በትግራይ ጦርነቱ ሲጀመር የመጀመሪያው የአሜሪካ መልዕክተኛ ትውስታ ከዓመት በኋላ

የአሜሪካው ሴናተር ክሪስ ኮንስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካው ሴናተር ክሪስ ኮንስ

ትግራይ ውስጥ ጦርነቱ ሲጀመር የአሜሪካ መንግሥት የመጀመሪያው መልዕክተኛ ሆነው ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩት ሴናተር ክሪስ ኩንስ በወቅቱ ስላደረጉት ጥረትና ጦርነቱ አሁን ስላለበት ሁኔታ ከቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ጋር አጭር ቆይታ አድርገው ነበር።

ከአንድ ዓመት በፊት በጦርነቱ መጀመሪያ አካባቢ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ተገናኝተው የአገራቸው የአሜሪካንን የእርስ በእርስ ጦርነት እንደ ምሳሌ በጥቀስ መክረው እንደነበር የሚያስታውሱት ሴናተሩ (የምክር ቤት አባል) ጦርነቱ በቶሎ መፍትሄ እንዲፈለግለት መክረው እንደነበር ተናግረዋል።

"የህወሓት ኃይሎች በትግራይ በሚገኙ የፌደራል ወታደራዊ ተቋማት ላይ ያደረሱትን ጥቃት ተከትሎ በምላሹ ጥቃት ለመሰንዘር እየተዘጋጁ ሳለ ነበር የተነጋገርነው" ሲሉ ሴናተሩ አስታውሰዋል።

ጨምረውም፤ "በእኛ በአሜሪካ ታሪክ የእርስ በእርስ ጦርነት መጀመሪያው ላይ በሁለቱም ወገኖች ያሉ ጀነራሎች ጦርነቱ ጥቂት ሳምንታት ብቻ እንደሚወስድ እና እንደሚያልቅ ገምተው እንደነበር ነግሬያቸዋለሁ" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጦርነቱ "ህመም ሳይፈጥር በቀላሉ እንደሚያልቅ" ይገምቱ እንደነበር የገለጹት ሴናተሩ፤ "በትግራይ በህወሓት ላይ የሚካሄደው መልሶ ማጥቃት ጥቂት ሳምንታት ብቻ እንደሚወስድ ነግረውኝ ነበር። የተወሰኑ ግለሰቦችን ለመያዝ እንጂ የእርስ በእርስ ጦርነት እንዳልሆነ ገልጸውልኝ ነበር" ሲሉም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የአሜሪካ የእርስ በእርስ ጦርነት ለዓመታት እንደቀጠለ ገልጸው፤ የሰሜኑ ጦርነትም እንደተገመተው በሳምንታት ሳያልቅ አንድ ዓመት እንዳለፈው በአጽንኦት ተናግረዋል።

"በአገራችን ታሪክ እጅግ ደም ያቃባ እና ውድመት ያደረሰ ጦርነት ነው" ሲሉ ስለ አሜሪካው የእርስ በእርስ ጦርነት አስከፊነት አስረድተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሐሳብ ለማስቀየር ይህንን የአገራቸውን የእርስ በእርስ ጦርነት ታሪክ ቢነግሯቸውም የተለወጠ ነገር እንደሌለ ከፎከስ ኦን አፍሪካ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኩንስ ገልጸዋል።

ሁለቱም ወገኖች፣ በዋነኛነት ኤርትራ እና ሌሎችም የቀጠናው ሚሊሻዎች እንዲሁም ሌሎችም ወገኖች ጦርነቱን አስከፊ እንዳደረጉት ሴናተር ክሪስ ኮንስ ጠቅሰዋል።

"አንድ ዓመት አልፎ ስናየው አሁን ጦርነቱ መፈናፈኛ የሌለው ነጥብ ላይ ደርሷል" ሲሉም በአገሪቱ አሁን ስላለው ሁኔታ ጠቅሰው ለዚህ ጦርነት ወታደራዊ መፍትሔ እንደሌለ እና ሁለቱም ወገኖች ለውይይት ወደ ጠረጴዛው እንዲመጡ አሳስበዋል።

የሌሎች አገራት ሚና

ከጦርነቱ ጀርባ ሌሎች አገራት ጣል ገብተው ጦርነቱን እያስፋፉት ነው ብለው የሚያምኑት ኩንስ፣ ሌሎች የውጭ ኃይሎች "ጦርነቱን እያባባሱት ነው" ይላሉ።

ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) እና ሌላም ወታደራዊ መሣሪያ ድጋፍ እያደረጉ ያሉ የውጭ ኃይሎች ጦርነቱን እያባባሱት እንደሚገኙ አስረድተዋል።

