ትግራይ፡ ኢትዮጵያ ሠራዊት ግድያ መፈጸሙን ማስረጃዎች አመለከቱ

በወታደሮቹ የተያዙት የሲቪል ልብስ የለበሱ ሰዎች ከግድያው በፊት
የምስሉ መግለጫ, በወታደሮቹ የተያዙት የሲቪል ልብስ የለበሱ ሰዎች ከግድያው በፊት

የቢቢሲ 'አፍሪካ አይ' ፕሮግራም ባደረገው ምርመራ በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጸመ አንድ ጭፍጨፋ በኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት መፈጸሙን የሚያመለክቱ ማስረጃዎች አግኝቷል። በዚህም ቢያንስ 15 ወንዶች የተገደሉበትን ትክክለኛውን ቦታ ለመለየት ችሏል።

የታጠቁና የወታደር የደንብ ልብስ የለበሱ ሰዎች ያልታጠቁ ወንዶችን ከአንድ የገደል አፋፍ ላይ በመውሰድ አንዳንዶቹን ላይ በቅርብ ርቀት በመተኮስ አስከሬኖችን ወደ ገደል ገፍተው ሲጨምሩ የሚያሳይ ቪዲዮ በየካቲት ወር መጨረሻ ላይ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ታይቶ ነበር።

ቢቢሲ ይህ ድርጊት የተፈጸመው የኢትዮጵያ ሠራዊት የህወሓት ኃይሎችን እየተዋጋ ባለበት ትግራይ ክልል ውስጥ ማኅበረ ዴጎ ከተባለች ከተማ አቅራቢያ መሆኑን አረጋግጧል።

ቢቢሲ ያገኛቸውን ማስረጃዎች ለኢትዮጵያ መንግሥት በማቅረብ ምላሽ የጠየቀ ሲሆን መንግሥት "በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የወጡ ነገሮችና ክሶች እንደ ማስረጃ ሊወሰዱ አይችሉም" በማለት "ገለልተኛ ምርመራዎችን ለማካሄድ የትግራይ ክልል ክፍት ነው" ሲል መልሷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው እንደተናገሩት፣ ትግራይ ውስጥ በኢትዮጵያ ሠራዊት ተፈጸሙ ስለተባሉት ጥፋቶች አስፈላጊው ምርመራ ተደርጎ አጥፊዎች በሕግ እንደሚጠየቁ መናገራቸው ይታወሳል።

ትግራይ ውስጥ ግጭቱ የተቀሰቀሰው የህወሓት ኃይሎች በመንግሥት ጦር ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ካዘዙ በኋላ ነበር። ህወሓትም የጠቅላይ ሚኒስትሩን እርምጃ በመቃወም "ትግሉን እንደሚቀጥል" ገልጾ ነበር።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዳለው ግጭቱ አስካሁን ድረስ ከሁለት ሚሊዮን ሰዎች በላይ እንዲፈናቀሉ ያደረገ ሲሆን፤ ከአራት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑትን ደግሞ የሰብአዊ እርዳታ እንዲጠብቁ አድርጓቸዋል።

የአካባቢው መልክአ ምድር በከፊል
የምስሉ መግለጫ, የአካባቢው መልክአ ምድር በከፊል
ቪዲዮው ላይ የተያው አካባቢ ከሳተላይት ከተገኘ ምስል ጋር ሲመሳከር
የምስሉ መግለጫ, ቪዲዮው ላይ የተያው አካባቢ ከሳተላይት ከተገኘ ምስል ጋር ሲመሳከር

ቪዲዮው የተቀረጸበትን ሥፍራ መለየት

የቢቢሲ 'አፍሪካ አይ' የምርመራ ጋዜጠኞች ቡድን፤ ቤሊንግካት እና ኒውሲ ከተባሉ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ተንታኞች ጋር በመሆን ጭፍጨፋው የተፈጸመበትን ሥፍራ ለመለየት የተለያዩ ተግባራት አከናውኗል።

