ሕጻናት ጤና፡ አሰቃቂ ጥቃቶች ሲፈፀሙ ያዩ ሕፃናት ለምን ዓይነት የአዕምሮ ጤና ችግር ይጋለጣሉ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሃዘን ያጠላበት መንደር፣ ስጋት ያንዣበበት አድባር። የተጎሳቆሉ እናቶች፣ ብርታት የከዳቸው አባቶች። ባረሱበት እጃቸው የእርዳታ እህል የሚለምኑ ቤተሰቦች።
እንባ ያቆሩ ዐይኖች ፣ በእንባ የራሱ ተርበትባች ጉንጮች፣ ያደፈ ልብስ ፣ ያረረ ከንፈር፣ መሄጃ የቸገራቸው ትንንሽ እግሮች።
ጥቃቶችን ተከትሎ ማሕበራዊ ሚዲያዎችን የሚያጨናንቁ ምስሎች ላይ የሚታዩ ናቸው።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በተፈፀሙ ጥቃቶች ንፁሃን ዜጎች ተገድለዋል። ጉዳት ደርሶባቸዋል። ንብረታቸው ወድሟል።
ዘግናኝ ጥቃቶች ቦታና ጊዜን ሳይመርጡ፤ በጨቅላ ሕጻናት ፊት ተፈፅመዋል።
ራሳቸው ሕጻናቱ ሳይቀሩ የጥቃቶቹ ሰለባ ሆነዋል።
ከእናታቸው አሊያም ከአባታቸው ጉያ ሥር ሳሉ ወላጆቻቸው ተነጥቀው ተገድለውባቸዋል።
ድርጊቱ ከልጅነት አዕምሯቸው በላይ የሆነባቸው ራሳቸውን ለማጥፋት ሞክረዋል፤ ያጠፉም እንዳሉ ሰምተናል።
በአሃ የሥነ ልቦና አገልግሎት ዳሬክተርና አማካሪ የሆኑት አቶ ሞገስ ገብረ ማሪያም በዓለም አቀፍ ደረጃ በጦርነትና በግጭት ምክንያት የሚደርሰው ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው ይላሉ።
በተለይ ደግሞ ካለፉት ሁለት አስርታት ወዲህ ቅርፁን በቀየረ መልኩ የልጆችን አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ሁኔታ በሚጎዳ ሁኔታ እጅግ ተባብሶ እንደሚገኝ ይናገራሉ።
ሕጻናት በግጭቶችና ጥቃቶች የሚደርስባቸው የሥነ ልቦና ተፅዕኖ እንደ እድሜ ደረጃቸው፣ ማለትም ባላቸው የስሜት፣ የቋንቋና የአስተሳሰብ መዳበር እንደሚለያይ የሚናገሩት አቶ ሞገስ፣ ሕጻናት በዚህ የስሜት ስስነት ላይ ሳሉ ጥቃቶችን ማየታቸው ወይም ማስተናገዳቸው ለከፋ የአዕምሮ ጤና ችግር ይዳርጋቸዋል ይላሉ።
ባለሙያው እንደሚሉት ሕጻናት እንዲህ ዓይነት አሰቃቂ ጥቃቶችን ሲያዩ፣ የሰው ልጅ ስሜቱን በውጫዊ መንገድ የሚቆጣጠርበትን ሥርዓት [Emotional Regulation] ያፈርሰዋል። ከአስተሳሰብ ጋር ያለውን ሥርዓት ያዛባዋል። ይህ ግን እንደ ሕጻናቱ የእድሜ ደረጃ ሊለያይ ይችላል።
ሥነ ልቦና ማለት አስተሳሰብ፣ ስሜትና ባህርይ ነው የሚሉት ባለሙያው፤ ስሜትና አስተሳሰብ ሲፈርሱ በባህርይና በአካል ላይ ያለው ተፅዕኖ ጎልቶ እንደሚታይ ይናገራሉ።
ሕጻናት እንዲህ ዓይነት ጥቃቶች ሲፈፀሙ ሲያዩ የሚሰማቸው ምን ይሆን?
