ትግራይ ፡ "ወታደሩ እንዳይደፍረኝ ስታገል ቀኝ እጄን አጣሁ"

ትግራይ ፡ "ወታደሩ እንዳይደፍረኝ ስከላከል ቀኝ እጄን አጣሁ"

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ለዚህ ዘገባ ሲባል ስሟን የማንጠቅሰው የ18 ዓመት ወጣት ከሁለት ወራት በላይ ሆስፒታል ውስጥ ሕክምና ተከታትላለች።

አንድ ወታደር ሊደፍራት ሲሞክር ራሷን ለማዳን ስትጣጣር ቀኝ እጇን እንዳጣች ለቢቢሲ ገልጻለች። ወታደሩ የወጣቷ አያት እንዲደፍሯት ለማድረግ መሞከሩንም ተናግራለች።

በትግራይ ክልል የተከሰተው ግጭት የእሷንና የሌሎችም የእድሜ እኩዮቿን ሕልም ቀጥፏል። አብዛኞቹ ቤታቸውን ጥለው በተራሮች ሥር ለመደበቅ ተገደዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መቀለን እንደተቆጣጠረ መግለጹን ተከትሎ እጅ አንሰጥም ያሉ የህወሓት አመራሮች እና አባላትን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ዘመቻ ተከፍቷል።

በዚህ ወቅት በትግራይ ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመ ነው የሚሉ ክሶች እየተሰሙ ነው። መንግሥት እነዚህን ክሶች አጣጥሏል።

ቢቢሲ ያነጋገራት ወጣት እና አያቷ ከትውልድ ቀያቸው አቢ አዲ መውጣት ስላልቻሉ ነበር ባሉበት የቆዩት።

ኅዳር 3 ቀን 2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መለያ ያደረገ ወታደር ቤታቸው እንደገባ ታስታውሳለች። ወታደሩ የትግራይ ተዋጊዎችን የት ናቸው? ሲል ጠይቋቸው ቤቱን መበርበር ጀመረ።

ቤቱ ውስጥ ማንንም ሳያገኝ ሲቀር ወጣቷና አያቷ አልጋ ላይ እንዲተኙ በማዘዝ በዙሪያቸው መተኮስ እንደጀመረ ትናገራለች።

"ከዚያም አያቴ ከእኔ ጋር እንዲተኛ አዘዘው። አያቴ በጣም ተቆጣ። መደባደብ ጀመሩ" ስትል ታስታውሳለች።

ወታደሩ አያቷን ከቤት አስወጥቶ ትከሻቸውና ታፋቸው ላይ ከተኮሰ በኋላ እንደሞቱ አስቦ ወደ ቤት ተመልሶ ገባ።

"'አሁን ማንም አያድንሽም። ልብስሽን አውልቂ' አለኝ። 'እባክህ ተው' ብዬ ብለምነውም ደጋግሞ በቡጢ መታኝ።"

ለበርካታ ደቂቃዎች ታግለዋል። ምንም እንኳን የወታደሩ ድብደባ ከባድ ቢሆንም እራሷን ለመከላከል ትታገለው ነበር። በስተመጨረሻ ሽጉጡን እንደደገነባትም ትናገራለች።

"ቀኝ እጄን ሦስት ጊዜ በጥይት መታኝ። እግሬ ላይም ሦስት ጊዜ ተኮሰ። ከውጪ የተኩስ ድምጽ ሲሰማ ቤቱን ጥሎ ወጣ።"

የወጣቷ አያት ሕይወታቸው አላለፈም ነበር። ሁለቱም ከፍተኛ ጉዳት ቢደርስባቸውም ከቤት ወጥተው እርዳታ ለመጠየቅ ድፍረቱን አላገኙም።

'ፍትሕ የለም'

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በግጭት ወቅት የሚከሰቱ ወሲባዊ ጥቃቶችን የሚመለከተው ቡድን መሪ ፕሪሚላ ፓተን "የቤተሰብ አባል እንዲደፍሩ የተገደዱ ሰዎች እንዳሉ የሚጠቁሙ የሚረብሹ ሪፖርቶች ሰምተናል" ሲሉ ተናግረዋል።

አንዳንድ ሴቶች የተለያዩ መሠረታዊ መገልገያዎችን ለማግኘት ከወታደሮች ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት ለመፈጸም እንደተገደዱ የሚጠቁም ሪፖርት እንደደረሰውም የተባበሩት መንግሥታተ ድርጅት ገልጿል።

ፕሪሚላ ፓተን እንዳሉት፤ የሕክምና መስጫ ተቋሞች ድንገተኛ የወሊድ መከላከያ እንክብል ግዢ ቁጥር እንደጨመረ አስታውቀዋል።

በወሲብ የሚተላለፉ በሽታዎች ምርመራ የሚያደርጉ ሴቶች ቁጥር መጨመሩንም አክለው፤ ይህም በግጭቱ ወቅት ወሲባዊ ጥቃት ስለመድረሱ ጠቋሚ ነው ብለዋል።

በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ ሦስት ተቃዋሚ የፓለቲካ ፓርቲዎች የዘፈቀደ ግድያ እንዲሁም በቡድን የሚፈጸም መድፈር "የዕለት ከዕለት ክስተት ሆኗል" ሲሉ መግለጫ አውጥተዋል። ፓርቲዎቹ አንድ አባት መሣሪያ ተደግኖበት ልጁን እንዲደፍር መገደዱን እንደ ማሳያ ጠቅሰዋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ሐኪም እና የሴቶች መብት ተሟጋች ቡድን አባል ጥር ላይ ለቢቢሲ በሰጡት መረጃ መሠረት፤ ቢያንስ 200 የሚደርሱ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሴቶች መደፈራቸውን በመቀለ በሚገኙ የተለያዩ ሆስፒታሎችና የጤና ተቋሞች ሪፓርት አድርገዋል።

