አሜሪካ ከኦሊምፒክ መቅረቷ ዋጋ ያስከፍላታል ስትል ቻይና አስጠነቀቀች

የቤጂንግ ኦሎምፒክ እንቅር የሚል ሰንደቅዓላማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አሜሪካ በአውሮፓውያኑ 2022 ቤጂንግ በሚካሄደው የክረምት ኦሎምፒክ ዲፕሎማቶቿ እንደማትልክ ማስታወቋን ተከትሎ ይህ ውሳኔዋ ዋጋ ያስከፍላታል ስትል ቻይና ዛተች።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ዛሆ ሊጂያን ዝርዝር መረጃ ሳይሰጡ ቻይና ለአሜሪካ ውሳኔ የአጸፋ ምላሽ ትሰጣለች ሲሉ ተናግረዋል።

ትናንት ሰኞ አሜሪካ ከቻይና የሰብአዊ መብት አያያዝ ጋር በተያያዘ ነው ዲፕሎማቶቿን ለኦሊምፒክ ውድድሩ እንደማትልክ ያስታወቀችው።

ይህንንም ስጋቷን ለመግለፅ ምንም ዓይነት ኦፊሴላዊ ልዑካን ወደ ውድድሩ እንደማትልክ ኋይት ሃውስ አስታውቋል።

ሆኖም የአሜሪካ ስፖርተኞች መወዳደር እንደሚችሉ እና የመንግሥትን ሙሉ ድጋፍ እንደሚያገኙ ተነግሯል።

ከዚህ ቀደም አሜሪካ ያለመሳተፍ ውሳኔ ካስተላለፈች፣ ቻይና "ተመሳሳይ እርምጃዎችን" እንደምትወስድ ተናግራለች።

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ባለፈው ወር የዲፕሎማቶች ልዑካን ላለመላክ እያሰቡ መሆኑን ተናግረዋል።

የኋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ጄን ሳኪ ሰኞ ክልከላውን መደረጉን አረጋግጠው አስተዳደሩ የዚህ አካል አይሆንም ብለዋል።

"የአሜሪካ ዲፕሎማቶች ውድድሩ በዢንጂያንግ አስከፊ የሰብአዊ መብት ረገጣ እና ጭካኔ እየተካሄደ ባለበት ወቅት መሆኑ የተለመደው የቻይና መደበኛ እንቅስቃሴ አድርገው ይመለከቱታል። እኛ ያንን ማድረግ አንችልም" ሲሉ ገልጸዋል።

ሳኪ አክለውም የአሜሪካ መንግሥት እንዳሉት "ለውድድሩ ሲዘጋጁ የነበሩ ስፖርተኞች መቅጣት ትክክለኛው እርምጃ ነው" ብሎ አያስብም። ሆኖም በውድድሩ ላይ የአሜሪካ ልዑካንን አለመላክ "ግልጽ መልዕክት ሊያስተላልፍ ይችላል" ብለዋል።

"የፖለቲካ መድረክ"

በዋሽንግተን ቻይና ኤምባሲ በበኩሉ የአሜሪካን ውሳኔ አስመልክቶ በሰጠው ምላሽ ድርጊቱ "የኦሊምፒክ መንፈስን በእጅጉ የሚጻረር ነው" ብሏል።

"እነዚህ ሰዎች መጡ ቀሩ አይመጡ ማንንም አያሳስብም። በቤጂንግ 2022 የክረምት ኦሊምፒክ ላይም ምንም ዓይነት ተጽእኖ የለውም" ሲሉ ቃል አቀባዩ ሊዩ ፔንግዩ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

ሊዩ አክለውም ለአሜሪካ ፖለቲከኞች ምንም ግብዣ እንዳልቀረበላቸው ገልጸው "ስለዚህ ይህ 'የዲፕሎማቶች አለመሳተፍ' ከየት እንደመጣ አይታወቅም" ብለዋል።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዣኦ ሊጂያን ከውሳኔው ቀደም ብሎ እንደተናገሩት "አሜሪካ የራሷን መንገድ ለመያዝ ካሰበች ቻይናም ተመሳሳይ እርምጃዎችን ትወስዳለች" ብለዋል ።

"የክረምት ኦሊምፒክ ጨዋታዎች የፖለቲካዊ ፍላጎት መጠቀሚያ መድረክ አለመሆኑን አፅንኦት መስጠት እፈልጋለሁ" ሲሉ ዣኦ በመደበኛ ጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ ተናግረዋል ።