ቪዲዮውን በመጀመሪያ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያወጡት ሰዎች ምስሉ የተቀረጸው ማኅበረ ዴጎ ከተባለ ቦታ አቅራቢያ መሆኑን ገልጸው ነበር። አፍሪካ አይም ጥርጊያ መንገድን፣ ኮረብታዎችን፣ ገደላማ ቦታዎችን ለየት ከሚያደርጋቸው ሁኔታና የከተማዋ አቅራቢያ የሚያሳዩ የሳተላይት ምስሎችን ጨምሮ በቪዲዮው ላይ የሚታዩትን መልክአ ምድራዊ ገጽታዎችን መርምሯል።

የታጠቁት ወታደሮች የጥላ አቅጣጫና ርዝመት ድርጊቱ የተፈጸመበትን ሰዓት ለመለየት የረዳ ሲሆን፤ የገደላማ አካባቢው ከሰሜን ወደ ደቡብ የተዘረጋ በመሆኑ የአፍሪካ አይ ቡድን ትክክለኛውን ቦታ ለማወቅ አስችሎታል።

በቪዲዮው ላይ የተራሮችን ቅርጽ ተከትሎ መስመር በማስመር የአካባቢውን መልክአ ምድር በሚያሳይ የማመሳከሪያ ካርታ ላይ ተመሳሳይ መስመር ሲሰመር አንድ ዓይነት መሆናቸው ተረጋግጧል። በአካባቢው ያለ የደረቀ የወንዝ መውረጃ መስመር፣ እጽዋቶችና የዛፎች አቀማመጥ በተጨማሪ ስፍራውን ለመለየት ጠቅመዋል።

ቢቢሲ አንድ የማኅበረ ዴጎ ነዋሪን በስልክ ያነጋገረ ሲሆን፤ እሱም የኢትዮጵያ ሠራዊት በጥር ወር ላይ ሦስት ዘመዶቹን ጨምሮ 73 ሰዎችን ከከተማው ይዘው መውሰዳቸውን ገልጾ ሰዎቹ እሰካሁን የት እንዳሉ እንደማይታወቅ ተናግሯል።

በተጨማሪም በከተማዋ አቅራቢያ በምትገኝ መንደር ውስጥ ነዋሪ የሆነ ሌላ ግለሰብ ወንድሙ በጭፍጨፋው ከተገደሉት መካከል እንደሆነ ለቢቢሲ ገልጿል። ግድያው የተፈጸመው ጥር ወር ላይ ማኅበረ ዴጎ ውስጥ እንደሆነም አስረድቷል።

"ከገደሉ አፋፍ ላይ ነበር የገደሏቸው" ብሏል።

ከቪዲዮ ላይ ከተገኘ ምስል ጋር ሲመሳከር
የምስሉ መግለጫ, ከቪዲዮ ላይ ከተገኘ ምስል ጋር ሲመሳከር
በአካባቢው ያለው በእጸዋት የተሸፈነ ቦታ ከሳተላይ ምስል ጋር ሲመሳከር
የምስሉ መግለጫ, በአካባቢው ያለው በእጸዋት የተሸፈነ ቦታ ከሳተላይ ምስል ጋር ሲመሳከር

ወታደሮቹንና የሞቱትን ሰዎች መለየት

አፍሪካ አይ በቪዲዮው ላይ የሚታዩትን የታጠቁ ወታደሮች ማንነት ለማረጋገጥ ባይችልም፤ ከለበሱት የደንብ ልብስና የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ቀለም ያለው በክንዳቸው ላይ ያረፈ አርማን በማየት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከሚለብሰው የደንብ ልብስ ጋር ተመሳሳይ ሆኖ አግኝቶታል።

