በምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ገንቤል ወረዳ ስለተፈፀመው ጥቃት ነዋሪዎች ምን ይላሉ?

ካርታ

በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ገንቤል ወረዳ ማክሰኞ መጋቢት 21/2013 ዓ.ም በዞኑ ውስጥ በሚገኘው በቦኔ ቀበሌ ውስጥ በሚገኙ ሰዎች ላይ "አሰቃቂና ዘግናኝ" መፈፀሙን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት አስታውቋል።

ክልሉ ትናንት ባወጣው መግለጫ ላይ ጥቃቱን ያደረሱት የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ናቸው ሲል ወንጅሏል።

መጋቢት 21/2013ዓ.ም ከምሽቱ 1፡30 ጀምሮ ጥቃቱ መፈፀሙን የሰባት ልጆች አባት የሆኑት የቦኔ ቀበሌ ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ስማቸው እንዳይጠስ የጠየቁት እኚህ የአካባቢው ነዋሪ እንዳሉት ተኩስ ሲሰሙ ልጆቻቸውን ይዘው ወደ ጫካ በመሸሽ መትረፋቸውን የተናገሩ ሲሆን ጨምረውም ቤቶች መቃጠላቸውን፣ ሴቶች፣ አዛውንቶችና ሕጻናት መገደላቸውን ተናግረዋል።

ሌላኛው ቢቢሲ ያነጋገራቸው ግለሰብ ደግሞ ወደ አካባቢው በ1977 ዓ.ም መምጣታቸውን ገልፀው ጥቃቱ እርሳቸው እና ቤተሰባቸው ከሚኖሩበት ስፍራ አቅራቢያ መፈፀሙን፣ አራት ልጆቻቸውን ይዘው በመሸሽ መትረፋቸውን ተናግረዋል።

28 ሰዎች በትናንትናው ዕለት መቅበራቸውን የሚናገሩት የሰባት ልጆች አባት የሆኑት ግለሰብ፣ በጥቃቱ ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል 18 ሰዎች ወደ ነጆ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ገልፀዋል።

የአራት ልጆች አባት የሆኑት የአካባቢው ነዋሪ ደግሞ በጥቃቱ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር 30 መሆን ይናገራሉ።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ረቡዕ ምሽት ላይ ይፋ እንዳደረገው በምዕራብ ወለጋ ውስጥ በሚገኘው በዚህ ወረዳ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት የተገደሉት ሰዎች 28 መሆናቸውንና ጉዳት የደረሰባቸው 12 መሆኑን ገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይም ዛሬ፣ ሐሙስ ዕለት በምዕራብ ወለጋ የደረሰውን ጥቃት አውግዘው፣ በሁሉም ቦታ በደርሰው ጥቃት የአጸፋ እርምጃ በክልልና በፌዴራል መንግሥት ቅንጅት እየተወሰደ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የ X ይዘትን ይለፉት
ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ፡ የሦስተኛ ወገን ይዘቶች ማስታወቂያ ሊኖራቸው ይችላል

የ X ይዘት መጨረሻ

ቢቢሲ ያነጋገራቸው እነዚህ የቦኔ ቀበሌ ነዋሪዎች ከእነዚህም በተጨማሪ በአካባቢው ከብቶቻቸውን በመያዝ ለግጦሽ በአቅራብያ ወደ ሚገኝ ቀበሌ ይዘው ሄደው የነበሩ 15 ታዳጊዎችም በታጣቂዎች መገደላቸውን ገልፀዋል።

ሁለቱም ግለሰቦች ማክሰኞ ምሽት የተከሰተውን ለቢቢሲ ሲያስረዱ፣ ታጣቂዎቹ ግለሰቦቹን ከየቤቱ በማውጣት አንድ ቦታ በመሰብሰብ በጥይት መግደላቸውን ገልጸዋል።

ከጥቂት ወራት በፊት በተመሳሳይ በምዕራብ ኦሮሚያ ውስጥ በሚገኝ ሌላ ስፍራ ላይ ታጣቂዎች ነዋሪውን በአንድ ቦታ ላይ በመሰብሰብ በፈጸሙት ጥቃት በርካታ ሰዎችን መገደላቸው ይታወሳል።

የሰባት ልጆች አባት የሆኑት ግለሰብ ጎረቤቶቻቸውን እና ዘመዶቻቸውን በጥቃቱ ማጣታቸውን ተናግረው፣ ከየቤቱ ተጠርተው መንገድ ላይ አውጥተው በጥይት ከተገደሉት መካከል አዛውንቶች፣ ታማሚ፣ የአንድ እና ሁለት ዓመት ሕጻናት የታቀፉ እናቶች እንደሚገኙበት አስረድተዋል።

