ባለፈው ሳምንት በቁጥጥር ስር የዋሉት የሚዲያ ባለሙያዎች የት ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, SM
ባለፈው ሳምንት ሲፒጄ የተሰኘው የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ባወጣው ሪፖርት ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት ዘጠኝ ጋዜጠኞችን በማሰር ኢትዮጵያ ሁለተኛ ናት ባለ ማግስት ነበር በመዲናዋ አዲስ አበባ ሦስት የሚዲያ ሠራተኞች በፀጥታ ኃይሎች የተያዙት።
በቅድሚያ በቁጥጥር ስር የዋለው 'ኡቡንቱ' የተሰኘው የዩቲዩብ ሚዲያ መስራቾች መካከል አንዱ እያስፔድ ተስፋዬ ሲሆን ኅዳር 28/2014 ዓ.ም ከወላጆቹ መኖሪያ ቤት ተይዞ መወሰዱን ወላጅ እናቱ ወ/ሮ ተሻለች ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
በመቀጠልም በተመሳሳይ በበዩቲዩብ ላይ የሚቀርበው የተራራ ኔትወርክ መስራች እና ዋና አዘጋጅ ታምራት ነገራ ታኅሣሥ 01/2014 ዓ.ም ከመኖሪያ ቤቱ ተይዞ መወሰዱን ባለቤቱ ወ/ሮ ሰላም በላይ ለቢቢሲ ገልጻ ነበር።
ሦስተኛዋ ደግሞ ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ ናት። ቅዳሜ ታኅሣስ 02/2014 ዓ.ም ከወላጅ አባቷ ቤት በቁጥጥር ስር መዋሏን ታላቅ እህቷ አገኘሁወርቅ አበበ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
ሁሉም ጋዜጠኞች በቁጥጥር ስር የዋሉት ጠዋት ረፋድ ላይ ከመኖሪያ ቤታቸው ሲሆን መኖሪያ እና የሥራ ቦታዎቻቸው ተፈትሸዋል። እንዲሁም ፖሊስ በኤግዚቢትነት የኮምፒውተር ሃርድ ዲስኮችን፣ የድምጽ መቅጃ መሳሪያዎችን እንዲሁም ካሜራዎችን ይዞ ሄዷል ሲሉ ቤተሰቦች ገልጸዋል።
ከሁለት ወር በፊት በቁጥጥር ስር ውሎ የነበረው እና ትላንት ሰኞ ታኅሣሥ 04 ፖሊስ በችሎት ቀርቦ "ፈትቼዋለሁ" ያለው የአሃዱ ሬዲዮ ጋዜጠኛው ክብሮም ወርቁን ጨምሮ አራቱ ጋዜጠኞች የት ናቸው ስንል ጠይቀናል።
ታምራት ነገራ
ታምራት በቁጥጥር ስር ከዋለ ጀምሮ ላለፉት አምስት ቀናት የት እንዳለ እንዳላወቁ እና በተለያዩ የፖሊስ ጣቢያዎች ቢያፈላልጉትም ታምራትን አየሁ የሚል እንደሌለ ባለቤቱ ሰላም በላይ ለቢቢሲ ተናግራለች።
በቁጥጥር ስር በዋለበት ወቅት የወሰዱት የፌደራል ፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱ ሰዎች እንደነበሩ የምትናገረው ሰላም ትላንት ሰኞ በድጋሚ ሚክሲኮ የሚገኘው የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ፣ እንዲሁም የአዲስ አበባ ፖሊስ ሄደው መጠየቃቸውን እና ታምራት የት እንዳለ "ፍንጭ እንኳን የሚሰጠን ሰው አላገኘንም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ኦሮሚያ ፖሊስ ጋር ነው የሚገኘው የሚል መረጃ እንደደረሳቸው ቅዳሜ እና እሁድን በተለያዩ የፊንፊኔ ዙሪያ ከተሞች ባሉ ፖሊስ ጣቢያዎች ዞረው ቢፈልጉም አላገኙትም።
"ኦሮሚያ ፖሊስ ነው ካሉን ጀምሮ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ፖሊስ መምሪያ፣ ቡራዩ እና ገላን አካባቢ ያሉ ጣቢያዎች ጋር ሁሉ ዞረን አፈላልገነዋል" የምትለው ሰላም "ወደዚያ ወደዚህ ከማለት ውጪ ምንም የተፈጠረ ነገር የለም" ብላለች።
