አሜሪካ በአየር ጥቃት 62 የአልሸባብ ታጣቂዎችን ገደልኩ አለች

አሜሪካ 62 የአልሸባብ ታጣቂዎችን ገደልኩ አለች

የፎቶው ባለመብት, AFP

የአሜሪካ ጦር በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰው እስላማዊው የአልሸባብ ቡድን ላይ በሰነዘርኩት ስድስት የአየር ጥቃቶች 62 የታጣቂው ቡድን አባላትን መግደል ችያለሁ ብሏል።

የአሜሪካ ጦር መግለጫ እንደሚለው ከሆነ ቅዳሜ ላይ በተሰነዘሩት 4 የአየር ጥቃቶች 32 ሚሊሻዎችን እንዲሁም እሁድ በተሰነዘረው 2 የአየር ጥቃቶች 28 ወታደሮችን መግደሉን ጦሩ አሳውቋል።

በአሜሪካ የአየር ጥቃት በርካታ የአልሸባብ ሚሊሻዎች ሲገደሉ ይህ ከአንድ ዓመት ወዲህ ትልቁ ነው። ከአንድ ዓመት በፊት አሜሪካ 100 የቡድኑ አባላትን እንደገደለች መግለጿ ይታወሳል።

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራም ዋይት ሃውስ ከገቡ በኋላ ደግሞ አልሸባብ ላይ ያነጣጠሩ የአየር ጥቃቶች ጨምረዋል።

ትራምፕ የአሜሪካ ጦር በአልሸባብ ላይ ጥቃቶችን እንዲፈጽም ተጨማሪ የጦር ፍቃድ ሰጥተዋል።

እአአ 1993 ላይ በአሜሪካ ጦር የልዩ ኃይል አባላት ላይ ከተሰነዘረው ጥቃት በኋላ ከትራምፕ በፊት የነበሩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች በሶማሊያ ቀጥተኛ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትን አብዝተው አይደፍሩም ነበር። 1993 ላይ 13 የአሜሪካ ጦር የልዩ ኃይል አባላት በመዲናዋ ሞቃዲሾ ከታጣቂዎች ጋር ሲፋለሙ ተገድለው ነበር። ይህም ብላክ ሆክ ዳዎን (Black Hawk Down) በሚል ርዕስ ወደ ፊልም ተቀይሮ በርካቶች ተመልክተውታል።

ከምረመራ ጋዜጠኞች ቢሮ የተሰበሰቡ አሃዞች እንደሚያሳዩት ከሆነ ከአውሮፓውያኑ 2017 ጀምሮ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ከ400 በላይ ሰዎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን ይህም ካለፉት 10 ዓመታት ድምር በላይ ነው።

አሜሪካ ጅቡቲ ላይ ካላት ግዙፍ የጦር ስፍራ በመነሳት ነው የአልሸባብ ሚሊሻዎች ላይ የአየር ጥቃት የምትሰነዝረው።

'የአሸባሪዎች የተመቸ ገነት የሆነ ስፍራ'

የአሜሪካ ጦር መግለጫ ጨምሮ እንዳለው፤ ይህ ተልዕኮ የተከናወነው ከሶማሊያ መንግሥት ጥምረት ጋር እንደመሆኑ በዘመቻው እንድም የተገደለ ሲቪል የለም።

''ከሶማሊያ መንግሥት እና ከሌሎች ዓለም አቀፍ አጋሮቻችን ጋር በመጣመር አልሸባብ ደህነነቱ የተጠበቀ ስፍራ የማግኘት አድሉን በመጠቀም እራሱን እንዲያደረጅ እና ተልዕኮውን እንዲፈጽም አንፈቅድለትም'' ይላል የጦሩ መግለጫ።

የአልቃይዳ አጋር የሆነው አልሸባብ ስለ አየር ጥቃቱ እስካሁን ያለው ነገር የለም።

መቀመጫቸውን በሶማሊያ ያደረገ ተመራማሪ ቡድን እንደሚለው ከሆነ የአየር ጥቃቶች ከመብዛታቸው የተነሳ አልሸባብ ጥቃት የሚፈጽምበትን ስልት እየቀያየረ ነው።

አልሸባብ እንደ ቀድሞ በጦር ካምፖች ላይ ያደርግ የነበረውን ጥቃት በመቀነስ ፊቱን ወደ መንግሥት ተቋማት እና ግብር ለአልሸባብ ወደማይከፍል የንግድ ተቋማት ላይ አዙሯል።

የአሜሪካ መንግሥት በቅርቡ ሶማሊያን ''ለአሸባሪ የተመቸ ገነት የሆነ ስፍራ'' ሲል ግልጿታል።

አልሸባብ አሁንም በርካታ የሶማሊያ ስፍራዎችን ተቆጣጥሮ ይገኛል። አጥፍቶ ጠፊዎችን፣ ተቀጣጣይ መሳሪያዎችን እና ከባድ የጦር መሳሪያዎችን በመጠቀም አሁንም ከፍተኛ ጥቃቶችን ይሰነዝራል።