አሜሪካ ከ28 ዓመታት በኋላ ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮዋን በሶማሊያ በድጋሜ ጀመረች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አሜሪካ ከሶማሊያ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከሰላሳ ዓመታት በኋላ እንደገና ጀመረች።
የአሜሪካ መንግስት እንዳስታወቀው አጋጣሚው የምስራቅ አፍሪካ አገራት ያሳዩትን እድገት የሚያመላክት ታሪካዊ ቀን ነው።
ከዚህ ቀደም ተቀማጭነቱን በኬንያ ናይሮቢ ያደረገው ኤምባሲ አሁን በሞቃዲሾ በሚከፈተው ኤምባሲ ዶናልድ ያማማቶ አምባሳደር እንደሚሆኑ ታውቋል።
አሜሪካ በአውሮፓውያኑ 1991 ጥር ወር በሶማሊያ በአማፅያኑ ቡድኖችና በመንግስት መካከል በተፈጠረ ግጭት ኤምባሲዋን ዘግታ አምበሳደሩንና ሰራተኞቿን ማስወጣቷ ይታወሳል።
የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ ሒዘር ኖርት አሁን የተደረገውን ለውጥ አስመልክተው በሰጡት አስተያየት "ይህ ታሪካዊ ቀን የሶማሊያን እድገት ያሳየ ነው፤ አሜሪካ በአገሪቱ የምታደርገውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከርም ይህ አንድ እርምጃ ነው" ብለዋል።
ኤምባሲያቸውንም ተመልሰው መክፈታቸው በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ዘላቂነት ያለው ዲሞክራሲያዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማጠናከር እንደሆነ ገልፀዋል።
የፀጥታ ጉዳይን በተመለከተ ምንም እንኳን አልሻባብ አሁንም ችግር ቢሆንም የሞቃዲሾ የፀጥታ ሁኔታ እየተረጋጋ እንደመጣ ሳይገልፁም አላለፉም - ቃል አቀባይዋ።
አልሻባብ የሶማሊያን መዲና ሞቃዲሾን ለቆ እንዲወጣ በአፍሪካ ኅብረት ወታደሮች ግፊት የተደረገበት ከ7 ዓመታት በፊት ነበር፤ ይሁን እንጂ አሁንም በአገሪቱ ተለያዩ አካባቢዎች ተፅዕኖው እንዳለ ነው።
ባለፈው ዓመት የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በመዲናዋ ፀጥታ ለማምጣት ዘመቻቸውን አስፋፍተው ነበር፤ በዚህ ዓመትም በሰው አልባ የጦር ጀት ድብደባን ጨምሮ በወታደሮቿ ከ24 ጊዜ በላይ የአየር ድብደባ ፈፅማለች።
በአውሮፓውያኑ 1993 አሜሪካ በሶማሊያ ሞቃዲሾ ባደረገችው ውጊያ ወቅት 18 የልዩ ኃይል ወታደሮቿ መገደላቸውን ተከትሎ አሜሪካ ጣልቃ መግባት ሰግታ ነበር።
ባለፈው ወር 700 የሚሆኑ ሽብርተኛ ወታደሮች ከአፍሪካ ማስወታጣት መቻሏን አሜሪካ አስታውቃለች፤ ይሁን እንጂ አሁንም በሶማሊያ እያከናወኑት ያለው ተግባር ሰፊ እንደሆነ ገልፀዋል።