በደንብ ልብሱ ላይ ያለው የስፌት አይነትና ኪሶቹም ከኢትዮጵያ ሠራዊት ልብስ ጋር ይመሳሰላሉ። ከመካከላቸው አንደኛው ያደረገው አረንጓዴ ኮፍያና ላዩ ላይ ያለው አርማ ሠራዊቱ ከሚጠቀመው ጋር የቀረበ መመሳሰል አለው።

ወታደሮቹ የሚነጋገሩት በአማርኛ ሲሆን በቪዲዮዎቹ ላይ መሬት ላይ እንዲቀመጡ ከተደረጉት ካልታጠቁት ሰዎች ዙሪያ ቆመው እርስ በርስ ሲያወሩ ይሰማሉ።

"እነዚህን ሰዎች መልቀቅ የለብንም። አንዳቸውም መትረፍ የለባቸውም" ይላል አንድ ለካሜራው የቀረበ ድምጽ።

"እንዴት እንደሞቱ የሚያሳይ ቪዲዮ መቅረጽ አለብን" ይላል ሌላኛው ድምጽ።

ሌሎች ቪዲዮዎች ደግሞ ያልታጠቁት ሰዎች መሳሪያ ተደግኖባቸው ወደ ገደሉ ጫፍ ሲወሰዱና የታጠቁት ሰዎች በርካታ እስረኞችን ሲገድሉና አስከሬናቸውን ወደ ገደሉ ሲጥሉ ያሳያሉ።

በቪዲዮው አንዳንድ ክፍሎች ላይ ታጣቂዎቹ ተጠግተው አስከሬኖቹ ላይ ሲተኩሱ የሚታይ ሲሆን በሌላ ላይ ደግሞ ሟቾቹን ሲሳደቡና ሲሳልቁባቸው ይሰማል።

"ጋዝ አርከፍክፈን ማቃጠል ብንችል ደስ ይለኛል" ይላል ለካሜራው የቀረበው ድምጽ።

"እነዚህን ሰዎች ለማቃጠል ጋዝ ቢኖር ኖሮ ጥሩ ነበር" በማለት ሌላኛው ድምጽ ይመልሳል። "እንደ ሕንዶች አስከሬናቸውን ማቃጠል ነበር።"

የሲቪል ልብስ ለብሰው የሚታዩትና የተገደሉት ሰዎች ማንነት አይታወቅም። በታጣቂዎቹ የተያዙት ሰዎች በትግርኛ ሲነጋገሩ የሚሰሙ ሲሆን በቪዲዮው ላይ ወታደሮቹ የያዟቸው ሰዎች የህወሓት አባላት እንደሆኑ እንደሚያምኑ አመላካች ነገሮች አሉ።

"ይህ የወያኔ መጨረሻ ነው" ሲል ከታጣቂዎቹ መካከል አንዱ ይሰማል።

"ምህረት የለንም።"

የሂዩማን ራይትስ ዋች የአፍሪካ ቀንድ ኃላፊ የሆነችው ላቲሻ ባደር ለቢቢሲ እንደተናገረችው በቅርብ ወራት ውስጥ በክልሉ "በጣም ከፍተኛ የመብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን" ታዛቢዎች መመልከታቸውን ገልጻ፤ ነገር ግን ይህ ቪዲዮ "በተለይ አስደንጋጭ" ነው ብላለች።

"በቁጥጥር ስር የዋሉ ያልታጠቁ ሰዎች ሲገደሉ አይተናል" ያለችው ላቲሻ "በቪዲዮዎቹ ላይ የተመለከትናቸው ነገሮች የጦር ወንጀል ሊሆኑ ስለሚችሉ ክስተቱ ተጨማሪ ምርመራን የሚፈልግ ነው" ስትል ገልጻለች።

በኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት የሚለብሱት የደንብ ልብስና አርማ በቪዲዮው ላይ ካለው ጋር ይመሳሰላል
የምስሉ መግለጫ, በኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት የሚለብሱት የደንብ ልብስና አርማ በቪዲዮው ላይ ካለው ጋር ይመሳሰላል