በየመን ተኩስ አቁም ተግባራዊ በሆነ በደቂቃዎች ውስጥ ተጣሰ

የሃውቲ አማፅያን በሁደይዳህ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የሃውቲ አማፅያንና የመንግስት ደጋፊ ሃይሎች ተኩስ አቁሙን በመጣስ እርስ በእርስ እየተወነጃጀሉ ነው

በየመን ጦርነት ወሳኝ የእርዳታ መስመር በሆነችው ሁደይዳህ ከተማ በሃውቲ አማፅያንና በመንግስት ደጋፊ ሃይሎች መካከል የተደረገውተኩስ የማቆም ስምምነት ተፈፃሚ በሆነ በደቂቃዎች ውስጥ ተጣሰ።

ሁለቱ የየመን ተዋጊ ሃይሎች የተኩስ አቁም ስምምነቱን ያደረጉት በተባበሩት መንግስታት አስተባባሪነት ባለፈው ሳምንት ስዊድን ውስጥ ነበር።

ስምምነቱ ከሞላ ጎደል አራት ዓመታት ላስቆጠረው የየመን የእርስ በርስ ጦርነት መፍትሄ ለማበጀት ጅማሮ ይሆናል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት ነበር።

ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት በሁደይዳህ አማፅያኑ በመንግስት ደጋፊዎች ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል።

የመንግስት ደጋፊ ሃይሎችም ሁለቱ ሃይሎች እየተታኮሱ እንደሆነ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ገልፀዋል።

ሁደይዳህ ከየመን መዲና ሰንዓ 140 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ አራተኛ ትልቅ የአገሪቱ ከተማ ነች። ከተማዋ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እምብርት ስትሆን እንደ አውሮፓውያኑ በ2014 ማብቂያ ላይ በሁቲ አማፅያን እጅ ወድቃለች።

ላለፉት ስድስት ወራት በሳውዲ አረቢያና አጋሮቿ ጥምረት የሚደገፈው የየመን መንግስት እዚህች ከተማ ላይ ጥቃት ሰንዝሯል።

ሁለት ሶስተኛ የሚሆነው የየመን ህዝብ ህይወት በዚህች የወደብ ከተማ በሚገባ የምግብ፣ የመድሃኒትና የነዳጅ አቅርቦት ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ይነገራል።

በአሁኑ ወቅት 22 ሚሊዮን የሚሆኑ የመናዊያን የምግብ እርዳታ ሲያስፈልጋቸው ስምንት ሚሊዮን የሚሆኑ ደግሞ ለወዲያው የሚሆን ምግብ እንኳ የሌላቸው እንደሆኑ ተገልጿል።