'የሐዘን መግለጫ ማውጣት ሰልችቶናል' አቶ አገኘሁ ተሻገር

አቶ አገኘሁ ተሻገር

የፎቶው ባለመብት, AMMA

በተለያዩ ስፍራዎች በሚፈጸሙ ጥቃቶች በሚገደሉ የአማራ ተወላጆች የሐዘን መግለጫ መውጣት የክልሉ መንግሥት እንደሰለቸው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር ተናገሩ።

በምዕራብ ወለጋ ውስጥ የተገደሉ ሰላማዊ ሰዎችን በተመለከተ በሰጡት መግለጫ ላይ ርዕሰ መስተዳደሩ እንደተናገሩት በተደጋጋሚ በሚፈጸሙ ጥቃቶች ሐዘናቸው እንደበረታና ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ እንዲፈለግ ጠይቀዋል።

"የፖለቲካ ልዩነት ሊኖር ይችላል ህፃናትና እናቶች ግን መሞት የለባቸውም" ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ፤ "የሐዘን መግለጫ ማውጣት ሰልችቶናል፣ በጉዳዩ ላይ እልባት እንዲሰጥ እንፈልጋለን" ሲሉ ችግሩ በቶሎ መፍትሄ እንዲበጅለት ጥሪ አቅርበዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር ክስተቱን በማስመልከት በሰጡት መግለጫ ላይ በአማራ ብሔር አባላት ላይ የሚፈጸመውን ግድያ የፌደራል መንግሥት በአስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጥ ክልላቸው እንደሚፈልግ ተናግረዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በአማራ ላይ የሚፈጸመው ግድያ እንዲቆም የክልሉ መንግሥት በጉዳዩ ላይ አስቸኳይ ውይይት እንደሚፈልግም አስታውቀዋል።

በተለያዩ ጊዜያት በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በሚፈጸሙ ጥቃቶች "በተለይም ኦነግ-ሸኔ የተባለው ቡድን አማራን ነጥሎ በማጥቃት የሚታወቅ ነው። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ነፃ አውጭ ነኝ የሚል ቡድንም በአማራ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እያደረሰ ነው" ሲሉ ጥቃቱ በማን እንደሚፈጸም ተናግረዋል።

በአማራ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን የገለጹት አቶ አገኘሁ፤ ከሰሞኑ በተፈጸመው ግድያም የክልሉ መንግሥት ማዘኑንና "ይህ ጉዳይ ካልተሻሻለ የአገሪቱን ዜጎች ተቻችለው የመኖር ሁኔታን አደጋ ላይ የሚጥል ነው" በማለት ችግሩ የአማራ ክልልን እንዳሳሰበው ገልጸዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በምዕራብ ኦሮሚያ ጥቃቱ ፈጽሟል ያሉት ኦነግ-ሸኔ "ከኦሮሚያ ክልል አልፎ በክልላችን ገብቷል" በማለት፣ "አንዳንዶች ኦነግ-ሸኔ ስለመኖሩና ስላለመኖሩ ሊነግሩን ይፈልጋሉ፤ ምን አይነት መግለጫ ማውጣት እንዳለብን ሊነግሩን የሚፈልጉም አሉ። ይህ ተገቢ አይደለም" ማለታቸውን የክልሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል።

የምዕራብ ወለጋ ጥቃት

በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን ታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት የበርካታ ሰዎችን መገደል ተከትሎ ድርጊቱ ከተለያዩ ወገኖች ውግዘት ገጥሞታል።

ማክሰኞ መጋቢት 21/2013 ዓ.ም በምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ገንቤል በተባለው ወረዳ በቦኔ ቀበሌ የነዋሪዎችን ማንነት በለየ ሁኔታ የተፈጸመውን ጥቃት በቀዳሚነት ይፋ ያደረገው የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ነበር።

መስተዳደሩ ስለተፈጸመው ጥቃት ባወጣው መግለጫ ላይ "አሰቃቂና ዘግናኝ" ያለውን ጥቃት የፈጸመው ኦነግ-ሸኔ እንደሆነ ጠቅሶ በጥቃት ፈጻሚዎቹ ላይ እርምጃ መወሰዱንና ይህም እንደሚቀጥል ገልጾ ነበር።

