ፌስቡክ በሮሂንጃ የጥላቻ ንግግር ምክንያት የ150 ቢሊዮን ፓውንድ ክስ ቀረበበት

የሮሂንጃ ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በአሜሪካና ዩናይትድ ኪንግደም የሚገኙ በደርዘን የሚቆጠሩ የሮሂንጃ ስደተኞች ፌስቡክ በማህበረሰባቸው ላይ የጥላቻ ንግግር እንዲሰራጭ ፈቅዷል በማለት ግዙፉን የማህበራዊ ሚዲያ ከሰዋል።

የፌስቡክ መድረኮች በሮሂንጃ ማህበረሰብ ላይ ጥቃት አበረታተዋል በማለት ከ150 ቢሊዮን ፓውንድ (200 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ) ካሳ ጠይቀዋል።

በቀድሞዋ በርማ ወይም የምይናማር በአውሮፓውያኑ 2017 በተደረገ ወታደራዊ ዘመቻ ከ10 ሺህ የሚልቁ የሮሂንጃ ሙስሊሞች ተገድለዋል።

ምይናማር አብዛኛው ህዝቧ የሂንዱ እምነት ተከታይ ነው።

በአሁኑ ወቅት ሜታ እየተባለ የሚጠራው ፌስቡክ ለቀረበበት ክስ ወዲያውኑ ምላሽ አልሰጠም።

ኩባንያው "በጥላቻ የተሞሉ እና አደገኛ የሆኑ የተሳሳቱ መረጃዎችን ማሰራጨቱ ለዓመታት እንዲቀጥል ፈቅዷል" በሚል ተከሷል።

በእንግሊዝ አንዳንድ የሮሂንጃ ስደተኞችን ወክሎ እየተከራከረ ያለው የብሪታኒያ የህግ ተቋም ለፌስቡክ የፃፈውን ደብዳቤ ቢቢሲ የተመለከተ ሲሆን የተዘረዘሩትም ዋና ዋና ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው።

  • የፌስቡክ ስልተ ቀመሮች (አልጎሪዝም) በሮሂንጃዎች ላይ የጥላቻ ንግግርን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲታዩ አድርጓል።
  • ድርጅቱ በምንያማር ስላለው የፖለቲካ ሁኔታ የሚያውቁና መረጃዎችን የሚያጣሩ ተቆጣጣሪዎችን መቅጠር አልቻለም።
  • ኩባንያው በሮሂንጃ ላይ ሁከት የሚቀሰቅሱ ፅሁፎችን (ልጥፎችን) ማውረድም ሆነ መሰረዝ አልቻለም።
  • በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና በመገናኛ ብዙኃን ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም ኩባንያው "ተገቢ እና ወቅታዊ እርምጃ" መውሰድ አልቻለም።

በአሜሪካ ጠበቆች በሳንፍራንሲስኮ ፌስቡክ ቢሮ ላይ "በደቡብ ምሥራቅ እስያ በምትገኝ ትንሽ ሀገር ውስጥ ለተሻለ የገበያ ትስስር በሮሂንጃ ሕዝብ ሕይወት ለመገበያየት ፈቃደኛ ነው" በማለት ኩባንያውን ከሰውታል።

በአውሮፓውያኑ 2013 "ሂትለር አይሁዶች ላይ ባደረገው መንገድ እነሱን ልንዋጋቸው ይገባል" በማለት በሮይተርስ የዜና ወኪል ባደረገው ምርመራ ላይ የወጣውን ይህንን ፅሁፍ ጨምሮ ሌሎች የፌስቡክ ፅሁፎችን ዋቢ አድርገዋል።

ሌላኛው በፌስቡክ የወጣ ፅሁፍ እንዲሁ "ነዳጅ አፍስሱና እሳት ለኩሱባቸው አላህን በፍጥነት ይገናኛሉ።" ይላል።

ፌስቡክ በምይናማር ከ20 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች አሉት። ለብዙዎች የማህበራዊ ድህረ-ገጹ ዋነኛ ወይም ብቸኛ ዜና የማግኛ ምንጭ እና የማጋሪያ መንገድ ነው።

ፌስቡክ በአውሮፓውያኑ 2018 በሮሂንጃ ላይ የሚደርሰውን ጥቃት እና የጥላቻ ንግግር ለመከላከል በቂ ስራ እንዳልሰራ አምኗል።

ድርጅቱ ይህንን ያለው የፌስቡክ መድረክ ለሰብዓዊ መበት ረገጣ መስፋፋት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል የሚል በራሱ በድርጅቱ የተሰራ ገለልተኛ ሪፖርትን ተከትሎ ነው።

የሮሂንጃ ማህበረሰብ በምይናማር እንደ ህገወጥ ስደተኛ ተደርገው የሚታዩ ሲሆን በመንግሥት እና በህዝቡ ለአመታት አድሎ ሲደርስባቸው ቆይቷል።