በተለያዩ አገራት የውጭ ኃይሎች የሚያደርጉት የእጅ አዙር ጦርነት (ፕሮክሲ ዋር) ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ ለማስረዳት የየመን እና የሊቢያን ጦርነት ጠቅሰዋል።

የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት አንድ ቀን ማክተሙ እንደማይቀር እና ጦርነቱ ሲያልቅም የሰብአዊ መብት ጥሰትን "የደገፉ ወይም ያመቻቹ ተጠያቂ ሊደረጉ ይገባል" ሲሉም ሴናተሩ አክለዋል።

በአሜሪካ ኮንግረስ በሁለቱም ወገኖች [በዴሞክራቶች እና በሪፐብሊካኖች] ተቀባይነት ያለው፣ የሰብአዊ መብትን የሚጥሱ ላይ ማዕቀብ የሚጥል እና ለሰሜኑ ጦርነት ፖለቲካዊ መፍትሔ የሚደግፍ ሕግ ማቅረባቸውንም አያይዘው ጠቁመዋል።

የአሜሪካው ሴናተር ክሪስ ኩንስ ጨምረውም የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ኢትዮጵያ ላይ የመፍረስ አደጋ የጋረጠ እንደሆነ ከቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

አሁን ላይ ጦርነቱ ያለበት ሁኔታ ወደ ሰላማዊ ድርድር የሚያመራ ሳይሆን የሚከፋፍል እንደሆነ ገልጸው "ይህም ወደ ዘር ጭፍጨፋ ሊያመራ ይችላል" ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በመላው ኢትዮጵያ በብሔር የተደራጁ ሚሊሻዎች መኖራቸው እንዲሁም በክልሎች መካከል ተከታታይ ግጭቶች እና ውጥረቶች መስተዋላቸውን እንደ ማስረጃ ጠቅሰዋል።

"ይህም በሚያሳዝን ሁኔታ በቲቶ [የቀድሞው የዩጎዝላቪያ ፕሬዝዳንት ጆሲፕ ብሮዝ ቲቶ] ሞት ወቅት የነበረችውን ዩጎዝላቪያ ያስታውሰኛል" ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ግን አንድ ዓመት ባስቆጠረው ጦርነት የአገሪቱን አንድነት ለማስቀጠል ተገዶ መግባቱን በተደጋጋሚ ይገልጻል። ህወሓት በተመሳሳይ በዚህ ጦርነት ተሳታፊ የሆንኩት የትግራይ ሕዝብ ህልውናን ለማስጠበቅ ነው ይላል።

ሴናተሩ በጦርነቱ ተሳታፊዎች ስለ ሌሎች ብሔር ተወላጆች አደገኛ ነገሮች መባላቸው እና ማኅበራዊ ሚዲያም ይህንን ለማባባስ መዋሉም እጅግ እንደሚያሳስባቸው የአሜሪካው ሴናተር ለቢቢሲ ገልጸዋል።

"ማኅበራዊ ሚዲያ ነውጠኛ አገላለጾችን ለማስተጋባት እየዋለ ነው። ይህም ያሳስበኛል። ያለነው የሰላም ድርድር ላይ ሳይሆን የሚከፋፍል ግጭት ውስጥ ነው። ይህም ወደ ዘር ጭፍጨፋ ሊያመራ ይችላል" ብለዋል።

ሰብአዊ ቀውስ

በሁሉም የጦርነቱ ተሳታፊዎች የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና ውድመቶች እንደሚያስባቸው የሚናገሩት ሴናተር ክሪስ ኩንስ ጦርነቱ ከባድ ሰብአዊ ቀውስ ፈጥሯል ይላሉ።

በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ በህወሓት፣ በአማራ ሚሊሻ፣ በኤርትራ ወታደሮች የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸው እንደማይካድም ሴናተሩ አክለዋል።

"መድፈር እንደ ጦር መሣሪያ ውሏል። ንጹሀን ዜጎች ተጨፍጭፈዋል። ታሪካዊ ቦታዎችን ወድመዋል። እጅግ አሳሳቢው የሆነው ግን ረሃብ እንደ ጦር መሣሪያ መዋሉ ነው" ብለዋል።

አሁን በሚሊዮን የሚገመቱ ዜጎች ሰብአዊ እርዳታ የሚሹ መሆናቸው እና 400 ሺህ ሰዎች በረሃብ አፋፍ ላይ መገኘታቸው እጅግ እንደሚያሳስባቸውም ተናግረዋል።

በጦርነቱ ሳቢያ ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ በግልጽ ባይታወቅም በበርካታ ሺዎች እንደሚቆጠሩ ይገመታል።

የመሠረተ ልማት አቅርቦት ላይ ከደረሰው ውድመት ባሻገር፤ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ አስቸኳይ የሰብአዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር ወደ 9.4 ሚሊዮን መድረሱን የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስታውቋል።