ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ በቅዳሜው ውይይት ላይ ምን አሉ?

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ እና ፕሬዚዳንት ለማ መገርሳ

የፎቶው ባለመብት, FBC

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ ከተለያዩ የኦሮሞ ማሕብረሰብ ክፍል ከተወጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች፣ ወጣቶችና ባለሃብቶች እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ተወካዮች ጋር ባሳለፈነው ቅዳሜ በጽህፈት ቤታቸው ውይይት አድረገዋል።

ውይይቱ የተመራው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ሊቀ መንበርና በሃገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር በዶ/ር ዐብይ አህመድ እና በኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳደር ፕሬዚዳንትና የኦዴፓ ምክትል ሊቀ መንበር በአቶ ለማ መገርሳ ሲሆን የጠቅላይ ሚንስትሩ ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ደግሞ የመወያያ ጽሁፍ አቅርበዋል።

''የኦሮሞ የፖለቲካ ትግል ከየት ወዴት'' በሚል ርዕስ በተካሄው ውይይት ላይ በክልሉና በኦሮሞ ፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ፣ የሕግ የበላይነትን ስለማስከበር እንዲሁም የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ የተዳሰሱ ጉዳዮች ነበሩ።

''ከፊታችን የተጋረጠው ችግር ጥንካሬ ሰጥቶን የሚያሻግረን እንጂ የሚገታን አይሆንም። የኦሮሞ አንድነት ነው ጥንካሬ የሚሰጠን፤ የሚያሻግረን። በውስጣችን ኖሮ ሊገፋ እና ሊጠላ የሚገባው የለም'' ያሉት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ሲሆኑ ጨምረውም፤ በኦሮሚያ የሚኖረውን ህዝብን በብሔር እና በኃይማኖት ከፋፍሎ ጦር ሜዳ ለማድረግ የሚያሴሩ አሉ፤ ህብረተሰቡ ከዚህ አይነት እኩይ ተግባር እራሱን ሊጠብቅ ይገባል ብለዋል።

''የሃገር ሽማግሌ ይምከር፤ ያስታርቅ። የተማረው ይጻፍ፣ ይመራመር፣ ያወያይ። የኦሮሞ ወጣት ለህዝቡ አንድነት ይረባረብ'' ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሩ።

የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ በበኩላቸው ''ለኦሮሞ ህዝብ ምላሽ ሰጥተናል ብለን አናስብም። ለረዥም ዓመታት የኦሮሞ ህዝብ ሲያነሳቸው ለነበሩ እና መስዋዕትነት ሲከፍልባቸው ለነበሩ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ትክክለኛው መንገድ ላይ ነን ብለን ነው የምናስበው'' ብለዋል።

በተጨማሪም በውይይቱ ላይ የተነሳው ሌላ ጉዳይ ኢትዮጵያ በውጪው ዓለም ያላት ተሰሚነት እየጨመረ ስለመምጣቱ ነው። "በሃገሪቱ የውጪ ፖሊሲ ላይ ማሻሻያዎች በመካሄዳቸው በዓለም አቀፍ መድረክ የኢትዮጵያ ተደማጭነት እየጨመረ መጥቷል" ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ።

እንደ ማሳያም የተነሳው የኢትዮጵያ መንግሥት ከአዲስ አበባ-ጅቡቲ ለተዘረጋው የባቡር መስመር ለቻይና በየዓመቱ 400 ሚሊዮን ዶላር ለአስር ዓመታት እንድትከፍል የሚያደርገው ስምምነት በድርድር እንዲሻሻል ስለመደረጉ ነው።

የክፍያ መጠኑን እና ከፍያ የሚፈጸምበት ጊዜ ላይ በድርድር ማስተካከያ መደረጉን ጠቅላይ ሚንስትሩ ተናግረዋል። በየዓመቱ የሚከፈለው ክፍያ የተጋነነ ስለመሆኑ እና ከዚህ የውል ስምምነት የተደረሰው በቂ ግንዛቤ ሳይያዝ መሆኑን በማስረዳት፤ ብድሩ የሚከፍልበትን ዓመት ከ10 ወደ 38 ዓመት ከፍ አስደርገናል የክፍያ መጠኑንም በየዓመቱ 98 ሚሊዮን ዶላር እንዲሆን ለማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