ጥቃት አድራሾቹ በከፈቱት ተኩስ ቤቶች መቃጠላቸውን የሚገልፁት እኚህ ግለሰብ ከተደበቁበት ጫካ የተመለሱት ሲነጋ መሆኑን ይናገራሉ።

ጥቃቱን ተከትሎ የክልል የጸጥታ አካላት በአካባቢ በመድረስ በጥቃት ፈጻሚዎቹ ላይ የአጸፋ እርምጃ መውሰዱን የተገለፀ ቢሆንም፤ የአካባቢው ነዋሪዎች ግን የኦሮሚያ ልዩ ኃይል መጋቢት 22/2013 ዓ.ም ማለዳ ከረፈደ መድረሱን ተናግረዋል።

የሰባት ልጆች አባት የሆኑት ግለሰብ ከእረኞቹ መካከል በየጫካው ሞተው የቀሩ ይኖራሉ የሚል ስጋት እንዳላቸው ይናገራሉ።

የአራት ልጆች አባት የሆኑት ግለሰብ ከዚህ በፊት በአካባቢው የሚገኙ ታጣቂዎች እነርሱ ላይ ጥቃት እንደማይደርስባቸው እና ስጋት እንዳይገባቸው በመግለጽ ከአካባቢው እንዳይሄዱ ሲነግሯቸው እንደነበር ይናገራሉ።

አሁንም ቢሆን ለደኅንነታቸው እንደሚሰጉ የሚናገሩት እነዚህ ግለሰቦች "ቤታችን ገብቶ ለማደር ስለምንሰጋ አዳራችን ከጫካ ነው" ብለዋል።

በአሁኑ ጊዜ ጥቃት በተፈጸመበት አካባቢ የክልሉ ልዩ ኃይል መሰማራቱን ጨምረው አስረድተዋል።

ቢቢሲ ጥቃቱ የተጸፈመበት አካባቢ አስተዳዳሪን ምላሽ ለማግኘት ወደ ተንቀሳቃሽ ስልካቸው በተደጋጋሚ ቢደውልም ባለመነሳቱ ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል።

የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የተፈጸመውን ግድያ በተመለከተ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ እንዳሰፈረው "በምዕራብ ወለጋ በነዋሪዎች ላይ የተፈፀመው ጥቃት በአካባቢው የፀጥታ ሁኔታ አለመሻሻሉንና ይልቁንም ወደ አዋሳኝ አካባቢዎች እየተስፋፋና ተያያዥ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እያስከተለ መሄዱን ያሳያል" ብሏል።

ወደ ሰላሳ ለሚደርሱ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነውን ጥቃት የተፈጸመው ኦነግ-ሸኔ በተባለው ቡድን እንደሆነ የክልሉ መንግሥትና ከጥቃቱ የተረፉ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ኦነግ-ሸኔ የተባለው ቡድን ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር አፈንግጦ የወጣ መሆኑ የሚነገር ሲሆን ባለፉት ሁለት ዓመታት በምዕራብ ኦሮሚያ በሚገኙ አካባቢዎች በተደጋጋሚ በሰላማዊ ሰዎች ላይ በመፈጸም ስሙ ይተቀሳል።

በተጨማሪም ቡድኑ የጸጥታ አካላትን፣ የአካባቢ አስተዳዳሪዎችንና የመንግሥት ሠራተኞችን ኢላማ በማድረግ ግድያዎችን መፈጸሙ በተደጋጋሚ ተዘግቧል።

ቡድኑ በሚፈጽመው ጥቃት የቀበሌና የክልል አመራሮችን ጨምሮ በርካታ ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውን ያመለከተው የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ረቡዕ እለት ባወጣው መግለጫ፤ በጥቃቶቹ የግልና የመንግሥት ንብረቶች መውደማቸውንም ገልጿል።

የታጣቂ ቡድኑ እንቅስቃሴ በተለይ በምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች እጠነከረ በመጣበት ጊዜ የፌደራልና የክልሉ የጸጥታ ኃይሎች ተከታታይ እርምጃዎችና ዘመቻ ማካሄዳቸው ይታወሳል።

በዚህም መንግሥት ታጣቂ ቡድኑን ከአካባቢው ለማስወገድ በተለያዩ ጊዜያት በወሰዳቸው እርምጃዎች በርካታ አባላቱን መግደሉንና መማረኩን ሲገልጽ መቆየቱ ይታወሳል።

የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር እንዳሉት ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ የጸጥታ አካላት በኦነግ-ሸኔ ላይ በተወሰዱት እርምጃ 1947 አባላቱ ሲገደሉ 489ቱ ደግሞ መማረካቸውን ተናግረዋል።

ቡድኑ በሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ የሚፈጽመው ጥቃት በተለይ በዚህ ዓመት እተደጋገመና የሚገደሉ ሰዎች ቁጥርም እየበረከተ መጥቷል።