በማስከተልም የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል አራርሳ መርዳሳ ኦነግ-ሸኔ የተባለው ቡድን በጥቃቱ "ጭፍጨፋ ፈፅሟል" በማለት ቡድኑን ተጠያቂ አድርገዋል።

ኮሚሽነሩ ጨምረውም በጥቃቱ የተገደሉት 28 ሰዎች ሲሆኑ ከመካከላቸውም 16ቱ ወንዶችና 12ቱ ደግሞ ሴቶች መሆናቸውን ገልጸው ሌሎች 12 ሰዎችም ጉዳት ደርሶባቸዋል ብለዋል።

ጥቃቱ መፈጸሙ ከተሰማ በኋላ የተለያዩ ወገኖች በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ በማውገዝ መግለጫ በማውጣት ሐዘናቸውን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ በንጹሐን ዜጎች ላይ የደረሰውን ጥቃት እንደሚያወግዙና የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ለሟች ቤተሰቦችና ለኢትዮጵያውያን ገልጸዋል።

ጨምረውም በጥቃት ፈጻሚዎቹ ላይ የክልልና የፈዴራል መንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በቅንጅት የአጸፋ እርምጃ እየወሰዱ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረውም "ጠላቶቻችን በውስጥና በውጭ ተደራጅተው ንጽሐን ዜጎቻችንን በመግደል የጀመርነውን ጉዞ ለማሸማቀቅና ከመንገዳችን ለማስወጣት ጥረት እያደረጉ ነው። መሥዋዕትነት እየከፈልንም ቢሆን የኢትዮጵያን አንድነት አጠናክረን ጉዟችንን እንቀጥላለን" ብለዋል።

ሕዝቡም በጥፋት ኃይሎች ወጥመድ ላይ ላለመግባት በማስተዋል እንዲጓዝ ጠይቀው፤ በእንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች ከመንግሥት ጋር ተባበሮ ጥፋተኞችን ወደ ሕግ ለማቅረብና ግድያዎች እንዲቆሙ በትብብር ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን

ኮሚሽኑ በምዕራብ ወለጋ በነዋሪዎች ላይ የተፈፀመው ጥቃት በአካባቢው ያለው የፀጥታ ሁኔታ አለመሻሻሉንና ይልቁንም በክልሉና በአዋሳኝ አካባቢዎች እየተስፋፋና ተያያዥ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እያስከተለ መሄዱን ያሳያል ብሏል።

ጨምሮም የፌዴራል መንግሥት አካባቢውን ለማረጋጋት በጊዜያዊነት ከሚወስዳቸው እርምጃዎች በተጨማሪ ነዋሪዎች በየትኛውም ክልል በሰላም የመኖር መብታቸውን በሚያረጋግጥ መልኩ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚያስችል ሁኔታ ለመፍጠር መጠነ ሰፊና ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ እቅድ መንደፍ እንደሚኖርበት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ገልጿል።

የአሜሪካ ኤምባሲ

ኤምባሲው በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ ሰሞኑን በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ክልሎች የተፈጸሙ ጥቃቶችን በሚመለከት ባሰፈረው መልዕክት ላይ ድርጊቶቹን አውግዟል።

"በኦሮሚያ ምዕራብ ወለጋና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ መተከል ውስጥ የተፈጸሙትን የሰላማዊ ሰዎች ግድያን አጥብቀን እናወግዛለን" ብሏል።

ለሟቾች ቤተሰቦችና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተሰማውን ሐዘን የገለጸው ኤምባሲው፤ "እንዲህ አይነት ግድያዎችን ተቃውመን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን እንቆማለን" ሲል ጥቃቶቹን አውግዟል።

ኢዜማ

ተፎካካሪ ፓርቲ የሆነው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ-ኢዜማ ሰሞኑን የተፈጸመውን ጥቃት መሠረት አድርጎ "አገሪቱ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለውን ማንነት ላይ ያተኮረ ግድያን" በተመለከተ መግለጫ ውጥቷል።

