የሰሜኑ ጦርነት ሃሳብን በመግለጽ ነጻነት ላይ ያሳደረው ጫና ምን ይመስላል?

የሚራመዱ ሦስት ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በዛሬው ዕለት በምትከበረው የዓለም የፕሬስ የነፃነት ቀን ለረጅም ጊዜ በዘለቀ የርስ በርስ ጦርነት ሚሊዮኖች ያለ እርዳታና መረጃ እንዳያገኙ ባለበት ሁኔታ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ትኩረት ከሚደረግባቸው አገራት አንዷ ሆናለች።

በጦርነት በተጎዳችው የትግራይ ክልል ለበርካታ ወራት የስልክም ሆነ የኢንተርኔት አገልግሎት የለም። ከጦርነቱም ጋር በተያያዘ መንግሥት ጥሎት የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተቺዎችን ለማፈን ተጠቅሞበታል በሚል የመብት ቡድኖች ይከሱታል። መንግሥት ግን ይህንን አይቀበለውም።

በወቅቱም ክስ ካቀረቡት መካከል የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪው ሲፒጄ አንዱ ሲሆን ኢትዮጵያ የጋዜጠኞችን እስር ለማጠናከር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እየተጠቀመች ነው ብሎም ነበር።

በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሄደው ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት በአብዛኛው የተካሄደው በጨለማ ውስጥ ነው።

ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት የመጀመሪያዎቹ ጥይቶች በትግራይ ሲተኮሱ ሁሉም የመገናኛ ዘዴዎች ስልክና ኢንተርኔት በአንድ ላይ ተቋረጡ።

በአብዛኛው የጦርነቱ ቀጠና የነበሩ አካባቢዎች ግንኙነት ያልነበራቸው ሲሆን፤ የትግራይ ክልል አሁንም ከመላው ዓለም ተቆራርጣ ትገኛለች።

ይህ ሁኔታ በተለይ የጦርነቱ ተሳታፊ አካላት ጅምላ ግድያ፣ መድፈርና ሌሎች እንደ ጦር ወንጀል የሚቆጠሩ ከባድ ጥሰቶች በመፈጸም በሚወነጀሉበት ወቅት ያለውን ትክክለኛ ሁኔታ ለመረዳት አዳጋች አድርጎታል።

ጋዜጠኞች ወደ ጦር ግንባር እንዳይጓዙ በጥብቅ በመከልከላቸውም ስለ ጦርነቱም ሆነ የጦርነቱ ዳፋን በተመለከተ ለሪፖርት የበቃው በጣም ትንሽ ነው።

ከዚያ ባሻገር ጦርነቱ በጋዜጠኝነት እና በመላ አገሪቱ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ላይ የራሱን አሻራ አሳርፏል።

"ከጦርነቱ በፊት እንደ ሲፒጄ አንዳንድ አሳሳቢ አዝማሚያዎችን መመልከት ጀመርን። በፖለቲካዊ አለመረጋጋቶች ወቅት የኢንተርኔት አገልግሎቶች ይዘጉ ነበር፤ ነገር ግን ጦርነቱ ከተጀመረበት ወቅት ጀምሮ ቀደም ሲል ይስተዋሉ የነበሩ ሁኔታዎች ጎልተው መታየት ጀመሩ። ከባለፈው ዓመት ኅዳር ጀምሮ በርካታ ጋዜጠኞች ክስ ሳይመሰረትባቸው አንዳንዶቹም ለወራት ታስረዋል" በማለት ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት የሲፒጄ ተወካይ የሆኑት ሙቶኪ ሙሞ ያስረዳሉ።

ባለፈው ዓመት ኅዳር ወር ላይ ኢትዮጵያ በአገሪቱ የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ላይ ከፍተኛ አደጋ በመደቀኑ ይህንንም "በመደበኛው የሕግ ሥርዓት መቆጣጠር ባለመቻሉና ይህንንም አደጋ ለመቀልበስ በሚል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ" ማወጇ የሚታወስ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ ቢያንስ 14 ጋዜጠኞች ለእስር ተዳርገዋል።

መንግሥት በበኩሉ የጋዜጠኝነት ተግባራቸውን በማከናወናቸው ኢላማ አለመደረጋቸውን የገለጸ ሲሆን የታሰሩት ወንጀሎች ፈፅመዋል በሚል ተጠርጥረው ነው ብሏል።

በእስር ላይ ከነበሩት መካከል መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) የትግርኛ ቋንቋ የሬድዮ አገልግሎት የቀድሞ ሁለት ጋዜጠኞች፣ የዩቲዩብ ቻናል የሆነው ኡቡንቱ ቴሌቪዥን ዋና አዘጋጅ፣ የተራራ ኔትወርክ ዋና አዘጋጅ እንዲሁም የሮሃ ቴሌቪዥን ተባባሪ መስራች ይገኙበታል።

ከዚህም በተጨማሪ የአሶሺየትድ ፕሬስ ዘጋቢ፣ የካሜራ ባለሙያ እና የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋዜጠኛም እንዲሁ በእስር ላይ የነበሩ ሲሆን ከእነዚህ መካከል በርካቶቹ መፈታታቸው ይታወሳል።

ከእነዚህም መካከል የአሶሼትድ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘጋቢው አሚር አማን በመንግሥት በአሸባሪነት የተፈረጀውን አማፂ ቡድን አባላትን ቃለ መጠይቅ ካደረገ በኋላ ለአራት ወራት ያህል በእስር ላይ ቆይቷል።

"ሀሳቦች እንዳይወጡ ማገድ አይቻልም። አሁን የተለየ ጊዜ ነው። ዜናዎችና ታሪኮች ወደ ህዝብ እንዳይደርሱ መከልከል አይቻልም። እኛ ለአገር ስጋት አይደለንም። እየሠራን ያለነው ሥራችንን ነው። ሐሳብን የሚያፍን ሥርዓት ሊኖረን አይገባም። ከዚህ በፊት ብዙ ጊዜ ሞክረነዋል እና በጭራሽ አልሰራም። በፍጹም አልረዳንም" በማለት አሚር ያስረዳል።

ሲፒጄ በቅርቡ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት ጋዜጠኞችን በማሰር ኢትዮጵያ ሁለተኛ ናት በሚል ሪፖርት አውጥቷል።

በዛሬው ዕለትም ድርጅቱ በእስር ላይ ያሉት ደሱ ዱላ እና ቢቂላ አመኑ የተሰኙ ጋዜጠኞች እንዲፈቱና ክሳቸው እንዲቋረጥ ጠይቋል።

የማኅበራዊ ሚዲያ የሆነው የኦሮሚያ ኒውስ ኔትወርክ ጋዜጠኞቹ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ ቢሆንም የታሰሩት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቢነሳም ደሱ እና ቢቂላ በእስር ቤት እንዳሉና ህገ መንግሥቱን በመፃረር በቀረበባቸው እስከ ሞት የሚያደርስ ከፍተኛ ቅጣት እንደሚጠብቃቸውም ገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ለጋዜጠኞች ጭላንጭል የተስፋ መስኮት ቢታይም ኢትዮጵያ በታሪኳ ለጋዜጠኞች በጣም አስቸጋሪ ቦታ ሆና ቆይታለች።