አል-ሸባብ በሶማሊያ የተሰማሩ በርካታ የብሩንዲ ወታደሮችን እንደገደለ ተገለጸ

የአፍሪካ ሕብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል አባል

በሶማሊያ የተሰማሩ በርካታ የብሩንዲ ወታደሮች በካምፓቸው ላይ የአል-ሸባብ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት መገደላቸው ተገለጸ።

የተገደሉት ወታደሮች ምን ያህል እንደሆኑ ከአፍሪካ ኅብረትም ይሁን ከሶማሊያ ባለሥልጣናት መረጃ ባይሰጥም፣ የብሩንዲ ወታደራዊ ኃላፊ 30 ወታደሮቻቸው እንደተገደሉ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

አክራሪው የሶማሊያ ኢስላማዊ ታጣቂ ቡድን አል-ሸባብ በበኩሉ በጥቃቱ ከ170 በላይ ብሩንዲያውያን ወታደሮችን መግደሉን በመግለጽ መግለጫ አውጥቷል።

ወታደሮቹ በአፍሪካ ኅብረት ስር ሶማሊያው ውስጥ እየተንቀሳቀሱ የነበሩ ናቸው።

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሐማት፣ የአል-ሸባብን የሽብር ጥቃት አውግዘዋል።

በሶማሊያ፣ ሻበሌ በተባለው ቀጠና የተሰማራው የወታደሮች ቡድን (አትሚስ) ከብሩንዲ፣ ኡጋንዳ፣ ጂቡቲ፣ ኬንያ እና ኢትዮጵያ የተወጣጡ ፀጥታ አስከባሪዎች ይገኙበታል።

ትላንት ከሶማሊያ መዲና ሞቃዲሹ በ130 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ወታደራዊ ሰፈር ከፍተኛ ውጊያ እንደነበር የሶማሊያ ወታደራዊ አመራር ኮማንደር ሞሐመድ አሊን ጠቅሶ ኤኤፍፒ ዘግቧል።

"በሁለቱም ወገን ሰዎች ሞተዋል። ከፍተኛ ውጊያ ነበር። ቦምብ በጫነ መኪና ጥቃት ከሰነዘሩ በኋላ የተኩስ ልውውጥ ነበር" ብለዋል ኮማንደሩ።

አል-ሸባብ ወታደራዊ ሰፈሩን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩን ቢገልጽም ይህ ግን እስካሁን በገለልተኛ አካል አልተጣራም።

የሶማሊያ መንግሥት ከአል-ሸባብ ጋር የሚያደርገውን ውጊያ የሚደግፈው የአፍሪካ ኅብረት የሚያሰማራቸው ወታደሮች ከዚህ ቀደመም በታጣቂ ቡድኑ ጥቃት ደርሶባቸዋል።

የዓይን እማኞች እንዳሉት፣ በጦር ሰፈሩ ከነበረው የተኩስ ልውውጥ በተጨማሪ መሣሪያ ከሂሊኮፕተር ሲተኮስም ነበር።

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሐማት፣ በሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ሕይወታቸውን የሰጡትን የብሩንዲ ወታደሮች አመስግነው ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን ተመኝተዋል።

በአትሚስ ስር በሶማሊያ የተሰማሩ ፀጥታ አስከባሪዎች በዚህ ጥቃት ሳቢያ አላማቸው እንደማይዛነፍ ገልጸዋል።

የአፍሪካ ኅብረት ለሶማሊያ መንግሥት የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚቀጥልበትም አክለዋል።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለአትሚስ የሚያደርገውን ድጋፍ በማጠናከር በሶማሊያ ሰላም እንዲወርድ እንዲያግዝም ሊቀ መንበሩ ጠይቀዋል።