋል። ሳላሃዲን "መስጊድ በመዘጋቱ ልቡ ያላዘነ ማን ነበር?" ሲል አንድ ዓመት ወደ ኋላ ተጉዞ ያስታውሳል።
"መስጊድ መሄድ ለአንድ ሙስሊም የዘወትር ተግባር ቢሆንም፣ በረመዳን መስጊድ ተዘግቶ ስናይ ግን ድጋሚ የሚከፍትም አይመስልም ነበር" ሲል እርሱን ጨምሮ ሕዝበ ሙስሊሙ ዘንድ ተፈጥሮ የነበረውን ሐዘን ያስታውሳል።
በድሬዳዋ ብቻ ሳይሆን ኮቪድ-19 ዓለምን የሚያሰጋ ወረረሽኝ ተብሎ ከታወጀ ገና በሦስተኛ ወሩ ነበር በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው የረመዳን ፆም የገባው።
በሚያዚያ 2012 ዓ.ም የዓለም የጤና ድርጅት በአንድ ወር ውስጥ በአምስት አህጉራት ቫይረሱ መግባቱ ሪፖርት ተደርጎልኛል በማለት ነበር ወረርሽኙን ዓለም አቀፍ ሲል ያወጀው።
ታዲያ በወቅቱ ከሚታወቀው ባህሪይው የማይታወቀው የሚበልጠው ኮሮናቫይረስ በመላው ዓለም ያሉ 1.8 ቢሊዮን ሙስሊሞች ታላቁ የረመዳን ጾምን በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እንዲያሳልፉ ተገድደው ነበር።
አገራት ይህ ገና ማንነቱ በቅጡ ያልተለየ በሽታ የዜጎቻቸውን ህይወት እንዳይቀጥፍ የሐይማኖት ቦታዎችን ጨምሮ የመሰባሰቢያ መንገዶችን አግደውም ነበር።
በእስላማዊ የቀን መቁጠሪያ ሂጅራ መሰረት፣ ዘጠነኛ ወር ላይ የሚውለው ረመዳን በኢትዮጵያ እና በሌላው የዓለም ክፍል ብቻ ሳይሆን በእስልምና ቅዱስ በሆነው የመካ ከተማም እንደቀደመው ተሰብስቦ መስገድ ቀርቶ ወደ ሳዑዲ አረቢያ መግባትም ክልክል ነበር።
ዓለም ከኮሮናቫይረስ ጋር የተሻለ ተላምዳ እና ከትባቱም በመላው ዓለም መዳረስ በጀመረበት ዓመት የረመዳን ወር ተጀምሯል።

የፎቶው ባለመብት, Salahadin
ድሬዳዋ
ሸምሰዲን ባለፈው ዓመት ረመዳን በድሬዳዋ ከተማ ብቻ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር ያክል ተዋጥቶ በከተማዋ ባሉ ቀበሌዎች በሙሉ ያሉ አቅመ ደካሞችን ማገዛቸው እንደሚያስደስተው ይናገራል።
"ድሬዳዋ ከአንድ ቤት ሁለት ሦስት ልጅ በውጭ አገር የሌለው የለም። በውጭ ያሉትም በከተማ ካሉት ብዙ ገንዘብ ሰብስበን ድጋፍ አድርገን ነበር" ሲል ያስታውሳል።
አክሎም በከተማዋ የኮሮናቫይረስ ያመጣው ድንጋጤ ከፍተኛ እንደነበር እና ይህም በተለይ በንግድ ላይ ለተሰማሩ ሰዎች ከፍተኛ ጫና አስከትሎ እንደነበርም ይገልጻል።
ነገር ግን ያኔ መስጊዶቹ መዘጋቱ እና የነበረው ጥንቃቄ ዋጋ ቢስ አልነበረም የሚለው ሸምሰዲን፤ በዚህ ዓመት የኮሮናቫይረስ ከፍተኛ ስርጭት ላይ እንደሚገኝ ከግምት ውስጥ በማስገባት ጥንቃቄው መቀነሱ ያሳስበዋል።
በመስጊዶች ውስጥ "ሰው ለራሱ ሲል እንዲጠነቀቅ ትምህርት እየተሰጠ ቢሆንም ቸልተኝነቱ ያሳስበኛል" ሲል ይናገራል።
"በአሁኑ ዓመት እርዳታ የማሰባሰብ ተግባራት አምብዛም አይታዩም" የሚለው ሳላሃዲን፤ ምን አልባት ጾሙ ሲገባ እርዳታዎች (ዘካ) ይደረጋል ብሎ እንደሚጠብቅ ይናገራል።
