ምያንማር ሮሂንጂያ፡ ሳን ሱ ቺ የቀረበባቸውን የዘር ማጥፋት ክስ ተቃወሙ

የማያንማር መሪ ሳን ሱ ቺ በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት -ዘ ሄግ ሲናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በተባበሩት መንግሥታት ፍርድ ቤት [አይ ሲ ጀ] የቀረቡት የምያንማር መሪ አን ሳን ሱ ቺ ፤ አገራቸው የቀረበባትን የዘር ማጥፋት ወንጀል ክስ ተቃውመዋል።

የዓለም የኖቤል ሰላም ሎሬት የሆኑት ሳን ሱ ቺ ክሱን የተቃወሙት የቀድሞዋ በርማ የአሁኗ ምያንማር በሮሂንጂ ሙስሊሞች ላይ ጭካኔ የተሞላበት የዘር ጭፍጨፋ ፈፅማለች በሚል በስፋት የተሰራጨውን ክስ በተመለከተ ነው።

በመክፈቻ ንግግራቸው በምያንማር ላይ የቀረበው ክስ "ያልተሟላና ትክክል ያልሆነ" ብለውታል።

አክለውም ከክፍለ ዘመናት በፊት በርካታ ሮሂንጃዎች ይኖሩበት በነበረው ረካይን ግዛት ችግሮች እንደነበሩ አውስተዋል።

የቡዲሂስት እምነት ተከታዮች የሚበዙባት ምያንማር በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር 2017 ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ ወስዳ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሮሂንጃ ሙስሊሞች ሲገደሉ ከ700 ሺህ በላይ የሚሆኑት ወደ ጎረቤት አገር ባንግላዴሽ ተሰደዋል።

ምያንማር ሁል ጊዜም ቢሆን በረካይን ግዛት የፅንፈኞችን ጥቃት ለመከላከል ጥረት ታደርጋለች። በመሆኑም ሳን ሱ ቺ ይህንን አቋም በመያዝ፤ ጥቃቱን "ውስጣዊ የወታደሮች ግጭት" ነበር፤ ይህም የሮሂንጃን ታጣቂዎች በመንግሥት የፀጥታ አካላት ላይ ጥቃት በመፈፀማቸው የተቀሰቀሰ ነው ብለውታል።

ሳን ሱ ቺ "በዚህ ጊዜ የምያንማር ወታደሮች ያልተመጣጠነና ያልተገባ ኃይል ተጠቅመው ይሆናል፤ በመሆኑም ወታደሮች የጦር ወንጀሎችን ፈፅመው ከሆነ እነርሱ ሊከሰሱ ይገባል" ብለዋል።

በምያንማር ህዝብ ዘንድ ተደማጭነት እንዳላቸው የሚነገርላቸው ሳን ሱ ቺ፤ ያላቸው ሥልጣን ውሱን መሆኑ ቢነገርም የተባበሩት መንግሥታት መርማሪዎች አገኘነው ባሉት 'ውስብስብ መረጃ' ምክንያት ግን ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ይህም ለአራት ዓመታት በቁም እስር ላይ ላዋላቸው ጦር እንዲቆሙ የተመረጡት ሳን ሱ ቺ ትልቅ ውድቀት ነው ተብሏል።

ሳን ሱ ቺ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት አገራቸው ከራካይን የተሰደዱት ሰዎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ቁርጠኛ መሆኗን በመግለፅ፤ ፍርድ ቤቱ ግጭቱን እንዲያገረሽ ሊያደርግ የሚችል ድርጊት መፈፀሙን እንዲያቆም አሳስበዋል።

ይህንን ንግግራቸውን በቴሌቪዥን የተከታተሉ እና በባንግላዴሽ በኩቱፓሎንግ የስደተኖች ካምፕ የሚገኙ ስደተኞች "ውሸታም ፣ ውሸታም፣ አሳፋሪ" እያሉ በመጮህ ተቃውሟቸውን ሲገልፁ ነበር።

ከስደተኞቹ አንዱ የሆነው የ52 ዓመቱ አብዱ ራሂም "ውሸታም ናቸው፣ ትልቅ ውሸታም" ሲል ገልጿቸዋል።

ከሄግ ፍርድ ቤት ውጭ የሮሂንጃ ሙስሊሞች ደጋፊ የሆኑ የተወሰኑ ሰዎች በቡድን በመሆን " ሳን ሱ ቺ፤ በአንቺ አፍረናል!" ሲሉ ተደምጠዋል።

በሌላ በኩል የእርሳቸው ደጋፊ የሆኑ ወደ 250 የሚጠጉ ተቃዋሚዎች የእርሳቸውን ምስል በመያዝ " ከጎንዎ ነን!" ሲሉ ድጋፋቸውን አሳይተዋል።

የምያንማር ዜጋ የሆነችውና አሁን ኑሮዋን በአውሮፓ ያደረገችው ፖ ፕዩ የሰልፉ አንዷ አስተባባሪ ስትሆን "ዓለም በአን ሳን ሱ ቺ ይበልጥ ትዕግስተኛ መሆን ይጠበቅበታል" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

"እስካሁን በእርሷ እምነት አለን፤ እንደግፋታለን። በአገራችን ሰላምና ብልፅግና ያመጡ እና ይህንን ውስብስብ ችግር የፈቱ ብቸኛ ሰው ናቸው" በማለትም አክላለች።

ሳን ሱ ቺ ከዓመታት በፊት በሰብዓዊ እና ፖለቲካዊ መብት ተሟጋችነታቸው ሰበብ በተደጋጋሚ ለእስር እና እንግልት ተዳርገዋል። ለዚህ በጎ ተግባራቸውም እ.ኤ.አ. በ1991 የኖቤል ሰላም ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የተሰጣቸው የኖቤል ሽልማት እንዲነጠቅ የሚጠይቁ ወገኖችም ቢበራከቱም ኮሚቴው ግን ሽልማቱን መንጠቅ እንደማይችል ማስታወቁ ይታወሳል።

Presentational grey line