ዶናልድት ትራምፕ ስለ ሶማሊያ የተሳሳቱት ምንድነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጋዜጠኛ ኢስማኢል ኢይናሼ ሶማሊያ በማያገባት የአሜሪካ ምርጫ እሰጥ-አገባ ውስጥ ገብታለች ይላል።
ለምን? እንዴት? - ኢስማኢል እንዲህ ያስረዳል።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ሶማሊ-ኤሜሪካዊቷ ፖለቲከኛ ኢልሃን ኦማር ላይ ጥርስ ከነከሱ ሰንበትበት ብለዋል። በተለይ ደግሞ የአሜሪካ ምርጫ መቃረቡን ተከትሎ ስለእሷ ክፉ ሲያወሩ ተደምጠዋል።
ነገር ግን ትራምፕ በፖለቲካ ተቀናቃኛቸው የተገቱ አይመስሉም። የፖለቲከኛዋን የትውልድ አገርንም በነገር እየጎሸሙ ነው።
በቅርቡ እንኳ በኦክላሆማ ግዛት ተልሳ ከተማ በነበራቸው የምርጫ ቅስቀሳ የ37 ዓመቷን ፖለቲከኛ አሜሪካ ልክ እንደ ሶማሊያ "እንደትረበሽ" ትፈልጋለች ሲሉ ወንጅለዋል።
"አገራችንን ልክ እንደ መጣችበት አገር ሶማሊያ አስደተዳደር ማድረግ ትሻለች። መንግሥት የሌለበት፣ ደህንነት ያልተጠበቀበት፣ ፖሊስ የማይታይበት፤ ረብሻ ብቻ እንዲሆን ነው የምትፈልገው። እዚህ መጥታ አገር እንዴት እንደሚመራ ልታስተምረን ትፈልጋለች። ይቅርብን እናመሰግናለን።"
በአውሮፓውያኑ 1995 ከሶማሊያ ተሰዳ በልጅነቷ አሜሪካ የገባችው ኢልሃን ኦማር የሚኒሶታ ግዛት የኮንግረስ ተወካይ ናት። ሚኒያፖሊስ ከሚኒሶታ ግዛት ከተሞች አንዷ ናት። ከተማዋ ከጆርጅ ፍሎይድ ግድያ በኋላ ብላክ ላይቭስ ማተር [የጥቁሮች ሕይወት ዋጋ አላት] የተሰኘው እንቅስቃሴ እንደ አዲስ የተቀሰቀሰባት ናት።
ነገር ግን ፕሬዝደንቱ ከገዛ አገራቸው ረብሻ ይልቅ የትውልደ ሶማሊያዊቷን ፖለቲከኛ አገር ቀውስ ላይ ማተኮር መርጠዋል።
ፖለቲከኛዋ የፕሬዝደንቱ ንግግር 'ዘረኛ' እንደሆነ ጠቅሳ ምላሽ ሰጥታለች። ፕሬዝደንቱ ይህንን የተናገሩት በሚኒሶታ ግዛት የመጪው ምርጫ ተቀናቃኛቸው ጆ ባይደን ከእሳቸው የተሻለ ተቀባይነት ስላላቸው ነው እንዲህ ዓይነት ንግግር ያሰሙትም ብላለች።
ወጣም ወረደ ትራምፕና ደጋፊዎቻቸው ስለ ሶማሊያ ያላቸው አመለካከት፤ የአሜሪካ ወታደሮች በ1993 ዓ.ም ሞጋቃዲሾ ላይ ከፈፀሙት የከሸፈ ተልዕኮ ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፕሬዝደንቱ፤ ፖለቲከኛዋን 'በጥላቻ የተሞላችና አሜሪካን የምታጣጥል ሶሻሊስት' ሲሉ ይኮንናሉ።
ትራምፕ፤ ኢልሃን የጆ ባይደን ደጋፊ ናት ይበሉ እንጂ ፖለቲከኛዋ ለበርኒ ሳንደርስ ግልፅ የሆነ ድጋፍ ታደርግ ነበር።
ትራምፕ ባለፈው ዓመት በሰሜን ካሮላይና በነበራቸው የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ደጋፊዎቻቸው "ወደ አገሯ ላካት" እያሉ ሲጮሁ እንደነበር አይዘነጋም።
ኢልሃን፤ የአሜሪካ ሕግ አውጪዎች ለእስራኤል ያግዛሉ ብላ በትዊተር ገጿ መፃፏን ተከትሎ ከዴሞክራቶች ጭምር ትችት ሲሰዘነርባት እንደነበር አይዘነጋም። ይህን ተከትሎ በይፋ ይቅርታ ጠይቃም ነበር።
በወቅቱ ሪፐብሊካኑ ራንድ ፖል ፖለቲከኛዋ ወደ አገሯ የምትመለስ ከሆነ የጉዞ ወጪዋን እንደሚሸፍኑ መናገራቸው ይታወሳል።
ትራምፕና ሶማሊያ
ትራምፕ ለሶማሊያ ያላቸው አመለካከት ዚያድ ባሬ ከሥልጣን መውረድ በኋላ የተቃኘ ይመስላል። ባሬ በ1991 ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ ሶማሊያ በዓለማችን ካሉ ቀውስ ያለባቸው አገራት መካከል አንዷ እንደሆነች ሲጠቀስ መስማት አዲስ አይደለም።
ምንም እንኳ ሶማሊያ የዚያን ጊዜ ከነበረችበት ሁኔታ አሁን ብትሻሻልም በወቅቱ የተሰጣት ስም አሁንም መለያዋ ሆኗል።
