በእስር ላይ ያሉ ጋዜጠኞች ያሉበት ሁኔታ እንዲታወቅ ኢሰመኮ ጠየቀ

የፎቶው ባለመብት, SM
በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች ያሉበት ሁኔታ ሊታወቅና በቤተሰቦቻቸውና በሕግ አማካሪዎች ሊጎበኙ ይገባል ሲል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጠየቀ።
ኮሚሽኑ ጋዜጠኞቹን በሚመለከት ባወጣው መግለጫ በእስር ላይ የሚገኙትን የሚድያ ባለሙያዎች የክብሮም ወርቁ፣ የታምራት ነገራ፣ የመዓዛ መሐመድ እና የእያስፔድ ተስፋዬን ጉዳይ ለማወቅ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገረ መሆኑን ገልጿል።
የአሃዱ ሬዲዮ አርታኢ የሀፐነው ክብሮም ወርቁ ሁለት ወር ለሚሆን ጊዜ በአስር ላይ ቆይቶ ጉዳዩ በፍርድ ቤት ሲታይ የቆየ ሲሆን እያስፔድ ተስፋዬ፣ ታምራት ነገራ እና መዓዛ መሐመድ በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር የዋሉት ባለፈው ሳምንት ነበር።
የክብሮም ወርቁና የታምራት ነገራ ቤተሰቦች በአሁኑ ጊዜ ሁለቱ ጋዜጠኞች ስላሉበት ቦታና ሁኔታ ምንም አይነት መረጃ እንደሌላቸው በመግለጽ የደኅንነታቸው ሁኔታ እንደሚያሳስባቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ኢሰመኮ በመግለጫው በተለይ ታምራት ነገራ በፖሊስ ከተያዘ ጀምሮ፣ እንዲሁም በእስር ላይ የቆየው ክብሮም ወርቁ በፍርድ ቤት የዋስትና መብት ከተፈቀደለት በኋላ ያሉበትን ቦታና ሁኔታ በቤተሰቦቻቸው አለመታወቁ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሳስበው አመልክቷል።
ጨምሮም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሁኔታ ውስጥም ቢሆን የታሰሩ ሰዎች ያሉበት ቦታና ሁኔታ ሊታወቅና በቤተሰብ እና በሕግ አማካሪ የመጎብኘት መብታቸው ሊጣስ አይገባም ብሏል።
በመሆኑም "የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ሁለቱ ታሳሪዎች የሚገኙበትን ቦታ በአስቸኳይ ለቤተሰቦቻቸው እና ለሕግ አማካሪያቸው እንዲያሳውቁና በቤተሰቦቻቸው የመጎብኘት መብታቸው" እንዲከበርላቸው ኮሚሽኑ አጥብቆ አሳስቧል።
ኮሚሽኑ ጨምሮም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሰብአዊ መብቶችን መርኆዎችን ባከበረ መልኩ ተግባራዊ መሆኑን የሚመለከታቸው አካላት በቅርብ ሊከታተሉ እና ሊያረጋግጡ እንደሚገባ ጥሪ አቅርቧል።
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር የጋዜጠኞችን እስር አስመልክቶ ማክሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እና አገሪቱ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ እንደሚገነዘብ ገልጾ "እየጨመረ የመጣው የጋዜጠኞች እስር እንደሚያሳስበው" አመልክቷል።
ማኅበሩ ጨምሮም በአስር ላይ ያሉ ጋዜጠኞች ያሉበት ሁኔታ አለመታወቁ ተገቢውን የሕግ ጥበቃና ፍትሕ እንዳያገኙ እንደማያደርጋቸው በማመልከት፣ የሰሞኑ በጋዜጠኞች እስር በአገሪቱ "እየታየ የነበረውን የጋዜጠኝነት ትግበራ ነጻነት ወደፊት ጥላ እንዳያጠላበት ያሳስበናል" ሲል ስጋቱን ገልጿል።
የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ሲፒጄ የሰሃራ በታች ወኪል ሙቱኪ ሙሞ ባለፈው ሳምንት ውስጥ በርካታ በዩቲዩብ ላይ ባሉ መገናኛ ብዙኃን የሚሰሩ ጋዜጠኞች እስርን የተመለከቱ ሪፖርቶች እንደደረሷቸው እና ጉዳዩም እጅግ አስደንጋጭ ሆኖ እንዳገኙት ተናግረዋል።
የወጡ ሪፖርቶችን እየመረመሩ መሆናቸውን በመግለጽ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋዜጠኞችን ለእስር ኢላማ ማድረግን አጠናክሮ የሚያስቀጥል በመሆኑ የሰሞኑ እስርም ከዚሁ ጋር የሚሄዱ ናቸው ብለዋል።
ጨምረውም "ባለሥልጣናት የታሰሩ ጋዜጠኞችን እንዲፈቱ እና በርካታ ችግሮች ያሉበትን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን የፕሬስ እንቅስቃሴን ለመገደብ ጥቅም ላይ ማዋላቸውን እንዲያቆሙ ጥሪያችንን እናቀርባለን" ሲሉ ሙቱኪ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪው ተቋም ሲፒጄ ባለፈው ሳምንት ባወጣው ዓመታዊ ሪፖርት ዘጠኝ ጋዜጠኞችን በማሰር ከሰሃራ በታች ካሉ አገራት ኢትዮጵያ በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ገልጾ ነበር።
በተያያዘ ዜና የፌደራል ፖሊስ "አሸባሪውን ሸኔ በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ የተጠረጠሩ" ያላቸውን የአሶሺየትድ ፕሬስ ጋዜጠኞችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ምስላቸውና ስማቸው በቴሌቪዥን የቀረበው ጋዜጠኞች አሚር አማን፣ ቶማስ እንግዳ እና አዲሱ ሙሉነህ የተባሉ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፣ በሽብርተኛንት የተፈረጀውን ቡድን ወታደራዊ እንቅስቃሴ በመቅረጽና ቃለመጠይቅ በማድረግ መረጃ አሰባስበው ከአገር ውጪ በመላክ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነግሯል።