ሰላም መንግሥት አንድን ሰው ጥያቄ ካለው ለምን ወስዶ ይጠይቃል የሚል አቋም እንደሌላትና ባለቤቷም በቁጥጥር ስር በዋለበት ወቅት ሕጋዊ ሰዎች ናቸው የመጡት በሚል "ያለምንም ማጉረምረም ነው ተነስቶ የሄደው" ብላለች።
"ለቤተሰብ አባል ከእጁ ላይ ተወስዶ ሲሄድ እና የት እንዳለ ማወቅ አለመቻል ከባድ ነው። ይዘውት የሄዱትን ባለሞያዎች የት እንደወሰዱት ስንጠይቅ አናውቅም ነው ያሉት። ለአንድ እናት ልጇ የመንግሥት አስከባሪዎች ወስደው የት እንደሆነ አለመንገር ምን ማለት ነው?" ሲሉ ይጠይቃሉ።
ቤተሰባቸው ከባድ ጭንቀት ውስጥ እንዳለ እና የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንን ጨምሮ ለሚመለከታቸው ተቋማት ደብዳቤ ማስገባታቸውን፣ ነገር ግን እስካሁን ታምራት እዚህ ጋር ነው የሚል አለመገኘቱን ተናግራለች።
ባለቤቷን አስከምታገኝ ድረስ ከመፈለግ እንደማትደክም የምትናገረው ሰላም "አለ የሚሉት ቦታ፤ ብሎም መጀመሪያ የወሰዱት የሕግ ሰዎች ጋር በየቀኑ መሄዳችንን አናቆምም" ብላለች።
የተለያዩ ጫና ይፈጥራሉ ተብለው የሚታመኑ የመንግሥት ተቋማት ጋር እርዳታ መጠየቅ ብሎም ለመገናኛ ብዙኃን መናገሯን እንዳማታቆምም አክላለች።
"መንግሥትን ግን የምንጠይቀው፣ መመርመር የመንግሥት መብት ነው። ግን እዚህ ጋር ነው ያለው ብለው መንገር፤ እናት ለልጇ ምግብ እና ልብስ ማቀበል፤ ባለቤቴን መጠየቅ ደግሞ የእኛ መብት ነው። በሕይወት አለ ወይ? ካለ የት ነው? በሕይወት መኖሩን ማወቅ እፈልጋለሁ። ኬሌለም በግልጽ በሕይወት የለም ብለው እንዲነግሩኝ እፈልጋለሁ" ስትል ሰላም ጠይቃለች።
ክብሮም ወርቁ
ክብሮም በአሃዱ ራዲዮ የዜና ክፍል አዘጋጅ ሲሆን በተለይም በራዲዮው ላይ በሚያቀርበው የመዝናኛ ፕሮግራሞች ይታወቃል። ክብሮም ጥቅምት 16/2014 ዓ.ም "ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት" ወንጀል ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን፣ ይህም በራዲዮ ጣቢያው የሐይቅ ከተማ በህወሓት ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር ውላለች የሚል ዘገባ መሰራቱን ተከትሎ መሆኑ ይታወሳል።
ቢቢሲ ላለፈው አንድ ወር ገደማ ልጃቸው የት እንዳለ እንደማያውቁ ለፍርድ ቤት የተናገሩትን ወላጅ አባቱን በስልክ አነጋግሯል። ክብሮም መጀመሪያ ታስሮ የነበረው በተለምዶ ሦስተኛ የሚባለው የአዲስ አበባ ፖሊስ የነበረ ሲሆን ያኔ ጥየቃ እንደሚፈቀድ እና ከሩቅ ሰላምታ እንደሚለዋወጡ ብሎም ምግብ ሲያቀብሉት እንደነበር ተናግረዋል።
ነገር ግን ፍርድ ቤት ኅዳር 09/2014 ዓ.ም በ15 ሺህ ብር ዋስትና እንዳሰናበተው እና እርሳቸውም ገንዘቡን መክፈላቸውን ተናግረዋል። ለአንድ ሳምንት ያህል ይፈታል ብለው ቢጠብቁም ባለመፈታቱ ለችሎት መማልከታቸውን እና ፖሊስ ይግባኝ መጠየቁን ለችሎት በመግለጹ በእስር መቆየቱን ተናግረዋል።
ነገር ግን ይግባኙ ውድቅ መደረጉን እና ይፈታ ብሎ ፍርድ ቤቱ ቢወስንም ልጃቸው አለመፈታቱን ተናግረዋል።
"ስናስቸግራቸው ይፈታል አሉ። ከዚያም እንዲፈታ ለመረከብ መታወቂያዬን ሰጠሁ፤ የሚፈረሙ ነገሮችን ፈረምኩ። ውጪ ጠብቁ አሉ፤ ነገር ግን ይዘውት በሚኒባስ ሄደዋል" ሲሉ ይናገራሉ።