ነገር ግን አሁንም ወጣቶቹ እየተወያዩ እንደሚገኙ አና በተቻለ መጠን በዚህኛውም ረመዳን ድጋፎችን ለማጠናከር እና ወደ መስጊድ የሚመጡ ሰዎችን በማስተባባር ስርጭቱ እንዳይጨምር ለማድረግ ሥራ መጀመራቸውን ይናገራል።
ከአንድ ዓመት በፊት የኮሮናቫይረስ ከፍተኛ ስርጭት አይሎባት የነበረችው ድሬዳዋ አሁን ላይ በመላው አገሪቱ የተስፋፋው ኮሮናቫይረስ በሁሉም ከተሞች ተስፋፍቶ ስጋቱን ከከተማዋ ጋር ሌሎችም እንዲጋሩት አድርጓል።

የፎቶው ባለመብት, Salahadin
አዲስ አበባ
ልክ እንደ ሰላሃዲን ሁሉ ባለፈው ዓመት በአዲስ አበባ እርዳታ ሲያሰባስቡ ከነበሩ ወጣቶች መካከል ነው አዱኛው ሙጬ።
ባለፈው ዓመት 10 ሺህ አባወራዎችን ለአንድ ወር የሚሆን ቀለብ በማሰባሰብ ካከፋፈሉት ወጣቶች አንዱ የሆነው አዱኛው በተያዘው ዓመት ይቀዝቅዝ እንጂ ድጋፉ አልቀረም ሲል ያስረዳል።
በተያዘው ዓመትም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደቀጠሉ የሚናገረው አዱኛው፣ ከአንድ ሳምንት በፊት አፋር ክልል ሄደው ከነጃሺ በጎ አድራጎት ማኅበር ጋር ድጋፍ አድርገው መመለሳቸውን ይናገራል።
ባለፈው ዓመት በአፋር ክልል በጎርፍ የተጎዱ ሰዎችን በዕለት ደራሽ ድጋፍ ሲያግዙ መቆየታቸውን ያስታውሳል። የረመዳን ጾምን አስመልክቶም ለ150 አርብቶ አደሮች መልሰው እንደቋቋሙ አምስት አምስት ፍየል ለግሰው መመለሳቸውን ያስረዳል።
"ሁሌ ዱቄት ይዞ መሄድ ሳይሆን መልሶ ለማቋቋም ነው ፍየሎቹን የሰጠናቸው። በአንድ ኣመት አምስት ፍየል 15 ይሆናል ተብሎ ይታመናል፤ ይህም በዘላቂነት መልሰው እንዲቋቋሙ ያግዛል" ሲል ለቢቢሲ ገልጿል።
ነገር ግን እንዳለፈው ዓመት ድጋፍ የማሰባሰብ ሥራውን ማስተባባር በተለይም የማኅበራዊ ሚዲያውን የያዙት አጀንዳዎች ትኩረት አለማግኘቱን ያስረዳል። ወጣቶቹም የማስተባባር ሥራውን ማካሄድ የሚችሉበት ሌሎች አማራጮች እንዳልነበሯቸውም ይገልጻል።
አዱኛው ያለፈውን ዓመት ሲያስታውስም ምንም እንኳን ድጋፍን በማሰባሰብ እና መሰል ሥራዎች በመስጊድ ውስጥ ቢያሳልፍም ህዝበ ሙስሊሙ ውስጥ ተፈጥሮ የነበረውን ሐዘን ያስታውሳል።
"ብዙዎች መስጊድ ተዘግቶ ሲያዩ አልቅሰዋል፣ ረመዳን ታላቅ የሰደቃ ወቅት በመሆኑ ብዙ የተቸገሩ ሰዎች መስጊድ ደጅ ተቀምጠው የሚረዱበት ወር ነው። እነዚህ ሰዎች የዓመት ወጪ ጭምር የሚያገኙበት ወር ነው። በአጠቃላይ ለኔም በግሌ ከባዱ የረመዳን ወር ነበር" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
በ2013 ግን መስጊዶች ተከፍተው ረመዳን ጾም ተጀምሯል። ለአዱኛው ይህ መልካም ዜና ቢሆንም "ያለው መዘናጋት እጅግ ያሳስበኛል" ሲል ይነጋራል።
በአዲስ አበባ ሰዎች ማስክ የሚያደርጉት ፖሊስ እንዳይቀጣቸው ብቻ ይመስላል የሚለው ወጣቱ፤ ከአዲስ አበባ ውጪ ሲንቀሳቀስ ደግሞ ማስክ የሚለብስ ሰው እንደውም ኮሮናቫይረስ ያለበት ተደርጎ እንደሚታሰብ ይናገራል።
