እያስፔድ ከወላጆቹ ቤት በፖሊስ ተይዞ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ወላጅ እናቱ ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Eyasped Tesfaye/Facebook
አክቲቪስት እያስፔድ ተስፋዬ ከወላጆቹ መኖሪያ ቤት በፖሊስ መያዙን ወላጅ እናቱ ለቢቢሲ ገለጹ።
ማክሰኞ ሲቪል እና የአዲስ አበባ ፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱ ሰዎች መኖሪያ ቤታቸውን ለሰዓታት ከፈተሹ በኋላ እያስፔድን ይዘው መሄዳቸውን ወላጅ እናቱ ወ/ሮ ተሻለች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ፖሊሶች ኅዳር 28/2014 ዓ.ም ረፋድ ከ3፡30 እስከ 7 ሰዓት ድረስ እያስፔድ የሚኖርበት የወላጅ እናቱ መኖሪያ ቤትን ከበው ከፈተሹ በኋላ እያስፔድን ይዘውት እንደሄዱ ተናግረዋል።
የፀጥታ አካላቱ እያስፔድን በምን ምክንያት በቁጥጥር ሥር እንዳዋሉት እንዳልተነገራቸው እና ጥያቄ በሚያርቡበት ወቅት "ሲቆጡ" እንደነበረ የእያስፔድ እናት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ስጠይቃቸው ቆጣ ቆጣ ይላሉ። የእኔ እና የእነሱ መጋጨት ልጄን ያስጨንቀብኛል ብዬ ዝም አልኩ" በማለት ለፀጥታ አካላቱ እያስፔድን ለምን ይዘው እንደሚሄዱ አጥብቀው ከመጠየቅ መቆጠባቸውን ተናግረዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው እና ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ሌላ የእያስፔድ የቤተሰብ አባል ከአዲስ አበባ ፖሊስ የመጡ የፀጥታ ኃይሎች በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ ፍተሻ ማካሄዳቸውን እና በመጨረሻም እያስፔድ ለጥያቄ እንደሚፈለግ በመጥቀስ ይዘውት እንደሄዱ ተናግረዋል።
ይህ የቤተሰብ አባል እንደሚሉት የፀጥታ ኃይል አባላቱ ፍተሻ ከማድረጋቸው በፊት ለረጅም ሰዓታት ትዕዛዝ እየጠበቁ እንደሆነ በመናገር ሲጠባበቁ መቆየታቸውን ይናገራሉ።
ይህ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የቤተሰብ አባል እያስፔድ በቁጥጥር ሥር የዋለው ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ ሳይሆን እንደማይቀር ግምታቸውን ሰጥተዋል።
እያስፔድ በምን ምክንያት በቁጥጥር ሥር እንደዋለ ለመጠየቅ የአዲስ ፖሊስ ኮሚሽንን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ስልክ ባለማንሳታቸው ሳይሳካ ቀርቷል።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ቃል አቀባይ ጄይላን አብዲ በጉዳዩ ላይ መረጃ እንደሌላቸው እና አጣርተው እንደሚገልጹልን ነግረውናል።
ተፈጻሚ እየሆነ በሚገኝ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያትም የፀጥታ አባላቱ መኖሪያ ቤታቸውን ለምን እንደሚፈትሹ እና የፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንደያዙ መጠየቅ አለመቻላቸውን የእያስፔድ እናት ጨምረው ይናገራሉ።
የፀጥታ አካላቱ ከብዙ ሰዓት ፍተሻ በኋላ እያስፔድ የሚጠቀምባቸውን ላፕቶፕ ኮምፒዩተር እና ሞባይል ስልክ መውሰዳቸውን ተናግረዋል።
"እኔ እግሬን ተሰብሬ እያከመኝ ነበር። ወደ ቤት ውስጥ ከገቡ በኋላ ጥያቄ እየጠየቁት እሱም ሲመልስላቸው ነበር። መኝታ ቤት ስለነበርኩ ምን እንደሚባባሉ በትክክል አልሰማሁም" ይላሉ የእያስፔድ እናት።
የፀጥታ አካላቱ እያስፔድን ወደ 'አዲስ አበባ ፖሊስ' ይዘውት እንደሚሄዱ ከተናገሩ በኋላ እህቱ የፖሊስ አባላቱን ተከትላ እያስፔድ የት እንደታሰረ አረጋግጣ መመለሷን ወላጅ እናቱ ይናገራሉ።
እያስፔድ ማን ነው?
እያስፔድ ለበርካታ ዓመታት በተቃውሞ ፖለቲካ እና በማኅበራዊ ሚዲያ አንቂነት ይታወቃል።
እያስፔድ በሚያራምደው የፖለቲካ አቋም ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ መታሰሩን የቅርብ ጓደኞቹ ይናገራሉ።
ከስምንት ዓመት በፊት የሰማያዊ ፓርቲ አባል በነበረበት ወቅት ከሌሎች የፓርቲው አባላት እና አመራሮች ጋር እንዲሁም በ2009 የታወጀውን የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ተከትሎ ለእስር ተዳርጎ ነበር።
በቅርብ በተቋቋመው እና 'ኡቡንቱ' በተሰኘ ዩቲዩብ ላይ በሚተላለፈ ሚዲያ ላይ እየሰራ ይገኛል።