ከዚያም ቤተሰቦቹ ለፌደራሉ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት አካልን ነጻ የማውጣት ክስ ማስገባታቸውን እና ችሎቱ አቤቱታቸውን ውድቅ አድርጎት እንደነበረ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበው ነበር።
በይግባኝ ክሱን ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የወሰዱት የክብሮም ቤተሰቦች ፖሊስ ትላንት ታኅሣሥ 04/2014 ዓ.ም ለምን እንዳልፈታ እንዲያብራራ ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር።
ፖሊስ ለችሎቱ በጽሁፍ ይዞት በመጣው መልስም ክብሮምን ኅዳር 09/2014 ዓ.ም ለቅቄዋለሁ ሲል ገልጿል። የክብሮም ወላጅ አባት በችሎት ቀርበው ፖሊስ ይህንን ቢልም ልጃቸውን እንዳላገኙት እንዲሁም ካዩት እንኳን አንድ ወር ሊሞላው መሆኑን ተናግረዋል።
አባት የልጃቸውን ጉዳይ በተመለከተም ለኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚሸን እና እምባ ጠባቂ ኮሚሽን ማመልከታቸውን እና እስካሁን መልስ እንዳላገኙ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ክብሮም የልብ ቀዶ ህክምና አድርጎ ነበር። መኝታም ሆነ ምግብ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት። ከዚህ በኋላ ተስፋችን ፈጣሪ ብቻ ነው" ሲሉ አባቱ ክብሮም ስላለበት የጤና ሁኔታ ገልጸዋል።
እያስፔድ ተስፋዬ
እያስፔድ በቁጥጥር ስር በዋለበት ዕለት ኡቡንቱ የተሰኘው ሚዲያው ወደሚገኝበት ቢሮ ፖሊሶች ይዘውት መሄዳቸውን እና ብርበራ ተደርጎ ካሜራዎችን ጨምሮ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ይዘው መሄዳቸውን ባልደረቦቹ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በተጨማሪም እያስፔድ ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ እንደሚገኝ እና እሁድ ጠዋት ብሎም ማክሰኞ በተወሰኑ ወዳጆቹ መጎብኘቱም ታውቋል።
እያስፔድ በቁጥጥር ስር ከዋለ ሰባት ቀናት የተቆጠረ ሲሆን እስካሁን ድረስ ፍርድ ቤት አለመቅረቡን ብሎም ጠበቃ እንዲቆምለት በቤተሰቦቹ ጥረት ቢደረጉም በቁጥጥር ስር የዋለው ከአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ በመሆኑ ጠበቃ ሊቆምለት እንደማይችል እንደተነገራቸው እናቱ ገልጸዋል።
መዓዛ መሐመድ
ጋዜጠኛ መዓዛ በቁጥጥር ስር ከዋለች በኋላ በመኖሪያ ቤቷ ብሎም በሥራ ቦታዋ ላይ ፍተሻዎች መደረጋቸውን ቤተሰቦቿ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከተመሰረተ ገና አጭር ጊዜ የሆነው እና እስካሁን ሁለት ቪዲዮዎችን ብቻ በዩቲዩብ ላይ ያወጣው ሮሃ የተሰኘው የመዓዛ ሚዲያ ውስጥ ያሉ ኮምፒውተሮች ሃርድ ዲስካቸው ብሎም ሌሎች ቁሳቁሶች በፖሊስ መወሰዳቸው ታውቋል።
የመዓዛ ወንድም ዩሱፍ መሐመድ እንዳለው ዕሁድ ጠዋት ቤተሰቦቿ ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ሄደው እንደጠየቋት ይናገራል።
