ሦስት ሰዎች በምዕራብ ወለጋ በታጣቂዎች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, GREAT COMMISSION FB
የታላቁ ተልዕኮ በኢትዮጵያ (ግሬት ኮሚሽን) አገልጋዮች የሆኑ ሁለት ግለሰቦችና አንድ ተማሪ በምዕራብ ወለጋ ገንጂ ከተማ አቅራቢያ በታጣቂዎች በጥይት መገደላቸውን የድርጅቱ ዳይሬክተር አቶ ግርማ አልታዬ ለቢቢሲ ገለፁ።
የአካባቢው ባለስልጣናት ግድያው የተፈፀመው በአካባቢው ታጥቀው በሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ነው ማለታቸውን የሚናገሩት አቶ ግርማ ግለሰቦቹ በበርካታ ጥይት ተመትተው መሞታቸውን አስረድተዋል።
አቶ ግርማ የድርጅታቸው ሠራተኞች የተገደሉብትን ሁኔታ ሲያስረዱ "አቶ ምስጋን ሥራ በመዘጋቱና ወደ ቤተሰቦቹ ለመሄድ በመፈለጉ እንዲሁም በነቀምት የትራንስፖርት እጥረት ስለነበር አቶ አሰፋ መኮንን በድርጅቱ መኪና እንዲሸኙት" መደረጉን ይገልፃሉ።
አቶ አሰፋ የ10ኛ ክፍል ተማሪ የሆነውን ልጃቸውን ሳሙኤል አሰፋን ጭነው ወደ ጊምቢ ግለሰቡን ለመሸኘት እንደሄዱ ያስረዳሉ።
"ከጊምቢ በኋላ ወደ ውስጥ ወደ ገንጂ መግባታቸውን በወቅቱ አላወቅንም ነበር" የሚሉት አቶ ግርማ ወደ ከተማ ሲቃረቡ የተኩስ ርምታ እንደተከፈተባቸው ተናግረዋል።
"ምናልባት ከጊምቢ በኋላ ትራንስፖርት በማጣታቸው ምክንያት ወደ ውስጥ ለመዝለቅ ወስነው ይሆናል" ሲሉ ሁኔታው የተቀየረበትን አጋጣሚ ያስረዳሉ።
ከሟቾቹ መካከል የሆኑት አቶ አሰፋም ሆኑ አቶ ምስጋኑ "በአካባቢው ማኅበረሰቡ ድረስ በመዝለቅ የሚያገለግሉ ነበሩ" ያሉት አቶ ግርማ፤ የአቶ ምስጋኑ የትውልድ አካባቢያቸው ጭምር መሆኑን ገልፀዋል።
ታላቁ ተልዕኮ በኢትዮጵያ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ መንቀሳቀስ ከጀመረ አርባ ዓመት ሆኖታል የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ "ድርጅታችን ከማንኛውም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የራቀ ነው" በማለት ሠራተኞቻቸው ትኩረት ተደርጎባቸው መጠቃታቸውን እንደማያምኑ ይገልጻሉ።
ምዕራብ ወለጋ ከ20 ዓመት በላይ ተንቀሳቅሰናል በማለትም ጥቃት ይደርስብናል የሚል ስጋት በሠራተኞቻቸውም ላይ እንደሌለ ያስረዳሉ።
ግለሰቦቹ ተሳፍረውበት የነበረው መኪና በበርካታ ጥይት መመታቱን የሚናገሩት ዳይሬክተሩ ከፍተኛ ጉዳት ስለደረሰበት በአካባቢው ያለው የኮማንድ ፖስት ካምፕ ውስጥ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
አቶ ምስጋኑ ከትናንት በስቲያ በትውልድ መንደራቸው፣ አቶ አሠፋና ልጃቸው ደግሞ በትናንትናው ዕለት በጉደር ከተማ ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈፅሟል ብለዋል።
በምዕራብ ኦሮሚያ ከዚህ ቀደምም በተደጋጋሚ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጨምሮ በተለያዩ ሰዎች ላይ ጥቃትና ግድያ ተፈጽሟል።
አካባቢውም ከክልሉና ከፌደራል መንግሥቱ በተወጣጣ ኮማንድ ፖስት ስር ከሆነ ረጅም ጊዜ እንደሆነው ይታወቃል።