ሕጻናቱ አሰቃቂ ጥቃቶችን ሲያዩ ወዲያው እና እየቆየ ሲሄድ የሚሰማቸው ስሜት አለ። የሚያሳዩት ባህርይም እንዲሁ። ባለሙያው በአጭርና በረዥም ጊዜ የሚታዩ ባህርያት ሲሉ ይለዩታል።
. በአጭር ጊዜ
በስሜት፡ የመደንገጥ፣ የመረበሽ፣ የፍርሃት ስሜት ይታይባቸዋል።
በባህርይ፡ ይህ ለውጥ በእድሜ ደረጃ ቢለያይም ሕጻናት ከወላጅ ወይም ከተንከባካቢ ጋር ባልተለመደ ሁኔታ የመጣበቅ ወይም መለየት አለመፈለግ ይታይባቸዋል። በተቃራኒው ደግሞ እድሜያቸው ከፍ ባሉት ለብቻቸው መሆን መፈለግ ይስተዋላል።
እድሜያቸው እስከ ስድስት ዓመትና ከዚያ በላይ ያሉት ሕጻናት ደግሞ ለብቻ መተኛት ይፈራሉ። መመገብ፣ መጠጣት፣ መተኛት ይቸገራሉ። ቅዠት፣ ሽንትና ሰገራን መቆጣጠር አለመቻል ዓይነት ከአካል ጋር የተያያዙ ችግሮችም ይታይባቸዋል።
በአስተሳሰብ፡ መርሳት ያጋጥማቸዋል፤ ትኩረት ለማድረግ ይቸገራሉ።
. በረዥም ጊዜ
በረዥም ጊዜ በአብዛኛው የሚታየው የባህርይ ችግር ነው።
በባህርይ፡ የሱስ ተገዥ መሆን ፣ የአልኮል ተጠቂ መሆን፣ ወጣት ጥፋተኝነት ከዚህም ሲያልፍ በጎልማሳነት ዘመናቸው ወንጀለኛ የመሆን እድላቸው ከፍተኛ ነው። ያዩትን ወይም የደረሰባቸውን ነገር እነርሱም ሲያደርጉት ሊገኙም ይችላሉ።
በአስተሳሰብ፡ የትምህርት ስኬት ላይ አነስተኛ መሆን
በስሜት፡ የሃዘን ስሜት፣ ተስፋ መቁረጥ እና ዋጋ የለኝም የሚል ስሜት ይስተዋልባቸዋል።
ከዚህ አስከፊ የሆኑ ምልክቶችም ሊታይባቸው ይችላል። እነዚህ ምልክቶች ታዲያ ቶሎ እርምጃ ለመውሰድና መፍትሔ ለመፈለግ እንደሚረዱ አቶ ሞገስ ይናገራሉ።
እዚህ ደረጃ ላይ የደረሱት ሕጻናት ሌላ ሰው ያላየው፣ ያልሰማውና ያልሸተተው ለእነርሱ ሊታያቸው፣ ሊሰማቸውና ሊሸታቸው ይችላል። ጉዳቱ ሲደርስ የሰሙት ድምፅ፣ ሽታ ወይም ያዩት ነገር ተመልሶ ይመጣባቸዋል።
ወይም በሌላ ሽታና ዕይታ ቅርፁን ቀይሮ ሊከሰት ይችላል።
ይህ ከፍ ባለ የእድሜ ክልልም ሊታይ ይችላል።
የሚያጋጥማቸው የአዕምሮ ጤና ችግር ምንድን ነው?
ባለሙያው እንደሚሉት እነዚህ ሕጻናት ከሥነ ልቦና ቁስለት ጋር በተያያዘ ለሚታይ ከፍተኛ የአዕምሮ ጤና ችግር [Post Traumatic Disorder] ይጋለጣሉ።
ይህ ችግር ሥር እየሰደደ ሲመጣም ድባቴ፣ ጭንቀት እና እስከ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ የአዕምሮ ህመም -እብደት ደረጃ ሊደርስ ይችላል።
በባህርይም፣ በስሜትም፣ በአስተሳሰብም ሆነ በመስተጋብር የዕለት ከዕለት ሥራቸውን ማከናወን አይችሉም።
ከዚህ ችግር እንዴት መውጣት ይችላሉ?