በመስጊድ ውስጥ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ምክንያት በሙስሊም መቃብር አካባቢ ያለውን ነገር እንደሚመለከት የሚያስረዳው አዱኛው ሁኔታውን አሳሳቢ ሲል ይገልጻል።
"በቀን ሦስት አራት ሰው ኮሮና ነው እየተባለ በጥንቃቄ ሲቀበር አያለሁ" በማለት ይህ በረመዳን ጾም ወቅት የሚደረጉ የማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች በአግባቡ ካልተደረጉ "እልቂት እንዳያመጡ እሰጋለሁ ይላል።
ታዲያ ከሐይማኖታዊ ስብስቦች ውጪም "መርካቶም፣ አውቶብስ ውስጥም ሆነ ሌላ ቦታም ጥንቃቄዎች ያለመኖራቸው በአጠቃላይ ገና ብዙ ማሻሻል ያስፈልጋል" ሲልም የግል ምልከታውን ያስቀምጣል።
መውጫ
በተለያዩ የዓለም ክፍሎች አሁንም መስጊዶችን ጨምሮ የእምነት ቤቶች ተዘግተዋል አልያም በአነስተኛ ቁጥር ማኅበራዊ ርቀቶች ተጠብቀው ሐይማኖታዊ ሥርዓቶችን በመከወን ላይ ይገኛሉ።
በኢትዮጵያ የሐይማኖት ተቋማት ከኮሮናቫይረስ መከሰት በፊት ወደ ነበረው አገልገሎት ከገቡ ሰነባብተዋል። ብዙዎች ማኅበራዊ ርቀትን መጠበቅ የመሳሰሉ ተግባራት ተረስተዋል ሲሉም ይደመጣል።
ታዲያ የተያዘው የረመዳን ጾምን ተከትሎ የሚካሄዱ የጋራ ሐይምኖታዊ ክንውኖች በጥንቃቄ ካልተከወኑ ብዙዎችን ሊጎዳ እንደሚችል እነዚሁ ወጣቶች ይናገራሉ።
"እኛ ወጣቶች የራሳችንን ሚና ተስፋ ሳንቆርጥ እንጫወታለን" የሚለው አዱኛው "አንድ ህይወት ማዳን ዓለምን ማዳን ነው፤ አንድ ነፍስ ማጥፋት ዓለምን ማጥፋት ነው" ሲል ቁርአንን በመጥቀስ የበጎ ፈቃድ ተግባራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ይናገራል።
ይህም የተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም በረመዳን ወቅት ጥንቃቄዎች እንዲካሄዱ እየጣሩ እንደሆነ ይገልጻል። ያለፈው ዓመት የመስጊድ መዘጋት ትርጉሙ ትልቅ እንደሆነ እና ይህ በሽታ ሥጋዊ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ህይወታችንን እንዳይጎዳ ቀድመን እንድንጠነቀቅ ሊያሳስበን ይገባል ይላል።
በተያዘው ዓመትም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማከፋፈል፣ ሰዎች ሲሰግዱ እንዲራራቁ እና እጅ መታጠብን ጨምሮ ማታ ማታ መስጊድ ላይ በማስተባባር ሕዝበ ሙስሊሙን በቫይረሱ እንዳይጎዳ ለማንቃት ማሰባቸውን ገለጿል።
"እነዚህ ነገሮች ዋጋ እንዳያስከፍሉን እና እንደቅጠል እንዳንረግፍ የሐይማኖት አባቶች ከማንም በላይ ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው" የሚለው አዱኛው "ይሄ ግን ለእነሱ ብቻ የሚተው ሳይሆን እኛ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ደግሞ ማታ ማታ በቡድን በቡድን ሆነን እናስተባብራል" ሲል ለቢቢሲ ገልጿል።













