ሶማሊያ የተባበሩት መንግሥታት መልዕክተኛ ኒኮላስ ሃይሶምን አባረርች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሶማሊያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መልዕክተኛ የሆኑትን ኒኮላስ ሃይሶም እራሳቸውን እንደ ሶማሊያ መሪ በመቁጠር ዓለም አቀፉን ድርጅት ''አዋርደዋል'' በማለት ከሃገሯ አባረረች።
ኒኮላስ ሃይሶም የቀድሞ የአልሸባብ መሪ ለነበሩት ሙክታር ሮቦው አጋርነታቸውን ያሳዩ ሰልፈኞች ግድያ አሳስቦኛል ብለው ነበር።
የሶማሊያን ደቡብ ምዕራብ ግዛት ለማስተዳደር ተወዳድሮ የነበረው የቀድሞ የአልሸባብ መስራች እና አባል ሙክታር ሮቦው በሶማሊያዋ ባይዶዋ ከተማ የአሚሶም የሰላም አስከባሪ ኃይል አባል በሆኑ የኢትዮጵያ ወታደሮች በቁጥጥር ሥር ውሎ ከምርጫ ሳይሳተፍ መቅረቱ ይታወሳል።
የሙክታር ሮቦው እስር እና በምርጫ እንዳይሳተፍ መደረጉን ተከትሎ በተነሳው ተቃውሞ፤ 15 ሰዎች መገደላቸውን እና ወደ 300 የሚጠጉ ደግሞ ለእስር መዳረጋቸውን የተባበሩት መንግሥታት አስታውቋል።
የተባበሩት መንግሥታት አልሸባብን እየተዋጉ ለሚገኙት የሶማሊያ መንግሥት ጦር ስልጠናዎችን፣ የደንብ ልብስ እንዲሁም ክፍያ ይሰጣል።
ትናንት ከአል-ቃይዳ ጋር ጥምረት ያለው አልሸባብ በሞቃዲሹ ወደ ሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ቅጥር ግዚ ውስጥ ሞርታር ተኩሻለሁ ብሎ ነበር።
በጥቃቱ ሶስት ሰዎች መጎዳታቸውን የተባበሩት መንግሥታት አስታውቋል።
የአልሸባብ ምክትል መሪ የነበሩት ሙክታር ሮቦው ቡድኑን እ.አ.አ. 2017 ላይ ነበር ክደው የተለዩት።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
'ሉዓላዊነት ተጥሷል'
ሙክታር ሮቦው ከአልሸባብ እራሱን ካገለለ ከአንድ ዓመት በኋላ የሶማሊያን ደቡብ ምዕራብ ግዛት ለማስተዳደር ከሳምንታት በፊት በተካሄደ ምርጫ ለመሳተፍ ፍላጎቱን አሳይቶ ነበር።
ሆኖም ምርጫው ከመከናወኑ ጥቂት ሳምንታት በፊት ሙክታር ሮቦው በሶማሊያ መንግሥት በቁጥጥር ሥር ውሎ በምርጫው እንዳይሳተፍ ተደርጓል።
የሶማሊያ መንግሥት ሙክታር ሮቦው ''ከጽንፈኛ አስተሳሰቡ አልተላቀቀም'' ብሎታል።
በሶማሊያ የተባበሩት መንግሥታት መልዕክተኛ ኒኮላስ ሃይሶም ከአራት ቀናት በፊት ሙክታር ሮቦው ለምን እንደተሳረ፤ እንዲሁም በደጋፊዎቹ ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ እንዲመረመር የሚጠይቅ ደብዳቤ ለሶማሊያ መንግሥት ጽፈው ነበር።
የሶማሊያ መንግሥት ለተመድ መልዕክተኛው ምላሽ ስለመስጠቱ ባይታወቅም፤ የውጪ ጉዳይ ሚንስትሩ አህመድ ኢሴ አዋድ የተመድ መልዕክተኛው እኛ ሃገር ተቀባይነት የላቸውም ብለዋል።
''ኒኮላስ ሃይሶም ዲፕሎማሲያዊ አሰራሮችን ጥሰዋል፣ እራሳቸውንም የሶማሊያ መሪ አድርገው ቆጥረዋል። ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምግባር ውርደት ናቸው። የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና ነጻነት ተጋፍተዋል'' በማለት የውጪ ጉዳይ ሚንስትሩ ለቢቢሲ ሶማልኛ ተናግረዋል።
ኒኮላስ ሃይሶም ደቡብ አፍሪካዊ ሲሆኑ፤ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ የሕግ አማካሪ ነበሩ።
ከዚያም አፍጋኒስታን፣ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን የተባበሩት መንግሥታት መልዕክተኛ በመሆነ አገልግለዋል።












