ትራምፕ የአሜሪካ ወታደሮች ከሶማሊያ እንዲወጡ አዘዙ

የአሜሪካ ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ወታደሮች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ከሶማሊያ እንዲወጡ አዘዙ።

ፔንታጎን እንዳለው፤ ወታደሮቹ ከጥር 15 በኋላ ሶማሊያን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ተላልፏል።

በአሁኑ ጊዜ የአል-ሸባብ እና የአይኤስ ታጣቂዎችን በመዋጋት ረገድ ድጋፍ የሚሰጡ ወደ 700 የሚጠጉ የአሜሪካ ወታደሮች ሶማሊያ ውስጥ ይገኛሉ።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት እንደተናገሩት፤ አንዳንዶቹ የአሜሪካ ወታደሮች ወደ ተለያዩ የሶማሊያ ጎረቤት አገሮች በመሻገርም ድጋፍ ሲሰጡ ቆይተዋል።

ከዚህ ቀደም ትራምፕ ለዓመታት የቆዩት የአሜሪካ ወታደሮች ከኢራቅ እና አፍጋኒስታን እንዲወጡ ባለፈው ወር ማዘዛቸው ይታወሳል።

በተለያዩ አገሮች የአሜሪካ ወታደሮች መሰማራታቸው ለከፍተኛ ወጪ እንደዳረጋቸው እና ውጤት አልባ እንደሆነም ትራምፕ ይናገራሉ። ወታደሮቹ ወደ አሜሪካ እንዲመለሱ ሲወተውቱም ነበር።

ተሰናባቹ ፕሬዘዳንት ትራምፕ ሥልጣናቸውን በይፋ ለባይደን ከማስረከባቸው በፊት ነው የአሜሪካ ወታደሮች ከሶማሊያ እንዲወጡ ያዘዙት።

ወታደሮቹ ከሶማሊያ መውጣታቸው ተጽዕኖ ይኖረዋል?

የአሜሪካ የቀድሞው የመከላከያ ሚንስትር ፀሐፊ ማርክ ኤስፐር ወታደሮቹ ሶማሊያ እንዲቆዩ ይፈልጉ ነበር። እኚህ ባለሥልጣን ባለፈው ወር ከሥራ የተባረሩ ሲሆን፤ የትራምፕ ውሳኔ የፀሐፊውን አቋም የሚጻረር ነው።

ፔንታጎን ያወጣው መግለጫ እንደሚለው፤ አብዛኛውን የአሜሪካ ወታደራዊ ኃይሎች ከሶማሊያ ማስወጣት ከአሜሪካ የፖሊሲ ለውጥ ጋር አይገናኝም።

"ለአገራችን ስጋት የሚሆኑ ጽንፈኛ ኃይሎችን በመዋጋቱ እንቀጥልበታለን። ስትራቴጂያዊ ጥቅማችንን በማስከበር እና በኃይል አሰላለፉ ያለንን ቦታ በማስጠበቁም እንቀጥላለን" ይላል መግለጫው።

ፔንታጎን እንዳለው፤ ሶማሊያ ውስጥ የሚቀሩ ወታደራዊ ኃይሎች መቀመጫቸው ሞቃዲሹ ትሆናለች።

ተንታኞች እንደሚሉት፤ የአሜሪካ ወታደሮች ከሶማሊያ መውጣታቸው በምሥራቅ አፍሪካ የተንሰራፋውን የጽንፈኛ ታጣቂዎችን ስጋት ያባብሰዋል።

ባለፈው ወር የአሜሪካ መንግሥት አማካሪዎች ወታደሮቻቸው ከሶማሊያ መውጣት የለባቸውም ብለው መክረው ነበር።

ያለ አሜሪካ ወታደሮች እገዛ በቀጠናው ያሉ ታጣቂዎችን ለመግታት አዳጋች እንደሚሆንም አስጠንቅቀዋል።

የሶማሊያ ባለሥልጣናት፤ የአሜሪካ ወታደሮች ከአካባቢው ከወጡ ቀውስ እንደሚከሰትና ሽብርተኞች እንደሚበረታቱ አመልክተዋል።

ውሳኔው ላይ እንዴት ተደረሰ?

ለአስርት ዓመታት በፖለቲካዊ ቀውስ ስትናጥ በነበረችው ሶማሊያ፤ የአፍሪካ ኅብረት እና የአሜሪካ ወታደሮች ተጣምረው ሞቃዲሹን መቆጣጠር ችለዋል።

ከሞቃዲሹ በተጨማሪ ሌሎችም በአል-ሸባብ ይዞታ ስር የነበሩ ግዛቶችን አስለቅቀዋል።

እአአ በ1993 ሞቃዲሹ ውስጥ 18 የአሜሪካ ልዩ ኃይል ወታደሮች ከታጣቂዎች ጋር ሲዋጉ መገደላቸውን ተከትሎ፤ የተለያዩ የአሜሪካ ፕሬዘዳንቶች በሶማሊያ ጣልቃ ላለመግባት ሲያንገራግሩ ቆይተዋል።

ዶናልድ ትራምፕ 2016 ላይ የምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርጉ አሜሪካን "ማቆሚያ ከሌለው ጦርነት" ለማውጣት ቃል ገብተው ነበር።

ሆኖም ግን በዋነኛነት የአየር ድብደባ በማድረግ ከአል-ሸባብ ጋር የሚደረገውን ፍልሚያ ገፍተውበታል።

ባለፈው ወር የአሜሪካ መከላከያ ባለሥልጣኖች ወታደሮች ከኢራቅ እና አፍጋኒስታን እንዲቀነሱ አስታውቀዋል።

በዚህ መሠረት፤ አፍጋኒስታን የሚገኙ ወታደሮች ከ5,000 ወደ 2,500 ይቀነሳሉ። ኢራቅ ያሉ ወታደሮች ቁጥር ደግሞ ከ3,000 ወደ 2,500 ይወርዳል ተብሏል።