ኢትዮጵያ የጋዜጠኞችን እስር ለማጠናከር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እየተጠቀመች ነው-ሲፒጄ

የፎቶው ባለመብት, CPJ
የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በሥራቸው ምክንያት በእስር ላይ የሚገኙ ሁሉንም ጋዜጠኞች በአስቸኳይ እና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፍታት አለባቸው ሲል ለጋዜጠኞች መብት የሚቆረቆረው ሲፒጄ ጠየቀ።
ኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመጠቀም የፕሬስ አባላትን ከማሰር መቆጠብ አለባት ሲል ሲፒጄ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ ጠይቋል።
ኢትዮጵያ ከእርስ በርስ ጦርነቱ ጋር በተያያዘ የአስቸኳይ ጊዜ ካወጀችበት ጥቅምት 23/2014 ዓ.ም ጀምሮ 14 ጋዜጠኞችን ማሰሯን ሲፒጄ አስፍሯል።
በእስር ላይ ከዋሉት መካከል መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) የትግርኛ ቋንቋ የሬድዮ አገልግሎት የቀድሞ ሁለት ጋዜጠኞች፣ የዩቲዩብ ቻናል የሆነው ኡቡንቱ ቴሌቪዥን ዋና አዘጋጅ፣ የተራራ ኔትወርክ ዋና አዘጋጅ እንዲሁም የሮሃ ቴሌቪዥን ተባባሪ መስራች ይገኙበታል።
ከዚህም በተጨማሪ የአሶሺየትድ ፕሬስ የቪዲዮ ጋዜጠኛ፣ የካሜራ ባለሙያ እና የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋዜጠኛ ከኦሮሞ ነፃነት ጦር ታጣቂዎች ዘገባ ጋር በተያያዘ በእስር ላይ መዋላቸውን በትናንትናው ዕለት ፖሊስ አስታውቋል።
እነዚህ ጋዜጠኞች ኅዳር 19/2014 ዓ.ም እንደታሰሩ አሶሺየትድ ፕሬስና የአገር ውስጥ ሚዲያ የዘገቡ ሲሆን ነገር ግን የጋዜጠኞች እስር ይፋ የሆነው በትናንትናው ዕለት ነበር።
ሦስቱ ጋዜጠኞች የአሶሺየትድ ፕሬስ የቪዲዮ ጋዜጠኛ የሆነው አሚር አማን ኪራዮ፣ የካሜራ ባለሙያው ቶማስ እንግዳ እንዲሁም የፋና ብሮድካስቲንግ ጋዜጠኛ አዲሱ ሙሉነህ ናቸው።
አሶሺየትድ ፕሬስ (ኤፒ) አሚር ለአንድ ዘገባ ጉዞ ካደረገ በኋላ መታሰሩን አመልክቷል። ሲፒጄ በቶማስ እና በአዲሱ እስር ዙሪያ ያለውን ሁኔታ ማጣራቱን መቀጠሉን ገልጿል።
ኤፒ ስለ አሚር የዘገባ ጉዞ ማብራሪያ ባይሰጥም ነገር ግን ሦስቱም የአገሪቱን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እና የፀረ ሽብርተኝነት ሕግን በመጣስ ተከስሰዋል ብሏል።
የመንግሥት ሚዲያዎች በበኩላቸው ሦስቱ ጋዜጠኞች በቁጥጥር ስር የዋሉት በአሸባሪነት የተፈረጀውን የኦሮሞ ነፃነት ጦር ወይም በመንግሥት ባለሥልጣናት ዘንድ ሸኔ ተብሎ የሚጠራውን ታጣቂ ቡድን አባላትን ቃለ መጠይቅ ማድረጋቸውን ተከትሎ እንደሆነ ዘግበዋል።
የኤፒ ሥራ አስፈጻሚ ጁሊ ፒስ አሚር፣ በኢትዮጵያ የርስ በርስ ጦርነት ላይ ሰፊ የዳሰሰ ዘገባዎችን መስራቱን ገልጸው ክሱንም "መሰረተ ቢስ ነው" ሲሉ አጣጥለውታል።
አሚር ከታሰረ በኋላ ቤተሰቡ በሳምንት ሁለት ጊዜ እንዲጎበኘው መፍቀዱን የኤፒኢ ቃለ አቀባይ ለሲፒጄ በላኩት ኢሜይል ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ቃል አቀባይ ጄይላን አብዲ ረቡዕ ማምሻውን እንደገለጹት የኦሮሞ ነፃነት ጦርን ማነጋገር በአገሪቱ የፀረ ሽብር ሕግ "ወንጀል" እንጂ የጋዜጠኝነት ተግባር እንዳልሆነ በስልክ ለሲፒጄ ተናግረዋል።
የጋዜጠኞቹ አላማ ጦሩን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ እንደሆነ የገለፁት ጄይላን ጊዜውን ባይጠቅሱም ፖሊስ ጋዜጠኞቹን ፍርድ ቤት ያቀርባቸዋል ብለዋል።
ሲፒጄ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሌሎች ስድስት ጋዜጠኞች መታሰራቸውን ቀደም ሲል መዝግቧል።
"የኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለፀጥታ ሠራተኞች እጅግ ሰፊ የሆነ የማሰር ሥልጣን ይሰጣል እንዲሁም ሕጋዊ ሂደቶችን ያቆማል፣ ጋዜጠኞች ሥራቸውን በአግባቡ እንዳይስሩ ይከለክላል እንዲሁም ለፕሬሱ አስፈሪ መልዕክት ያስተላልፋል" ሲሉ ከሰሃራ በታች የሲፒጄ ተወካይ ሙቶኪ ሙሞ ተናግረዋል።
"የኢትዮጵያ መንግሥት በሥራቸው ምክንያት ለእስር የተዳረጉ ጋዜጠኞችን በሙሉ መፍታት እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንደ ሰብብ በመጠቀም ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን መጣስ የለባቸውም" ብሏል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ትግርኛ ፕሮግራም የትግርኛ ቋንቋ የሬድዮ አገልግሎት ጋዜጠኞች የነበሩት ተክለ ሐይማኖት ግርማይ እና መኮንን ይብራህ ቤት ፖሊስ ጥቅምት 25/2014 ዓ.ም መምጣቱን ሲፒጄ ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ ከጠየቁ ከጋዜጠኞቹ ዘመድ፣ ጓደኛና የሥራ ባልደረቦች ተረድቷል።
መኮንንና ተክለሐይማኖት ከኢቢሲ የተባረሩት የሚዲያውን የሥነ ምግባር ደንብ ጥሰዋል በሚል እንደሆነም ተቋሙ ከጋዜጠኞቹ ዘመዶች ተረድቷል።
በሲፒጄ የተገመገሙ ሰነዶች እንደሚያሳዩት የጣቢያው ኃላፊዎች መኮንን ከየካቲት እስከ ግንቦት የሰራቸው ዘገባዎች የኤዲቶሪያል ይሁንታን ያላገኙና ህወሓትን የሚደግፉ ናቸው ሲሉ ከሰውታል።
ተክለ ሐይማኖት፣ ነሐሴ 4/2013 ዓ.ም በሰራው ዘገባ መንግሥት የትግራይ ተወላጆች የሆኑ የንግድ ተቋማትን እየዘጋ ነው በሚል የታገደ ሲሆን፣ የጣቢያው ኃላፊዎች በበኩላቸው ህወሓትን "በተዘዋዋሪ" የሚረዱ እንደሆኑ መናገራቸውን ሲፒጄ የተመለከተው ሰነድ ያስረዳል። ሲፒጄ የተክለሐይማኖትን ዘገባ ቅጂ ባለማግኘቱ መገምገም እንዳልቻለም አስፍሯል።
ሲፒጄ ኢቢሲን በስልክ፣ በኢሜይልና በተለያዩ ማኅበራዊ ድረ-ገፆች ምላሽ ለማግኘት ጥረት ያደረገ ሲሆን ምላሽ እንደሚሰጡትም መናገራቸውን አስፍሯል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሐመድ ኢድሪስ በበኩላቸው ለሲፒጄ በላኩት መልዕክት የኢቢሲ ጋዜጠኞች የታሰሩት ከሥራቸው ጋር በተያያዘ እንዳልሆነ እና እስራቸውም ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ "የጥንቃቄ የደኅንነት እርምጃዎች ምክንያት ሊሆን እንደሚችል" ጠቁመዋል።
ሲፒጄ ያነጋገራቸው የተክለሐይማኖት ዘመድ እና ወዳጅ በበኩላቸው ጋዜጠኞቹ የታሰሩት ሁለቱም በኢቢሲ ውስጥ ከነበራቸው ሥራ ጋር በተያያዘና በተለይም ከሥራ እንዲታገዱ ባደረጋቸው ፕሮግራሞች እና የትግራይ ተወላጆች በመሆናቸው ነው ብለዋል።
መኮንን እና ተክለሐይማኖት ከኢቢሲ መባረራቸውን ተከትሎም በመንግሥት ሠራተኞች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ለሚዳኘው የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርበው ነበር። በተያዙበት ወቅትም ጉዳያቸውን በመጠባበቅ ላይ እንደነበሩ ዘመዶቻቸው ለሲፒጄ ተናግረዋል።
ባለፈው ሳምንት ሲፒጄ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት ዘጠኝ ጋዜጠኞችን በማሰር ኢትዮጵያ ሁለተኛ ናት በሚል ሪፖርት ያወጣ ሲሆን ከሰሞኑም የተወሰኑት ጋዜጠኞች ያሉበት ቦታና ሁኔታ እንደማያውቁ ቤተሰቦቻቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች ያሉበት ሁኔታ ሊታወቅና በቤተሰቦቻቸውና በሕግ አማካሪዎች ሊጎበኙ ይገባል ሲል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጠይቋል።
ኮሚሽኑ ጋዜጠኞቹን በሚመለከት ባወጣው መግለጫ በእስር ላይ የሚገኙትን የሚድያ ባለሙያዎች የክብሮም ወርቁ፣ የታምራት ነገራ፣ የመዓዛ መሐመድ እና የእያስፔድ ተስፋዬን ጉዳይ ለማወቅ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገረ መሆኑን ገልጿል።












