በህወሓት ተይዘው በነበሩ ቦታዎች በሰው እና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, PMO
የህወሓት አማጺያን ተቆጣጥረው በቆዩባቸው የአፋር እና የአማራ ክልል አካባቢዎች በሰው እና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ተናገሩ።
"በግል እና በሕዝብ ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፤ የበርካታ ሰዎች ሕይወት አልፏል" ሲሉ ቢልለኔ ዛሬ ማክሰኞ ኅዳር 28/2014 ዓ.ም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ ተናግረዋል።
እንደ አብነትም ፕሬስ ሴክሬታሪያዋ በመዘዞ፣ በካሳጊታ፣ በደብረሲና፣ በሸዋ ሮቢት፣ በጋሸና እንዲሁም በላሊበላ አየር ማረፊያ በህወሓት ኃይሎች ደርሷል ያሉትን የንብረት ውድመት የሚያሳይ ምስል ለጋዜጠኞች አሳይተዋል።
ምስሎቹ በግለብ መኖሪያ ቤቶች፣ በባንኮች፣ በንግድ እና ጤና ተቋማት ንብረት ላይ የደረሰውን ከባድ ውድመት የሚያሳዩ ናቸው።
በንብረት ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ በንጹሃን ዜጎች ላይ ከባድ የመብት ጥሰቶች በበርካታ ቦታዎች ስለመፈጸማቸው የሚያመላክቱ ምልክቶች እየወጡ ነውም ብለዋል።
"በጋሸና እና በሰሜን ሸዋ በምትገኘው አንጾኪያ ህወሓት በንጹሃን ላይ የጅምላ ግድያዎች ስለመፈጸሙ ሪፖርቶች አሉ" ብለዋል ፕሬስ ሴክሬታሪዋ።
በንጹሃን ላይ ተፈጽሟል ከተባለው ግድያ በተጨማሪ የአስገድዶ መድፈር ጥቃቶች መፈጸማቸውን አመልክተው፣ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚመረምር ቡድን በአካባቢዎቹ መረጃ እያሰባሰበ ነው ብለዋል።
በተመሳሳይ ትናንት የመንግሥት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ ሰላማዊት ካሳ በሰጡት መግለጫ ላይ በህወሓት ተፈጽመዋል ያሉትን ወንጀሎች ተናግረዋል።
ሚኒስትር ዲኤታዋ በጋሸናና በሰሜን ሸዋ አንጾኪያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ዜጎችን በጅምላ መገደላቸውን የሚያረጋግጡ መረጃዎች አሉ ብለዋል።
ሰላማዊት ካሳ ህወሓት ከዚህ ቀደም በጭና፣ በጋሊኮማ፣ በአጋምሳ፣ በቆቦ፣ በዉርጌሳ፣ በውጫሌ እና በኮምቦልቻ የጅምላ ግድያዎችን ፈጽሟል ያሉ ሲሆን፤ እነዚህን በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን "በገለልተኛ ቡድን በማጣራት ዓለም እውነቱን እንዲገነዘብ ማድረግ ይገባል" ሲሉ ተናግረው ነበር።

ፕሬስ ሴክሬታሪዋ ቢልለኔ ስዩም ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ ላይ፤ ደሴ እና ኮምቦልቻ በመንግሥት ኃይል መያዛቸው ለህወሓት "ከፍተኛ ኪሳራ ነው" ብለዋል።
ከቀናት በፊት ወደ 12 የሚጠጉ የህወሓት ከፍተኛ የጦር አመራሮች ላይ እርምጃ መወደሱ የኢትዮጵያ መንግሥት ላስገኘው ድል አንዱ ምክንያት ነው ሲሉም ቢልለኔ ተናግረዋል።
የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት
ቢልለኔ የፌደራል አደጋ ስጋት እና መከላከል ኮሚሽንን በመጥቀስ ከትግራይ ወደ ሌሎች ክልሎች የተስፋፋውን ጦርነት ተከትሎ በአማራ ክልል የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር 1.4 ሚሊዮን መድረሱን ተናግረዋል።
ፕሬስ ሴክሬታሪዋ ከሳምንት በፊት በሰጡት መግለጫ የተፈናቃዮች ቁጥር 1.1 ሚሊዮን እንደነበረ ተናግረው ነበር።
በሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ እና ሰሜን ሸዋ ለሚገኝ 2 ሚሊዮን ሕዝብ የፌደራሉ መንግሥት 28 ሺህ ሜትሪክ ቶን ምግብ መመደቡን ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ ተሸርካሪዎች በቅርቡ ከህወሓት ቁጥጥር ነጻ ወደወጡት ጋሸና እና ላሊበላ ከተሞች መንቀሳቀስ መጀመራቸውን ተናግረዋል።
በአፋር 1.3 ሚሊዮን ሕዝብ አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልገዋል ያሉ ሲሆን በግጭቱ ምክንያት በክልሉ ከ400 ሺህ በላይ ሕዝብ ተፈናቅሏል ብለዋል። በተመሳሳይ በአፋርም የሰብዓዊ እርዳታ ለማቅረብ መንግሥት ከአጋር ድርጅቶች ጋር የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ቢልለኔ ጠቅሰዋል።
በትግራይ ደግሞ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ በረራ ወደ መቀለ ማደረግ መጀመሩን አስታውሰው፤ እስካሁን ድረስ ከአዲስ አበባ - መቀለ 4 ደርሶ መልስ በራዎች መደረጋቸውን እንዲሁም የሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ 203 ተሸርካሪዎች መቀለ መድረሳቸውንም ፕሬስ ሴክሬታሪዋ ተናግረዋል።
የሰብዓዊ እርዳታ ጭነው ወደ ትግራይ ያቀኑ ተሸከርካሪዎች እንዲመለሱ በህወሓት በኩል ፍላጎት አለመኖሩን ተናግረው ህወሓት ተዋጊ ኃይሎቹን ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቀስ ተሽከርካሪዎቹን ጥቅም ላይ እያዋለ ነው ብለዋል።
አንድ ዓመት ካለፈው በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር ወደ 9.4 ሚሊዮን መድረሱን የዓለም ምግብ ፕሮግራም በቅርቡ መሳወቁ ይታወሳል።
ድርጅቱ ጨምሮም በሰሜን ኢትዮጵያ በሚገኙት የትግራይ፣ የአማራ እና የአፋር ክልሎች ወስጥ የሚገኙ 9.4 ሚሊዮን ሰዎች አስከፊ ሕይወት እየገፉ መሆናቸውን አመለክቶ፣ ከእነዚህ መካከል 80 በመቶው ወይም 7.8 ሚሊዮን የሚሆኑት በጦርነቱ ምክንያት ሰብአዊ እርዳታ ማድረስ አዳጋች የሆኑባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ሰዎች ናቸው ብሎ ነበር።