አብዛኞቹ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ጥቃት አድራሾቹ የኢትዮጵያ መከላከያ መለያ የለበሱ እንደሆኑና ጥቃቱ ከደረሰባቸው በኋላ ወደ ሕክምና መስጫ እንዳይሄዱ እንዳስፈራሯቸው ተናግረዋል።

"ሰውነታቸው ላይ ጠባሳ አለ። አንዳንዶቹ የተደፈሩት በቡድን ነው። አንድ ሴት ለሳምንት ታግታ ተደፍራለች። ራሷን እንኳን አታውቅም። ፓሊስ የለም። ፍትሕም የለም" በማለት ያናገርናቸው ሐኪም ገልጸዋል።

የሴቶች መብት ተሟጋች ቡድን አባል "ከተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች በጣም የሚያስደነግጡ ታሪኮች ሰምተናል። የትራንስፖርት እጥረት ስላለ ልንረዳቸው አልቻልም። እጅግ ያሳዝናል" ብለውናል።

በመቀለ በሚገኝ ሆስፒታል የሚሠሩ ባለሙያ እንደሚሉት፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በየቀኑ አምስት ወይም ስድስት ሴቶች ወደ ሆስፒታሉ ሄደው መደፈራቸውን ገልጸዋል። እነዚህ ሴቶች ድንገተኛ የወሊድ መከላከያ እንክብልና ጸረ ኤችአይቪ መድኃኒትም ከባለሙያዎች ጠይቀዋል።

ይሆኖ የተባለው የሴቶች መብት ተሟጋች ቡድን አባል ወይኒ አብርሃ እስከ ታህሳስ መጨረሻ ድረስ መቀለ ነበረች። ሴቶችን መድፈር የውጊያ መሣሪያ እየሆነ ነው ትላለች።

"መቀለ ውስጥ ብዙ ሴቶች ተደፍረዋል። ይህ እየተደረገ ያለው የሰውን ሞራል ለመስበርና አስፈራርቶ ትግሉን እንዲያቆሙ ለማስገደድ ነው።"

የጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹም ጀነራል ብርሃኑ ጁላ እነዚህን ክሶች አጣጥለዋል።

"መከላከያ ኃይላችን አይደፍርም። ሽፍታ አይደለም። የመንግሥት ኃይል ነው። የመንግሥት ኃይል ደግሞ ሥነ ምግባርና ሕግጋት አለው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አዲሱ የመቀለ ከንቲባ አቶ አታክልቲ ኃይለሥላሴ፤ የመብት ተሟጋች ቡድኖች የጠቀሱት ቁጥር እጅግ የተጋነነ ነው ይላሉ።

በቅርቡ ከሴቶች እና ሕጻናት፣ ዐቃቤ ሕግ እንዲሁም ከጤና ሚንስትር የተውጣጣ ቡድን የወሲባዊ ጥቃት ክሶችን እንዲያጣራ ወደ ትግራይ ተልኳል።

የቡድኑ ሙሉ የምርመራ ውጤት ገና ይፋ ባይደረግም፤ ቡድኑ ሰዎች መደፈራቸውን አረጋግጧል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባለፈው ሳምንት ያወጣው መግለጫ፤ ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ በመላው ትግራይ 108 የመደፈር ሪፓርቶች እንደተመዘገቡ ይጠቁማል።

በሪፓርቱ መሠረት፤ ፓሊስና የሕክምና መስጫ ተቋሞች መደበኛ አገልግሎት እየሰጡ ባለመሆኑ ወሲባዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች ሪፖርት ለማድረግ ተቸግረዋል።

'መሀንዲስ መሆን እፈልግ ነበር'

የ18 ዓመቷ ወጣት ቀኝ እጇን ካጣች በኋላ ጉዳዩን ለቢቢሲ የገለጹ ዶክተር እንዳሉት፤ ወጣቷና አያቷ በኤርትራ ወታደሮች ጥቃት ከደረሰባቸው ከሁለት ቀናት በኋላ እንዴት እንደተረፉ ነግረዋቸዋል።

የኢትዮጵያ እንዲሁም የኤርትራ መንግሥት የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ እንደሌሉ ቢናገሩም፤ ወጣቷና አያቷ በኤርትራውያን ወታደሮች ጥቃት እንደደረሰባቸው ገልጸዋል።

የኤርትራ ወታደሮች የወጣቷና አያቷን ቁስል ጠግነው ለኢትዮጵያ ወታደሮች እንዳስረከቧቸውና ወደ መቀለ ሆስፒታል እንደተወሰዱ አክለዋል።

አያትየው አሁን ላይ ከጉዳቱ እያገገሙ ነው። የልጅ ልጃቸው ግን እጇን ስላጣች አሁንም የሕክምና ክትትል ያስፈልጋታል። እግሯ አሁንም በፋሻ እንደተጠቀለለ ነው።

ወጣቷን ቢቢሲ ያናገራት ሆስፒታል ሳለች ነው። ሕልሜ ተቀጨ እያለች ታነባ ነበር።

ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ዩኒቨርስቲ ገብታ ምህንድስና ማጥናት ነበር ሕልሟ። ተምራ፣ ሥራ ይዛ እናቷ ከሞቱ ጀምሮ ያሳደጓት አያቷን መጦር ትመኝ ነበር።

አያቷ ሆስፒታል የተኛችበት አልጋ አጠገብ ሆነው ስታለቅስ ያጽናኗታል። እሷ ግን "እንዴት ልሆን ነው? መሆን የምመኘውን ሳልሆን ቀረሁ" ስትል ማንባቷን ቀጥላለች።