ህዳሴ ግድብ፡ በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ መካከል የሚደረገው ውይይት ሊጀመር ነው

የፎቶው ባለመብት, Maxar Technologies via Reuters
በታላቁ የህዳሴ ግድም ዙሪያ በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ መካከል የሚካሄደው ውይይት በመጪው ቅዳሜና እሁድ እንደሚጀመር ኢትዮጵያ አስታወቀች።
ኢትዮጵያ እየነባችው ባለው ግዙፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ የውሃ አሞላልና ቀጣይ ሂደት ላይ እየተጀመረ ሲቋረጥ የቆየው የሦስትዮሽ ድርድር ለረጅም ጊዜ ከተስተጓጎለ በኋላ ነው አሁን እንደሚቀጥል የተነገረው።
የኢትዮጵያ ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር የሆኑት ስለሺ በቀለ (ዶ/ር፣ ኢንጂ) በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ እንዳሰፈሩት በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ የሚደረገው ውይይት በቅርቡ የአፍሪካ ሕብረትን የሊቀመንበርነት ቦታን ከደቡብ አፍሪካ የተረከበችው ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ትመራዋለች።
ከሊቀመንበሩ ለሦስቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እንዲሁም የውሃና ኢነርጂ ሚኒስተሮች በቀረበ ግብዣ መሰረት ውይይቱ እንደሚጀመር ሚኒስትር ስለሺ ገልጸዋል።
በውይይቱ ላይ ከሦስቱ አገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት በተጨማሪ የአፍሪካ ሕብረት ባለሙያዎች፣ ታዛቢዎችና ሌሎች ባለሙያዎች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
ሚኒስትሩ በትዊተር መልዕክታቸው ላይ ኢትዮጵያ በተፋሰሱ አገራት ላይ የጎላ ጉዳትን በማያስከትል ሁኔታ በመርህ ላይ የተመሰረተ፣ ፍትሃዊና ምክንያታዊ የሆነ የውሃ አጠቃቀም እንዲኖር ቁርጠኛ ናት ብለዋል።
አባይ ድንበር ተሻጋሪ ውሃ ነው፤ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ደግሞ ለኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት በጣም አስፈላጊ መሰረት ልማት ሲሆን ለተፋሰሱ የታችኛው አገራት ደግሞ ይህንን ውድ የተፈጥሮ ሃብት ለማልማትና በተሻለ ሁኔታ ለመጠቀም ያስችላቸዋል ብለዋል።
ድርድሩ ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ ተቋርጦ የቆየ ሲሆን ምንም እንኳን ተቀባይነት ባያገኝም ሱዳንና ግብጽ ኢትዮጵያ ሁለተኛ ዙር የግድቡን የውሃ ሙሌት ከመጀመሯ በፊት አሳሪና ሕጋዊ ስምምነት እንድትፈርም በተደጋጋሚ ሲጠይቁ ቆይተዋል።
ጨምረውም ውይይቱን አሁን እየመራው ካለው የአፍሪካ ሕብረት በተጨማሪ ሌሎች ዓለም አቀፍ አደራዳሪዎች እንዲሳተፉበት ሲወተውቱ ቢቆይም፤ ከኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት ሊያገኝ አልቻለም።
ግንባታው ከተጀመረ አስር ዓመታትን ያስቆጠረው ታላቁ የህዳሴ ግድም ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የተደረገበት ሲሆን ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ ለአገሪቱና ለአካባቢው አገራት ዋነኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ምንጭ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
የግብጽ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አልሲሲ ባለፈው ማክሰኞ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ እየገነባችው ባለው ግድብ ሳቢያ አገራቸው በምታገኘው የውሃ መጠን ላይ ተጽእኖ የሚፈጠር ከሆነ 'የከፋ አካባቢያዊ ችግር' ይፈጠራል ሲሉ አስጠነቅቀው ነበር።
ፕሬዝዳንቱ "ማንም ከግብጽ ውሃ ላይ አንዲት ጠብታ መውሰድ አይችልም፤ ይህ ከሆነ ደግሞ ከሚታሰበው በላይ አደገኛ አለመረጋጋት በአካባቢው ይፈጠራል" ብለዋል።
ኢትዮጵያ ግድቡን የምትጠቀመው ውሃውን በግዛቷ ውስጥ ለሚያስቀሩ ፕሮጀክቶች እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ብታስረዳም ሱዳን በተለይም ግብጽ የትኛውም አይነት በውሃው ላይ የሚከናወን ሥራ የእነሱን ይሁንታ ሳያገኝ መካሄድ እንደሌለበት ሲገልጹ ቆይተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ በአገሪቱ ምክር ቤት ላይ ባደረጉት ንግግር "ውሃ አሞላሉን በተመለከተ ተደራድረን ስናበቃ እንሙላ ካልን ክረምቱ ያልፍና በዓመት 1 ቢሊየን ዶላር እናጣለን" ሲሉ የውሃ ሙሌቱን ማዘግየት እንደማይቻል አመልክተዋል።
የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር የሆኑት ስለሺ በቀለም (ዶ/ር፣ ኢንጂ.) ኢትዮጵያ ወደ መጠናቀቁ የተቃረበውን የህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በምንም ዓይነት መልኩ እንደማታራዝመውና ለዚህም የሚያበቃ አሰራርና ምክንያትም እንደሌለ ተናግረዋል።
ይህ በአፍሪካ ትልቁ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ይሆናል የተባለው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ በአሁኑ ጊዜ 80 በመቶ ያህሉ ግንባታው የተጠናቀቀ ሲሆን በሚቀጥለው ዓመት በተወሰነ ደረጃ ኤሌክትሪክ ማመንጨት እንደሚጀመር ይጠበቃል።
የአባይ ወንዝን 85 በመቶ ያህሉን ውሃ የምታመነጨው ኢትዮጵያ አስካሁን ድረስ የረባ ጥቅም ሳታገኝ የቆየች ሲሆን ግብጽና ሱዳን ግን ሙሉ ለሙሉ በሚባል ሁኔታ የአባይ ወንዝን ለተለያዩ ግልጋሎቶች እያዋሉት ይገኛሉ።
በዚህም ሳቢያ በአባይ ወንዝ ውሃ ላይ ጥገኛ የሆነችው ግብጽ፣ ግድቡ በሚደርሳት የውሃ መጠን ላይ ከፍተኛ መቀነስን ያስከትላል በማለት ስጋቷን በይፋ ስትገልጽ ቆይታለች።















