በጎሳ ታጣቂዎች እና በአልሸባብ ወታደሮች መካከል ግጭት ተቀሰቀሰ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ሶማሊያ ውስጥ በጎሳ ታጣቂዎች እና በአልሸባብ ወታደሮች መካከል ግጭት ተቀሰቀሰ። ግጭቱ የተፈጠረው የአልሸባብ እስላማዊ ቡድን ነዋሪዎች የገንዘብ መዋጮ እንዲያደርጉ እና ልጆቻቸውም ቡድኑን እንዲቀላቀሉ እንዲያደርጉ መጠየቁን ተከትሎ ነው።
የጎሳ ታጣቂዎች የአልሸባብ ወታደሮችን ከሰፈራቸው ጠራርገው ለማስወጣት እያጣሩ መሆኑን፤ በትንሹ አራት የቡድኑን ወታደሮች እንደገደሉ ተናግረዋል። የጎሳ ታጣቂዎቹ መሪ በተኩስ ልውውጡ መገደሉም ተወስቷል።
ታጣቂዎቹ የሶማሊያ መንግስት የሥራዊትና የትጥቅ ርዳታ እንዲያደርግላቸው የጠየቁ ሲሆን ለአሁኑ ግን በራሳቸው ሃቅም መታገልን መርጠዋል።
የተኩስ ልውወጡ የተጀመረው ያለፈው ሳምንት ማክተሚያ ላይ አልሸባብ ነዋሪዎችን ዓመታዊ ሃይማኖታዊ ክፍያ (ዛካት) እንዲከፍሉ እንዲሁም ልጆቻቸውን ለምልምል ወታደርነት አሳልፈው እንዲሰጡ ከጠየቁ በኋላ ነው።
ይሄ ርምጃ በአልሸባብ ቁጥጥር ስር ባሉ ስፍራዎች ያሉ ነዋሪዎች ከፍርሃት ባሻገር መልሰው ማጥቃት መጀመራቸውን የሚያሳይ አብነት ተደርጎ ተቆጥሯል።
አልሸባብ የሶማሊያ መንግሥት በእጁ ሊያስገባቸው ያልቻላቸውን በደቡብ እና ማዕከላዊ ሶማሊያ የሚገኙ አንዳንድ ቦታዎችን የያዘ ሲሆን፣ ነዋሪዎች የቡድኑን ህግጋት እንዲያከብሩ ሲያስገድድም ባጅቷል።