አቶ ሞገስ እነዚህ የሥነ ልቦና ችግሮች ልጆች ላይ እንዳይከሰቱ መከላከል ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው ይላሉ።
ጥቃት ሲፈፀም በማየታቸው ደህንነታቸው ጥያቄ ውስጥ ስለሚገባም ያንን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።
"በድጋሜ ተጋላጭ እንዳይሆኑ ጥበቃ ማድረግ፣ ከፍተኛ የስሜት ጫና ውስጥ ስለሚሆኑ ያንን በማቃለል ጉዳቱን መቀነስ ይቻላል" ይላሉ ባለሙያው።
እንዲህ ዓይነት አጋጣሚ እንደሚያጋጥም መንገርና ማረጋገጫ መስጠት እንደሚያስፈልግም ያክላሉ።
ይሁን እንጂ ባለሙያው እንዳሉት የስሜት ደህንነታቸው ማረጋገጥ የሚቻለው የደህንነት ሁኔታቸው ሲረጋገጥ ነው።
ስሜት በአዎንታዊም በአሉታዊም መልኩ ስለሚጋባ ተንከባካቢዎቻቸው ያለባቸውን የስሜት ጫና የመቋቋም አቅማቸውን ማሳደግም ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ባለሙያው ይመክራሉ።
የሕጻናቱን ስሜትና ባህርይ መከታተል፣ እንዲያወሩ መፍቀድና ለከፍተኛ የሥነ ልቦና ቀውስ የሚደርሱ ከሆነም ባለሙያ ማማከር ያስፈልጋል።
"ብዙ ጊዜ ጥቃቶችና ግጭቶች ሲያጋጥሙ መሰረታዊ ፍላጎቶች ላይ እንጂ ሥነ ልቦናዊ ቁስሉን የሚያይ የለም" የሚሉት አቶ ሞገስ፤ ይህ ችግር የተደበቀና በቀላሉ የሚታይ ስላልሆነ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ይናገራሉ።
የዓለም ጤና ድርጅት የአፍላ ወጣቶችን የአዕምሮ ጤና በተመለከተ ባለፈው ዓመት በድረ ገጹ ላይ ያስቀመጣቸው ጥሬ ሀቆች የሚያሳዩት የታዳጊዎች የአዕምሮ ጤና ችግር አሳሳቢ መሆኑን ነው።
እነዚህን ችግሮች ለመቀነስ የባለሙያ እገዛ በሌለበት አገር በቀል መፍትሔዎችን ማሰብ ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ ባለሙያው ይናገራሉ።
ለዚህም እንደ እድር፣ ማሕበርና የቡና ዝግጅት ያሉ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ድጋፎችን ማሳደግ ያስፈልጋል።
በማውራትና በመነጋገር አንዱ በአንዱ እንዲሽር ለማድረግ እነዚህ ባህላዊ ክንውኖች ያላቸው አስተዋፅኦ የሚናቅ እንዳልሆነ ባለሙያው ያሰምሩበታል።
"ሩዋንዳና ደቡብ አፍሪካን በፈታኝ ጊዜዎቻቸው የረዳቸው ይህ ባህላዊ ዘዴ ነው" ሲሉ ምሳሌ ያጣቅሳሉ።
"በሥነ ልቦና ቁስል እሽክርክሪት ውስጥ ነው ያለነው"
ጥናቶች እንደሚያሳዩት ፈጣን የሆነ የአዕምሮ እድገት የሚካሄደው በሕጻንነት የእድሜ ክልል ነው። በመሆኑም የወደፊት የአዕምሮ ጤናቸውን የሚወስነውን እውቀት፣ ማሕበራዊና ስሜታዊ ክህሎት የሚቀስሙት በዚህ እድሜ ነው።
ልጆች የሚያድጉበት አካባቢም በደህንነታቸውና በእድገታቸው ላይ ወሳኝ ነው።
በቤት ውስጥ፣ በትምህርት ቤት ወይም በሌላ ቦታ የሚያዩት አሉታዊ ድርጊት ለአዕምሮ ህመም የመጋለጥ እድላቸውን እንደሚጨምረው ጥናቶቹ ያመለክታሉ።
ይህንን አቶ ሞገስም በሥራ ልምዳቸው ያረጋገጡት ነው።
"የዛሬ ፍርሃት፣ ጭንቀትና ግጭት አብዛኛው በልጅነት ያሳለፍነው ቁስል መገለጫ ነው" ይላሉ።
ባለሙያው እንደሚሉት ይህ ቁስል በወቅቱ ባለመታከሙ በጉልምስና ወቅት ተንጠባጥቦ ይገኛል። ይህም በትዳር ሕይወት፣ በመሥሪያ ቤት እንዲሁም በአካባቢ ላይ ይገለጻል።
"በሥነ ልቦና 'ቁጣ ቁጣን ይወልዳል' ይባላል" የሚሉት አቶ ሞገስ፤ እነዚህ ሕጻናት ያዩት፣ ሰው በአሰቃቂ ሁኔታ ሲደፈር፣ ሲገደል ወይም ራሳቸው ላይ ሲደርስ በመሆኑ አዕምሮ ደግሞ ይህን እንደሚለማመድ ይናገራሉ። የተለመደ ያደርገዋል።
በዚህም ምክንያት እነዚህ ሕጻናት የቤተሰብ፣ የመሥሪያ ቤት ወይም የአገር መሪ ሲሆኑ የሚደግሙት ይህንኑ ይሆናል ይላሉ።
"ኢትዮጵያ የሥነ ልቦና ቁስል እሽክርክሪት ውስጥ ነው ያለችው" የሚሉት ባለሙያው፤ ይህንን በጊዜ በማስቆምና በማከም አዙሪቱን መቁረጥ እንደሚያስፈልግ መክረዋል።
