መዓዛ የሥራ ሕይወቷን ስትጀምር መምህር እንደነበረች እና የሰማያዊ ፓርቲ አባል ሆና እስከሚፈርስ ድረስ ስትሳተፍ እንደነበር ወንድሟ ይናገራል። ከዚያም በፖለቲካ ፓርቲ ተሳትፎ ውስጥ መቆየቷን እና ቀጥሎም አባይ ሚዲያን መቀላቀሏን ዩሱፍ ለቢቢሲ ተናግሯል።
"እሷ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የበጎ አድራጎት ሥራ ላይ እንጂ የሚዲያ ሥራ ላይ ብዙም አትሳተፍም ነበር። የታሰረችበት ፖሊስ ጣቢያ ከመታሰሯ ከአንድ ቀን በፊት ሄዳ እስረኞችን ስትጠይቅ ነበር። በአማራ ክልል ጦርነቱን ተከትሎ የተደፈሩ ሴቶችን ማንም ሳይሰራ ሄዳ ስታናግር ነበር። እርዳታ ይዛ ሄዳ ማከፋፈል ላይ ነበር የተጠመደችው" ሲል ወንድሟ ተናግሯል።
በሥራ ቦታዋ ላይ ከተደረገው ብርበራ እና በኤግዚቢትነት የተወሰዱ የኮምፒውተር ሃርድ ዲስኮች እና መሳሪያዎችን በመመልከት ግን ከሥራዋ ጋር የተገናኘ እስር መሆኑን ይናገራል። መዓዛ እስካሁን ድረስ ፍረድ ቤት እንዳልቀረበች እና ጠበቃም እንዳልቆመላት ዩሱፍ ይናገራል።
መዓዛ የልጅ እናት ከመሆኗ ባሻገር ቤተሰቦቿን በዋናነት የመትደግፍ በመሆኗ እስሯ ለመላው ቤተሰቧ ጫና ይዞ መምጣቱን ወንድሟ ተናግሯል።
የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ሲፒጄ ምን አለ?
የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ሲፒጄ የሰሃራ በታች ወኪል ሙቱኪ ሙሞ ባለፈው እንድ ሳምንት ውስጥ በርካታ በዩቲዩብ ላይ ባሉ መገናኛ ብዙኃን የሚሰሩ ጋዜጠኞች እስርን የተመለከቱ ሪፖርቶች እንደደረሷቸው እና ጉዳዩንም እጅግ አስደንጋጭ ሆኖ እንዳገኙት ተናግረዋል።
"ሪፖርቶቹን ገና እየመረመርን ነው። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ በኋላ ጋዜጠኞችን ለእስር ኢላማ ማድረግን አጠናክሮ የሚያስቀጥል ሲሆን የሰሞኑ እስሮችም ከዚሁ ጋር የሚሄዱ ናቸው። ባለሥልጣናት የታሰሩ ጋዜጠኞችን እንዲፈቱ እና በርካታ ችግሮች ያሉበትን የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ሕግ የፕሬስ እንቅስቃሴን ለመገደብ ጥቅም ላይ ማዋላቸውን እንዲያቆሙ ጥሪያችንን እናቀርባለን" ሲሉ ሙቱኪ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ተወካይዋ አክለውም መንግሥት የዜጎቹን ደኅንነት የማስከበር ቀዳሚ ኃላፊነት እንዳለበት እና ጋዜጠኞችም ሥራቸውን በሚሰሩበት ወቅት ጥበቃ ሊደረግላቸው እንጂ ጥቃት ሊደርስባቸው እንደማይገባ ተናግረዋል።
"ነገር ግን ጋዜጠኞች ሥራቸውን በሚሰሩበት ወቅት የአደጋ ዳሰሳ እንዲያደርጉ እና ምንጮቻቸውን ብሎም ራሳቸወን ከአደጋ ለመከላከል የሚያስችሉ ጥንቃቄዎችን እንዲያደርጉ እናበረታታለን።"
ለዚህም ሲፒጄ በድረ-ገፂ ላይ ለጥንቃቄ የሚረዱ መረጃዎች ያሉ ሲሆን አንዳንዶቹን ወደ ኢትዮጵያ ቋንቋዎች እንደተተረጎሙ አመልክተዋል።
ጨምረውም "ጋዜጠኞች እንታሰራለን የሚል ስጋት ካላቸው ባለሞያዎቻችን እንደ ጉዳዩ አይነት አንድ ለአንድ ውይይት ሊያናግራቸው ይችላሉ" ሲሉ ሙቶኪ ተናግረዋል።
ከመንግሥት በኩል ስለጋዜጠኞቹ እስርና ሁኔታ አስካሁን የተሰጠ ምንም ማብራሪያ የለም።
ቢቢሲ ከፖሊስም ሆነ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት የታሰሩት ጋዜጠኞች ያሉበትን ሁኔታ ለመጠየቅ ያደረገው ሙከራ አልተሳካለትም።