ትራምፕ፤ ሶማሊያ ሕግ የሌለባት፣ ፖሊስ የማይታባት፣ መንግሥት የከሸፈባት ቢመስላቸውም እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው። ምንም እንኳ አል-ሻባብ አሁንም በሞቃዲሾ ጥቃቶችን ማድረስ ባያቆምም፤ ሶማሊያ ግን ትራምፕ የሳሏትን ዓይነት አይደለችም።
አስደናቂው ብሔራዊ ትያትር ባለፈው ሳምንት ተመርቋል። ሶማሊያም ውድና ምቾት ያላቸው ሆቴሎች አሏት። ካፌዎች እና የባህር ዳርቻ ምግብ ቤቶች በሶማሊያ አሉ።
የራስ ገዟ ሶማሊላንድ ሪፐብሊክ ዋና ከተማ የሆነችው ሃርጌሳ በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ በጣም ሰላማዊ ከሆኑ ከተሞች መካከል ናት። ሶማሊላንድ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እውቅና አታግኝ እንጂ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ታደርጋለች።
ዳሃብሺል እና ዎርልድ ረሚት የተሰኙት በአፍሪካ ስመ ገናናዎቹ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች የተመሠረቱት በሶማሊያውያን ነው። የአገሪቱ ዜጎች የወረቀት ገንዘብን ወደሚያስቀር የንግድ እንቅስቃሴ ማምራት ከጀመሩ ሰነባብተዋል።
በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፈው መንግሥት እስላማዊ ታጣቂዎችን ለመግታት እየጣረ ነው።

የፎቶው ባለመብት, AFP
በርካቶች ወደ አገራቸው እየተመለሱ ነው። ከእነዚህ መካከል የወቅቱ ፕሬዝደንት ሞሐመድ አብዱላሂ ሞሐመድ ወይም ፎርማጆ አንዱ ናቸው። ፎርማጆ አሜሪካ ውስጥ የተመዘገቡ ሪፐብሊካን ነበሩ። ነገር ግን አገራቸውን ለማገልገል የአሜሪካ ዜግነታቸውን ትተው መጥተዋል።
እርግጥ ነው አሜሪካውያን ስለ ሶማሊያ ሲያስቡ ትዝ የሚላቸው የ1991 የከሸፈ ወታደራዊ ተልዕኮ ይሆናል። በወቅቱ አንድ የጦር አበጋዝን ለመያዝ የመጡት አሜሪካውያን ድል ተነስተው ተመልሰዋል። ሁለት 'ብላክ ሃውክ' ሄሊኮፕተሮች ተመትተው ተጥለዋል፤ 18 የአሜሪካ ወታደሮች እና 500 ሶማሊያዊያን ተገድለዋል።
የአሜሪካውያኑ ወታደሮች ሬሳ በሞቃዲሾ መንገዶች ላይ ሲጎተት የሚያሳየው ምስል አሜሪካውያን አስደንግጧል፤ አሸማቋል።
ነገር ግን የትራምፕ መንግሥት አል-አሸባብን ለማጥፋት ሶማሊያ ውስጥ አሁንም ተልዕኮ ይፈፅማል። ሰው አልባ አውሮፕላኖች ይበራሉ። ልዩ ኃይሎች ማንነታቸውን ሸፍነው ይንቀሳቀሳሉ። ይህንን የሚያውቁ ግን ጥቂት አሜሪካውያን ናቸው።
ሶማሊያ ከሦስት አሥርት ዓመታት በፊት ምስቅልቅሏ ሲወጣ በርካቶች አገር ጥለው ተሰደዋል። ሶማሊያውያን ከአጥናፍ አጥናፍ ይገኛሉ። ከአርክቲክ እስከ ኒውዚላንድ ሶማሊያውያን የማይገኙበት የምድር ክፍል የለም ማለት ማጋነን አይሆንም።
በርካታ ጥቁሮችና ሙስሊሞች የሚኖሩባት የአሜሪካዋ ሚኒያፖሊስ ግዛት ደግሞ በርካታ ሶማሊያውያን የይገኙባታል።
ከመስከረም 1 [ወይንም 9/11] ክስተት በኋላ ሙስሊሞች አሜሪካ ውስጥ ጥርጣሬ እንደሚታዩ ማድረጉ ሳይታለም የተፈታ ነው። ፕሬዝደንት ትራምፕም ለሙስሊሞች ያለውን አመለካከት ከማላላት ይልቅ እያባባሱት ይመስላሉ።
ኢልሃን ለትራምፕ 'መልካም ስደተኛ' አይደለችም። ሂጃብ በኩራት የምትለብሰው ወጣቷ ፖለቲከኛ በአሜሪካ ሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ሂጃብ ለብሳ ለመቅረብ ተከራክራ መርታቷ አይዘነጋም።
የአሜሪካ ምርጫ አምስት ወራት ቀርተውታል። በእነዚህ ወራት ኢልሃን በፖለቲካ አቋሟ ሳይሆን በባህሏና እምነቷ ስትተችና ስትዘለፍ መስማት አያስደንቅ ይሆናል።














