የአሜሪካ ኮንግረንስ አባሏ ኢልሃን ኦማር ዘረኝነትን ለመዋጋት አስቸኳይ ለውጥ እንደሚያስፈልግ ተናገረች

የፎቶው ባለመብት, Stephen Maturen
ጆርጅ ፍሎይድ የተገደለበት የአሜሪካዋ ሜኒሶታ ግዛት ተወካይ የሆነችው የኮንግረስ አባሏ ኢልሃን ኦማር በአሜሪካ ያለውን ዘረኝነት ለመዋጋት አስቸኳይ ለውጥ እንሚያስፈልግ ተናገረች፡፡
ኢልሃን "በአገሪቷ ጥቁር ሕዝቦች ከባርነት ዘመን አንስቶ ያለፍርድ ግድያ፣ ከዚያም ወደ 'ጂም ክሮው' ወደተሰኘው ጨቋን ሕግ፣ እንዲሁእመ አሁን እያየነው ወዳለው ጭካኔ የተሞላበት የፖሊስ ድርጊት፣ ወደ ጅምላ እስር . . . ብቻ ሰብዓዊነታችን እንደተገፈፈ ነው" ስትል ለቢቢሲ ኒውስናይት ተናግራለች፡፡
ኢልሃን አክላም "ታመናል፤ ታክቶናል፡፡ በእያንዳንዱ ቀን ራሳችንን በዚህ ሁኔታ ውስጥ እናገኘዋለን፡፡ ማንም ይሁን ማን ግድ አይሰጠንም ግድ የሚለን እንዲመጣ የምንታገልለት ለውጥ ነው፡፡" ብላለች በምሬት፡፡
ኢልሃን በተለያየ ጊዜ ዘረኛ ንግግሮችና ድርጊቶችን በመቃወም ጠንከር ያሉ ሃሳቦችን በመሰንዘር ትታወቃለች፡፡
ከምርጫ ቅስቀሳቸው ጀምሮ የስደተኞችን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ ቃል እየገቡ የመጡት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ልክ የዛሬ አንድ ዓመት ብዙዎች አግላይ ያሉትን ንግግር አድርገው ነበር፡፡
ትራምፕ በንግግራቸው ከዚህ በኋላ አሜሪካ የምትቀበላቸው ስደተኞች ወጣት፣ የተማሩና እንግሊዝኛ ቋንቋ የሚችሉትን ነው፤ የስደተኞች የጥገኝነት ጥያቄ ተቀባይነት የሚያገኘው አቅማቸው ታይቶ ሲሆን፤ የአሜሪካን የሥነ ዜጋ ትምህርት ተፈትነው ማለፍ ይኖርባቸዋል ነበር ያሉት።
ብዙዎች ይህን ንግግራቸውን "ዘረኝነት የተሞላበት"፤ "ፀረ ስደተኛና ፀረ-ጥቁር ነው" ሲሉ ኮንነውታል፡፡
ከእነዚህም ውስጥ ትውልደ ሶማሊያዋ የኮንግረስ አባል ኢልሃን ኦማር አንዷ ነበረች። "ጥገኝነት ለሚጠይቁ ግለሰቦች ጀርባችንን ልንሰጣቸው አይገባም።
"የትራምፕ ንግግር በጣም ተስፋ አስቆራጭ ነው። በተለይም ከፍተኛ ፈተናን አምልጠው፣ አዲስ ተስፋን ሰንቀው የሚመጡ ሰዎች ላይ እንዲህ አይነት ንግግር ማድረጋቸው ሀዘኔን የበለጠ ይጨምረዋል። ምክንያቱም እኔም ከእነሱ አንዷ ነበርኩ" ማለቷ ይታወሳል።
የ37 ዓመቷ ኢልሃን ኦማር የሦስት ልጆች እናት ሶማሊ አሜሪካዊት ናት፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የመጀመሪያዋ አፍሪካ የተወለደች የአሜሪካ ኮንግረስ አባል ከሆኑት የመጀመሪያ ሙስሊም ሴቶች አንዷ ናት፡፡