የሕግ የበላይነትን የማስከበር ጉዳይ ሌላው ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አጽንዖት ሰጥተው የተናገሩበት ርዕስ ነበር። "ወንጀል ፈጽሞ ከሕግ ማምለጥ የማይታሰብ ነው" ያሉ ሲሆን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት በበኩላቸው "የተጠያቂነት አሰራር ዕውን እየሆነ በመምጣቱ የሕግ የበላይነት በኢትዮጵያ እየሰፈነ መጥቷል ብለዋል።"

"እዚህ አገር ውስጥ ከፈጣሪ በታች ይፈሩ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለው የሕግ የበላይነት መከበሩን አይተናል" ሲሉም ፕሬዚዳንት ለማ ተናግረዋል።

ከውይይቱ በኋላ የበርካቶችን ቀልብ ስቦ መነጋገሪያ የነበረው ግን ጠቅላይ ሚንስትሩ በመድረኩ ላይ የሰነዘሩት ሃሳብ ነው። ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ በኦሮሚኛ ቋንቋ በተካሄው በዚህ መድረክ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተለያዩ ችግሮች እያጋጠሙበት ወዳለው የወለጋ ክፍል ለምን እስካሁን ጉብኝት እንደላደረጉ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተው ነበር።

''ትውልዴ ጅማ ቢሆንም የልጅነት ጊዜዬን ያሳለፍኩት ወለጋ ውስጥ ነው። በትግል ምክንያት ከ16-17 ዓመት ያክል ወለጋ ነበርኩ። ለወለጋ ህዝብ ልዩ ፍቅር ነው ያለኝ። በዚያ በልጅነት ዘመኔ ውሃ ጠምቶኝ ስሄድ ውሃ አይሰጡኝም። ወተት ነበር የሚያጠጡኝ። ህዝቡንም ሃገሩንም በጣም ነው የምወደው" ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብለዋል።

ስልጣን ላይ ከመውጣታቸው ጥቂት ወራት በፊት የጊምቢ፣ የሻምቡ እና የነቀምቴን ህዝብ በስፍራው ተገኝተው እንዳነጋገሩ አስታውሰዋል። "ደምቢ ዶሎ ለምን አልመጣም ተብዬ ተወቀስኩ። እዚህ ቤተ-መንግሥት እንደገባሁ የሄድኩት ወደ ደምቢ ዶሎ ነው። አሁን በአካባቢው ችግር ሲከሰት ለምን ወደ ስፍራው አትሄዱም በሚለው ጥያቄ ላይ ከለማ ጋር በተደጋጋሚ ተነጋግረንበታል" ብለዋል።

ጨምረውም ከዚያ በኋላ ወደአካባቢው ላለመሄዳቸው በመረጃ የተደገፈ ምክንያት እንዳላቸው "እኔ መረጃው አለኝ፤ 'ህዝብ ከተፈናቀለ ሁለቱም ወደዚህ ይመጣሉ። እዚሁ እናስቀራቸዋለን' ይላሉ። 'ህዝብ ውስጥ ይገባሉ። ህዝብ ይስማሉ። እዚሁ እናሰቀራቸዋለን።' ይላሉ። አሁን ጉዳዩ ወደ አካባቢው መሄድ አይደለም" አስቀምጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም የሚያሳስባቸው የሕዝቡ አንድነት እንደሆነ ሲያጠቃልሉ "እኔ ወደ ሌላ ስፍራ ሄጄ ብሞት ኦሮሞ አንድ ሆኖ በትግሉ ይቀጥላል። በሕዝቡ መካከል ያለውን አንድነት ሊጎዳው ይችላል። ጉዳዩ የመስዋዕትነት ጉዳይ አይደለም። አንድነታችንን ሊንድ የሚችል ነገር ነው። ይህ ህዝብ ግን 'አንድነታችን በእናንተ ምክንያት አይናድም' የሚለን ከሆነ እኔ ችግር የለብኝም ነገ እሄዳለሁ'' ብለዋል።