ኢዜማ በመግለጫው ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በተለይም በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች ዜጎች በማንነታቸው እየተለዩ በአሰቃቂ ሁኔታ በተደጋጋሚ ጥቃት ሲደርስባቸው መቆየቱን ጠቅሶ፤ በዚህ ሳምንት በምዕራብ ወለጋ የተፈጸመውን ግድያ በማውገዝ ሐዘኑን ገልጿል።

በዚህ ሳምንት ከተፈጸመው ጥቃት ከተረፉ ሰዎች ሰማሁ ያለው ኢዜማ "ጥቃቱ ከመፈፀሙ በፊት አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ አካባቢውን እንዲያስተዳድሩ ኃላፊነት ከተሰጣቸው የቀበሌና ወረዳ ኃላፊዎች ማስፈራሪያ ደርሷቸው ነበር" ብሏል።

በተደጋጋሚ የተፈጸሙት ጥቃቶችና ወንጀሎች በታወቁና ውስን በሆኑ ቦታዎች መሆኑን የገለጸው ኢዜማ፤ ይህም "በክልልም ሆነ በፌደራል መንግሥት በኩል ችግሩን የሚመጥን ትኩረት ላለማግኘቱ አመላካች ነው" ብሏል።

የአገሪቱን ሰላም ለማናጋት በአገሪቱ ውስጥ ባሉ ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው ማኅበረሰቦች መካከል የእርስ በርስ ግጭት ሊያስነሱ የሚችሉ ጥቃቶች ሆን ተብሎ በተቀነባበረ መንገድ እየፈፀሙ መሆናቸውን ፓርቲው ይገልጻል።

ፓርቲው በጥቃቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች መደረግ ስላለበት ድጋፍና በዘላቂነት እንዲህ አይነቶቹን ጥቃቶች ለማስቆም ሊወሰዱ ይገባል ያላቸውን እርምጃዎች በመግለጫው ላይ አስፍሯል።

ኦነግ-ሸኔ

ሰሞኑን የተከሰተውና ቢያንስ ለ28 ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነውን ጥቃት ፈጽሟል ተብሎ የተከሰሰው መንግሥት ኦነግ-ሸኔ የሚለውና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን በምዕራብ ኦሮሚያ እንደሚንቀሳቀስ ይነገራል።

ቡድኑ ከሁለት ዓመት በፊት የትጥቅ ትግልን ትቶ ወደ አገሪቱ የፖለቲካ መድረክ ከተመለሰው ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር ተለይቶ የወጣ ሲሆን ከበርካታ ጥቃቶችና ግድያዎች ጋር ስሙ በተደጋጋሚ ሲነሳ የቆየ ነው።

ታጣቂው ይንቀሳቀስባቸዋል በሚባሉት የምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች በተለያዩ ጊዜያት በተፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ ሠላማዊ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን በርካቶች ደግሞ ከቤት ንብረታቸው እንደተፈናቀሉ ተዘግቧል።

በተጨማሪም በአካባቢው ባሉ የመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ የሚሰሩ ሰዎችን፣ የጸጥታ አካላትንና አመራሮችን በተለያዩ ጊዜያት በቡድኑ በተፈጸሙባቸው ጥቃቶች ሰለባ ሆነዋል።

ለእነዚህ ጥቃቶችም መንግሥት ተጠያቂ የሚያደርገው በኩምሳ ድሪባ (ጃል መሮ) ይመራል የሚባለው ኦነግ-ሸኔን ሲሆን ቡድኑ ግድያዎቹን አለመፈጸሙንና በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ እንደሚፈልግ ሰሞኑን መሪው ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ተናግሯል።

መንግሥት ታጣቂ ቡድኑን ከአካባቢው ለማስወገድ በተለያዩ ጊዜያት በወሰዳቸው እርምጃዎች በርካታ የቡድኑን አባላት መግደሉንና መማረኩን ሲገልጽ መቆየቱ ይታወሳል።

የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር እንዳሉት ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ የጸጥታ አካላት በኦነግ-ሸኔ ላይ በተወሰዱት እርምጃ 1947 አባላቱ ሲገደሉ 489ቱ ደግሞ መማረካቸውን ተናግረዋል።