በቻይና ማህበራዊ ድር አምባ ዌይቦ ላይ "የአሜሪካ ዲፕሎማቶች በቤጂንግ የክረምት ኦሊምፒክ ያለመሳተፍ ውሳኔ" የሚለው የፍለጋ ርዕስ ከማክሰኞ ማለዳ ጀምሮ ሳንሱር ተደርጓል።

ግሎባል ታይምስ በተባለው የመንግሥት ሚዲያ ላይ ከወጣው ጽሁፍ በታች ያሉት አብዛኛዎቹ አስተያየቶች ተሰርዘዋል። ከ1 ሺህ 500 የሚጠጉ አስተያየቶች ውስጥ ስምንቱ ብቻ ናቸው ያልተነኩት።

"ኦሊምፒክ የስፖርተኞች ነው። ከፖለቲከኞች ጋር ምን አገናኘው? ላለመሳተፍ ብትወስኑ የሚጎዱት የራሳችሁ ሃገር ሰዎች (ስፖርተኞችን ጨምሮ) ነው" ይላል አንዱ አስተያየት።

ከአሜሪካ እና ከሌሎች ሀገራት የተወከሉ ከፍተኛ የመንግሥት ተወካዮች ብዙውን ጊዜ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ ይገኛሉ።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ቀዳማዊት እመቤት ጂል ባይደን በቶኪዮ በተካሄደው የበጋ ኦሎምፒክ የአሜሪካን ልዑካን መርተው ተገኝተዋል።

አሜሪካ ውስጥ የዲፕሎማቶች አለመሳተፍ ውሳኔው በዲሞክራቲክ እና ሪፐብሊካን ህግ አውጭዎች ድጋፍ አግኝቷል።

የሪፐብሊካኑ የዩታ ሴናተር ሚት ሮምኒ በትዊተር ገፃቸው እንዳስታወቁት የባይደን አስተዳደር በኦሊምፒክ የዲፕሎማቶች ተሳትፎን እንዳይኖር "መከልከሉ ማለቱ ትክክል ነው" ብለዋል። ዲሞክራቷ የምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲም ውሳኔውን አድንቀዋል።

"ስፖርተኞቻችንን መደገፍ እና ማክበር ቢኖርብንም አሜሪካ እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለእነዚህ ጨዋታዎች የእኛን ይፋዊ ድጋፍ መስጠት አንችልም። ወይም ኦሊምፒክ የዘር ማጥፋት እና ጅምላ የሰብአዊ መብት ረገጣ በሚፈጽምባት ሃገር ውስጥ መካሄዱ ምንም ችግር እንደሌለው አድርገን መቀጠል አንችልም" በማለት ፔሎሲ ተናግረዋል።

አንዳንድ የዩናይትድ ስቴትስ ፖለቲከኞች ግን የዲፕሎማቶች አለመሳተፍ በቂ አይደለም ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

ሴናተር ቶም ኮተን ውሳኔውን "ግማሽ እርምጃ" ሲሉ የገለጹ ሲሆን አስተዳደሩ በውድድሩ ላይ "ሙሉ በሙሉ አለመሳተፍ ነበረበት" ብለዋል።

ቻይና በዚንጂያንግ ራስ ገዝ አስተዳደር ውስጥ በኡይግሮች እና ሌሎች አናሳ የሙስሊም ዜጎች ላይ ጭቆና እየፈጸመች ነው ስትል አሜሪካ ትከሳለች።

ዩናይትድ ኪንግደም እና አውስትራሊያን ጨምሮ ሌሎች ሃገራት ተመሳሳይ እርመጃ ለመውሰድ እያሰቡ ነው ተብሏል።

አሜሪካ ከዚህ ቀደም ሶቪየት አፍጋኒስታንን በመውረሯ ምክያት በአውሮፓውያኑ 1980 ውድድር ስፖርተኞቿ እንዳይሳተፉ አድርጋለች።

ሶቪየት ህብረት እና አጋሮቿ በበኩላቸው በሎስ አንጀለስ የተካሄደውን ቀጣዩን የ1984ቱን የበጋ ኦሊምፒክን ሳይሳተፉ ቀሩ።

አሜሪካ በአውሮፓውያኑ 2028 ኦሊምፒክን በሎስ አንጀለስ ልታዘጋጅ ሽር ጉድ እያለች ነው።